1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከንግድ ቦታቸዉ የተነሱ ነጋዴዎች ቅሬታ በድሬዳዋ

ሰኞ፣ ኅዳር 20 2014

የድሬደዋ አስተዳደር በከተማዋ ዋና ዋና ባላቸው መንገዶች ዳርቻ የሚገኙ የኮንቴይነር መሸጫ ሱቆች እንዲነሱ ባሳለፈው ውሳኔ ላይ የተለያዩ ነጋዴዎች ቅሬታ አቅርበዋል፡፡ ለረጅም ዓመታት ንግድ ፍቃድ አውጥተው ሲሰሩ ከቆዩበት ቦታ በአጭር ቀን እንዲነሱ የተሰጠው ውሳኔም ሆነ ለንግድሥራው አመቺ ባለመሆኑ ችግራቸው እንዲታይ ጠይቀዋል፡፡

https://p.dw.com/p/43cg8
Äthiopien Diredawa Shops
ምስል Mesay Tekelu/DW

ለሥራ ምቹ የሆነ ቦታ እንዲዘጋጅላቸው ጠይቀዋል

የድሬደዋ አስተዳደር በከተማዋ ዋና ዋና ባላቸው መንገዶች ዳርቻ የሚገኙ የኮንቴይነር መሸጫ ሱቆች እንዲነሱ ባሳለፈው ውሳኔ ላይ የተለያዩ ነጋዴዎች ቅሬታ አቅርበዋል፡፡ ለረጅም ዓመታት ንግድ ፍቃድ አውጥተው ሲሰሩ ከቆዩበት ቦታ በአጭር ቀን እንዲነሱ የተሰጠው ውሳኔም ሆነ በተለዋጭነት የተሰጣቸው ቦታ ለንግድ ሥራው አመቺ ባለመሆኑ ችግራቸው እንዲታይ ለዶይቼ ቬሌ በሰጡት አስተያየት ጠይቀዋል፡፡ የአስተዳደሩ ንግድ ፀ/ቤት የከተማዋን ውበት እና ደረጃ ከማስጠበቅ ባለፈ ነጋዴዎቹ አስተዳደሩ በሚያዘጋጀው ህጋዊ ቦታ ሥራቸውን እንዲሠሩ የሚያስችል ተግባር መሆኑን ገልፇል፡፡

በከተማዋ የተለያዩ የንግድ ሥራዎችን በኮንቴይነር ሱቆች ሲያከናውኑ መቆየታቸውን የገለፁ ነጋዴዎች በአጭር ቀናት ከሚሰሩበት ቦታ እንዲነሱና ለሥራ ምቹ ወዳልሆነ ቦታ እንዲዘወሩ በአስተዳደሩ የተወሰነው ውሳኔ ላይ ቅሬታቸውን ለዶይቼ ቬሌ ገልፀዋል።

ብድር ወስደው እየሠሩ ባሉት አነስተኛ ሥራ ትርፋማ ሆነው ብድራቸውን መመለስ እንዲችሉ ለሥራ ምቹ የሆነ ቦታ ሊዘጋጅላቸው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

Äthiopien Diredawa Shops
ምስል Mesay Tekelu/DW

የድሬደዋ አስተዳደር ንግድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሚኑ ጠሀ በዋና ዋና ጎዳናዎች እየሠሩ ያሉ ነጋዴዎችን በመስተዳድሩ ወደሚዘጋጁ ገበያ ማዕከላት የማምጣት እና የከተማዋን ደረጃ የማስጠበቅ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ውሳኔው ለረዥም አመታት በሥራ ውስጥ በቆዩት እነዚህን ሱቆች የሚተዳደሩ ነጋዴዎች ዳግም ወደ ሥራ አጥነት ከመመለስ ባለፈ አብዛኞቹ የሚንቀሳቀሱበትን የመንግሥት ብድር ለመመለስ አይቸገሩም ወይ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰተዋል፡፡

ላለፉት አመታት መንግሥት ሲያከናውን በቆየው የሥራ እድል ፈጠራ ሂደት ትኩረት ከሆነው የመሸጫ ቦታ ማመቻቸት ጋር በተያያዘ ባልተጠና መልኩ በርካታ የኮንቴይነር የንግድ ሱቆች በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች እንዲቀመጡ ተደርጓል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ጉራማይሌ በሆነ መልክ የኮንቴይነር ሱቆችን ማስቀመጥ ዛሬም ላለመቆሙ አብነቶቹ ብዙ ናቸው፡፡

መሳይ ተክሉ

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ