1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከቡራዩ ተወሰዱ ስለተባሉ የኦነግ አመራር

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 17 2015

በቡራዩ ፖሊስ ጣቢያ ከአንድ ዓመት በላይ ታስረው ቆይተዋል የተባሉት ሰባት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አመራር ዱከም ፖሊስ ጣቢያ እንደሚገኙ ፓርቲው እና የታሳሪዎች ቤተሰቦች አመለከቱ ። አመራሩ ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ ወደየት እንደተወሰዱ አላውቅም ሲል ፓርቲው በሳምንቱ መጨረሻ ባወጣው መግለጫ ዐሳውቆ ነበር ።

https://p.dw.com/p/4QXBE
 Logo Oromo Liberation Front

ፓርቲና ቤተሰብ፦ ታሳሪዎቹ ዱከም ታይተዋል ይላሉ

በቡራዩ ፖሊስ ጣቢያ ከአንድ ዓመት በላይ ታስረው ቆይተዋል የተባሉት ሰባት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አመራር ዱከም ፖሊስ ጣቢያ እንደሚገኙ ፓርቲው እና የታሳሪዎች ቤተሰቦች አመለከቱ ። አመራሩ ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ ወደየት እንደተወሰዱ አላውቅም ሲል ፓርቲው በሳምንቱ መጨረሻ ባወጣው መግለጫ ዐሳውቆ ነበር ።  የኦነግ አመራር ከዓመት በላይ ከቆዩበት ቡራዩ ፖሊስ ጣቢያ ዱካቸው የተሰወረው ከምርጫ ቦርድ እና ከፖለቲካ ድርጅቶች የተውጣጣ ኮሚቴ የእስር ሁኔታውን ለመጎብኘት ካቀደበት አንድ ቀን አስቀድሞ መሆኑን ፓርቲው ገልጧል ።


የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) በባለፈው ሳምንት መጨረሻ ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳመለከተው በቡራዩ ፖሊስ ጣቢያ ለአንድ ዓመት ከ2 ወራት ገደማ የታሰሩ ሰባቱ አመራር አባላቱ ከእስር ተወስደው ወዴት እንዳሉ አይታወቅም ይላል ።   ዱካቸው ጠፍቶኝ የታሰሩበትን እያፈላለኩ ነው ሲል ኦነግ መግለጫ ያወጣባቸው ሰባቱ ታሳሪ ጓዶቹ፤ አቶ አብዲ ረጋሳ፣ ሚካኤል ቦረን፣ ከነሳ አያና፣ ዶ/ር ገዳ ኦልጂራ፣ ዳዊት አብደታ፣ ገዳ ገቢሳ እና ለሚ ቤኛ ናቸው ፡፡

የኦነግ የፖለቲካ ኦፊሰር አቶ በቴ ዑርጌሳ ዛሬ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት ግን ለቀናት ዱካቸው ጠፍቶ የቆየው በእስር ላይ ያሉ የኦነግ አመራር አባላቱ ዱካም ፖሊስ ጣቢያ መገኘታቸውን ገልጸዋል፡፡ 
«ዱከም ፖሊስ ጣቢያ ቤተሰብ ከሩቅ አግኝቶአቸዋል፡፡ ሁሉም በዚያው አንድ ላይ ነው ያሉት» ያሉን አቶ በቴ ዑርጌሳ፤ ከዚህ በፊት በፀና ታመው በህክምና ክትትል ላይ የነበሩት አቶ ከነሳ አያና ከሌሎች ባልደረቦች ጋር በዚያው መኖራቸው ቢታወቅም ለቤተሰቦቻቸው አለመታየታቸውን አክለው ገልጸዋል ። ቤተሰብ ምግብ ከርቀት ከማቀበል ባለፈ እንደወትሮው እስረኞቹን ቀረብ ብለው ማየትና ማነጋገር እንዳልተፈቀደላቸውም አንስተዋል ፡፡

ሌላው አስተያየታቸውን የሰጡን ከእስረኞቹ አንዱ የሆኑት የአቶ ዳዊት አብደታ ወንድም አቶ ብርሃኑ አብደታ እስረኞቹ በዱካም መሆናቸውን እንደመረጃ ብሰሙም ቀርበው መጠየቅ ቀላል እንዳልሆነላቸው አንስተውልናል፡፡ «ከቡራዩ ያነሱዋቸው ባለፈው ማክሰኞ ከሰዓት 11፡00 አከባቢ ነው፡፡ ከዚያን ወዴት እንደወሰዱዋቸው ማወቅ አዳግቶን ነበር፡፡ አሁን በወሬ ወሬ ስንሰማ ዱከም ፖሊስ ጣቢያ እንዳሉ ነው፡፡ ነገር ግን ቀረብ ብለን መጠየቅ ቀላል አልሆነልንም፡፡ እዚህ መኖራቸውን ሰምተን መጣን ስንላቸው ማን ብሎአችሁ ነው እያሉ ለማስተናገድ ፈቃደኛ አለመሆን ይስተዋላል፡፡ እንደውም ይቆጡሃል፡፡ ይህ ነገር የሆነው ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ኮሚቴ አዋቅሮ ወደዚያ በመላክ የእስር ሁኔታውን ለመጎብኘት ባቀደበት ነው፡፡ ኮሚቴው ወደ ቡራዩ ሄዶ ከዚያ አጥቶአቸዋል፡፡ ድንገት ከዚያ ስለተወሰዱ የሚለብሱት የላቸው ምን እንደሚመገቡ እንኳ አናውቅም ።»  

ከዚህ በፊት እነዚህ አመራሮች ያለአግባ የተራዘመ እስር ላይ መሆናቸውን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ይፋዊ መግለጫ እንዳወጡባቸው ያስታወሱት የኦነግ ባለስልጣን አቶ በቴ ዑርጌሳ፤ ፓርቲው ይደርስብኛል የሚለውን ጫና በማስመልከት ለምርጫ ቦርድ እና ሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ተደጋጋሚ አቤቱታዎችን ሲያስገባ እንደነበርም ገልጸዋል፡፡ 
የኦነግ ባለስልጣናቱ ከእስር ቤት ወደ እስር ቤት እየተላለፉ ሲታሰሩ እንደነበሩ የገለጹት አቶ በቴ፤ በእስር ላይ የሚገኙትም ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ መሆኑን ዘርዝረዋል ።
 
ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና ከተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች የተውጣጡ 5 አባላት ያለው ኮሚቴ እስረኞቹን ለመጎብኘት አቅዶ ደብዳቤ ለኦሮሚያ ፖሊስ መጻፉን ተከትሎ እስረኞቹ ዱካቸው እንዲጠፋ ሆኗል በማለትም ድርጊቱ ሆን ተብለሎ እስረኞቹ ያሉበትን ሁኔታ ላለማሳየት የተደረገ እንደሆነ አንስተዋል፡፡ “የኮሚቴዎቹ አባላት አንድ ከምርጫ ቦርድ፣ አንድ ከገዢው ብልጽግና ፓርቲ፣ አንድ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) እና ሁለት ደግሞ ከአመልካቹ ፓርቲ ኦነግ ናቸው፡፡”

ይሁንና እነዚህን እስረኞች ያሰረው መንግስት በመሆኑ ያሉበትን የመጠቆምም ሆነ ያሰሩበትን ምክኒያት መጠቆም ያለበት መንግስት ነው ብለዋል፡፡ ይህንኑን በማስመልከትም ከክልል እስከ ፌዴራል መንግስት የላይኛው አስፈጻሚ አካላት እንዲሁም ለፍርድ ቤቶች ደብዳቤ ጽፈውም ምላሽ አለማግኘታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ከባለፈው ዓመት የካቲት ወር ጀምሮ ለአንድ ዓመት ከ2 ወር ከታሰሩበት ቡራዩ ፖለስ ጣቢያ ድንገት ተሰወሩ ስለተባሉት ሰባቱ የኦነግ አመራሮች፤ ከኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን እና ከቡራዩ ፖሊስ መምሪያ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለዛሬ አልሰመረም፡፡ ከዚህ በፊት ግን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ለነበሩት ባለስልጣን ጥያቄውን አቅርበን እነዚህ አመራሮች ታጣቂዎች ጋር በመስራት እንደሚጠረጠሩ መግለፃቸው ይታወሳል ።

ሥዩም ጌቱ 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ