1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከቡሌ ቦራ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ቅሬታና የመንግሥት ምላሽ 

ዓርብ፣ ጥር 3 2011

ከቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ተፈናቅለው ለአንድ ወር ያህል በባህር ዳር ሰታዲዮም ተጠልለው የሚገኙ 2ሺህ 500 የሚሆኑ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲው እንደማይመለሱ አመለከቱ፣ የኢኖቬሽንና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ደግሞ ወደ ዩኒቨርሲቲው አለመመለስ የግል ውሳኔ ነው ይላል፡፡

https://p.dw.com/p/3BOEG
Äthiopien Bulehora Universität Studenten
ምስል DW/Alemnew Mekonnen

ተማሪዎች ምህርታቸውን ይቀጥላሉ የሚል አምነት አለን

በቡሌ ሆራ ዩኒቭርሲቲ ሲማሩ የነበሩ ተማሪዎች ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ምክንት ብዙዎቹ ዩኒቨርሲቲውን ለቅቀው ወደየ ትውልድ አካባቢያቸው ተመልሰዋል፡፡
ከአንድ ወር በፊት ወደ ባሕር ዳር የመጡት የአማራ ክልል ተወላጆችም በጊዚያዊነት በባህር ዳር ሰታዲዮም ተጠልለው ይገኛሉ፡፡ በቅርቡ የኢኖቬሽንና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ጥር 1 እና 2 /2011 ዓ.ም ተማሪዎቹ ወደ ነበሩበት ዩኒቨርሲቲ እንደሚመለሱ በብዙኃን መገናኛ ዘዴዎች መግለጫ መስጠቱ ይታወሳል፡፡
ታዲያ ይህንን ጥሪ ተቀብለው ወደ ነበሩበት ዩኒቨርሲቲ እንደማይመለሱ ነው በባህር ዳር ሰታዲየም በጊዚያዊነት ተጠልለው ከሚገኙት መካከል ያነጋገርኳቸው የቡሌ ሆራ ተማሪዎች የሚናገሩት። በተለይም ሴቶች ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ተግባሮች እንደተፈፀሙባቸው ነው የሚናገሩት ። በዚህም ምክንያት ወደ ቡሌ ሆራ እንደጋና መመለስ አይታሰብም ያ የሚሆን ከሆነ ሌላ ቅጣት መሆኑን በምሬት ተናግረዋል። 
ሀገር የምንኖርበት እንጂ እየሞትን የምንገነባው አይደለም ያሉት ተማሪዎቹ መንግስት ቀርቦ ችግራቸውን ከስር መሰረቱ እንዲያውቅላቸው ጠይቀዋል፡፡ መንግስት በአማራ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሰቲዎች አንዲመድባቸው ነው ሁሉም «DW» ያነጋገራቸው ተማሪዎች የተናገሩት፡፡
ስለጉዳዩ እንዲነግሩኝ የትምህርት ሚኒስትር የህዝብ ግንኙነት ዳይረክተሯን በስልክ ለማነጋገር ብሞክርም ፈቃደኛነታቸውን ከገለፁልኝ በኋላ ቀጠሮ በያዙልኝ ሰዓት ብደውልና ስልካቸው ቢጠራም አንስተው ለማነጋገር አልፈቀዱም፡፡  የፌደራል መንግስት የኢኖቬሽንና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ በአጭር የእንግሊዝኛ ጽሁፍ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ “ተማሪዎቹ  በሚፈልጓቸው ዩኒቭርሲቲዎች መመደብ የሚሆን አይደለም፣ የተለያዩ መስፈርቶችን ተመልክቶ ምደባውን በመላ አገሪቱ በሚገኙዩ ኒቨርስቲዎች የሚመድበው የትምህርት ሚኒስቴር ነው፣ ቡሌሆራ ተፈጥሮ በነበረው ችግር ምክንያት ከዩኒቨርሲቲው ወጥተው የነበሩ ተማሪዎችን ከጥር 2/2011 ዓ.ም ጀምሮ እንደገና እየመዘገበ ነው፡፡ ሁሉም ተማሪዎች አንደገና ተመዝግበው ትምህርታቸውን ይቀጥላሉ የሚል አምነት አለን፣ ያን አለማድረግ ግን የራስ ውሳኔ ነው” ቡሌ ሆራ ዩኒቨረሲቲ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ዉስጥ ይገኛል፡፡

Äthiopien Bulehora Universität Studenten
ምስል DW/Alemnew Mekonnen

ዓለምነው መኮንን

አዜብ ታደሰ 

አርያም ተክሌ