1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚኢትዮጵያ

ከሜቴክ ጥላ ያልተላቀቀው ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ

ረቡዕ፣ ግንቦት 2 2015

ከ12 ቢሊዮን ብር በላይ ዕዳ ያለበት ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 100 ሚሊዮን ብር ገደማ ማትረፉን አስታውቋል። በመስከረም 2013 የተቋቋመው ኩባንያ አመራሮች ማሻሻያ ተግባራዊ እያደረጉ መሆኑን ቢናገሩም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተደረገ ውይይት ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ከቀድሞው ሜቴክ ችግሮች እምብዛም እንዳልተላቀቀ ጠቁሟል

https://p.dw.com/p/4RAJI
Äthiopien Parlament Addis Abeba
ምስል Solomon Muche/DW

ከሜቴክ ጥላ ያልተላቀቀው ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ወይዘሮ መሠረት ዳምጤ የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ አመራሮች ባለፈው ሣምንት ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ተግባራዊ እያደረጓቸው ስለሚገኙ የማሻሻያ እርምጃዎች ማብራሪያ ከመስጠታቸው በፊት ተቋሙ «መቀጠል የለበትም» የሚል አቋም ላይ ደርሰው ነበር። ዋና ኦዲተሯ በተቋሙ ላይ የያዙትን ጠንከር ያለ አቋም የፌድራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በኢትዮ ኢንጂኔሪንግ ግሩፕ የቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ማምረቻ ኢንዱስትሪ ላይ በ2013 እና 2014 በጀት ዓመት ያካሔደውን የክዋኔ ኦዲት ላይ ሲወያይ «እኔ አሁን የሰጡት አስተያየት ሐሳቤን ቀየረው እንጂ ይኸን የገንዘብ መጠን መነሻ አድርጓ ተቋሙ መቀጠል የለበትም የሚል ድምዳሜ ልሰጥ ነበር ተዘጋጅቼ የመጣሁት» ሲሉ ተናግረዋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሚያዚያ 25 ቀን 2015 ይኸ ውይይት የተካሔደው የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ እና የተቋሙ አመራሮች በተገኙበት ነው። የፍትህ ሚኒስቴር፣ የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር፣ የመንግሥት ግዥ አገልግሎት፣ የፌደራል የሥነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን እና የመንግሥት ልማት ድርጅቶች የተወከሉ ባለሥልጣናትም በመድረኩ ነበሩ። የመንግሥት ተቋማትን የበጀት አጠቃቀም በአይነ ቁራኛ የሚከታተለውን ተቋም የሚመሩት ዋና ኦዲተሯ ተቋሙ «መቀጠል የለበትም» ከሚል ድምዳሜ ያደረሳቸው መሥሪያ ቤታቸው ያካሔደው የክዋኔ ኦዲት ውጤት ነው። በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በንባብ የቀረበው የኦዲት ሪፖርት ተቋሙ 12 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ዕዳ እንዳለበት ይፋ አድርጓል።

ተቋሙ «ከ2002 እስከ 2011 ባሉት ዓመታት በ952.5 ሚሊዮን ዶላር እና በ27.8 ሚሊዮን ዩሮ  በላይ በሆነ ገንዘብ ከመመሪያ እና ከፍላጎት ውጭ ግዥ ለመፈጸም ውል መግባቱ» ባለፈው ሣምንት በተካሔደው ውይይት የተነሳ ሌላ ዕክል ነው። ህጋዊ የግዥ ሂደት ያልተከተለ እና ሰነዶች ያልቀረቡበት ግዥ መፈጸሙ፣ ተቋማዊ አቅምን ያላገናዘቡና አፈጻጸማቸው በእንጥልጥል የቀሩ የሥራ ውሎች መደረጋቸው አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ በሚመሩት ተቋም ውስጥ ከተገኙ ችግሮች መካከል ናቸው።

ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ራሱን ችሎ የተቋቋመው በመከላከያ ሚንስቴር ሥር የነበረው የብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ለሁለት ከተከፈለ በኋላ በመስከረም 2013 ነበር። በ10 ቢሊዮን ብር የመነሻ ካፒታል ከ13 ዓመታት ገደማ በፊት የተቋቋመው ሜቴክ የታላቁ የኅዳሴ ግድብ ግንባታን ጨምሮ በርካታ ሥራዎች እንዲያከናውን ቢታቀድም አልሆነለትም። በሜቴክ ይገነባሉ የተባሉት ፋብሪካዎች እና መሠረተ-ልማቶች ሳይሳኩ ቀርተው ውሎቹ ተሰርዘዋል፤ ሙስና እና ብልሹ አሰራርን በመሳሰሉ ጥፋቶች የተከሰሱት የኩባንያው አመራሮችም ታስረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን ከያዙ በኋላ መንግሥታቸው በወሰዳቸው እርምጃዎች ሜቴክ ለሁለት ሲከፈል መከላከያ ኮርፖሬሽን ኢንጂኔሪንግ ራሱን የቻለ ተቋም ሆኗል።

አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ በዋና ሥራ አስፈጻሚነት የሚመሩት ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ማምረቻ ኢንዱስትሪ እና የብረታ ብረት ፋብሪኬሽን ኢንዱስትሪን ጨምሮ በሥሩ ዘጠኝ ማምረቻዎች ይገኛሉ። አምባሳደር ሱሌይማን ተቋሙን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት እንዲመሩ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተሾሙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ የሆኑትን አምባሳደር ምሥጋኑ አረጋን በመተካት ባለፈው ጥር ወር ነበር። የቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ማምረቻ ኢንዱስትሪ ሥራ አስኪያጅ አቶ መስፍን መንግሥቱ ባለፈው ሣምንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ፊት ኩባንያው ተግባራዊ እያደረጋቸው የሚገኙ ማሻሻያዎችን ዘርዘር አድርገው አቅርበዋል።

"ኦዲት በተደረገበት ጊዜ ወደ 20 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ዕዳ ውስጥ ነበረ" ያሉት የቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ማምረቻ ኢንዱስትሪ ሥራ አስኪያጅ አቶ መስፍን መንግሥቱ "በዘንድሮው ዓመት የዘጠኝ ወር አፈጻጸማችንን ስናይ ኢንደስትሪው ወደ 101 ሚሊዮን ብር አትርፏል" ሲሉ ተናግረዋል። የፌዴራል ዋና ኦዲተር ወይዘሮ መሠረት ዳምጤ በተቋሙ ተግባራዊ እየተደረጉ ማሻሻያዎች ቢያደንቁም መፍትሔ የሚያሻቸው በርካታ ችግሮች መኖራቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎም ሆኑ ሌሎች የተቋሙ አመራሮች በተለይ በዕዳ ረገድ ለተነሱ ጥያቄዎች በቀጥታ መልስ ሳይሰጡ ቀርተዋል። ዋና ሥራ አስፈሚው ተቋሙ ለገባበት ቀውስ በዋናነት የቀደሙ አመራሮችን ተችተዋል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚው በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ የሚገኙት የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ አመራሮች ኃላፊነት ከተረከቡ ጥቂት ወራት ብቻ እንደሆነ ጠቅሰው «በብቃት ተመዝነው» የተሾሙ እንደሆኑ አስረድተዋል። በተቋሙ ሥር የሚገኙ ማምረቻዎች አደረጃጀት እየተቀየረ መሆኑን የገለጹት አምባሳደር ሱሌይማን «ለስርቆት እና ለሌብነት የማይመች አሠራር» በመዘርጋት ኢንዱስትሪውን ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ከውጭ የሚያስገባቸውን ዕቃዎች በመገጣጠም ላይ ያተኮረው ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ  «አምራች እንዲሆን» መታቀዱንም ገልጸዋል።

ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ