1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከማሊ መፈንቅለ-መንግስት ጀርባ፤የጀርመን ቅኝ ግዛትና የአፍሪቃ የካሳ ጥያቄ

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 23 2012

በምዕራብ አፍሪቃዊቷ ሀገር ማሊ ሰሞኑን መፈንቅለ-መንግስት ያካሄዱት  ወታደራዊ አዛዦች ሩሲያ ውስጥ ሰልጠና መውሰዳቸውን የሚጠቁሙ ዘገባዎች እየወጡ ነው። የሀገሪቱን  ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ቦባካር ኬታ ስልጣን እንዲለቁ ያስገደዱት ወታዳራዊ አመራሮች፤ ከመፈንቅለ መንግስቱ በፊት በሩሲያ ስልጠና ወስደዋል።

https://p.dw.com/p/3hjkR
Präsident von Mali besucht Bundeskanzlerin
ምስል picture-alliance/AP Photo/M. Sohn

ትኩረት በአፍሪካ

ከማሊ መፈንቅለ-መንግስት ጀርባ፤የጀርመን ቅኝ ግዛትና የአፍሪቃ የካሳ ጥያቄ

በምዕራብ አፍሪቃዊቷ ሀገር ማሊ ሰሞኑን መፈንቅለ-መንግስት ያካሄዱት  ወታደራዊ አዛዦች ሩሲያ ውስጥ ሰልጠና መውሰዳቸውን የሚጠቁሙ ዘገባዎች እየወጡ ነው።ባማኮ ዶት ኮም የተባለው የአካባቢው የመገናኛ ብዙሃን እንደዘገበው የሀገሪቱን  ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ቦባካር ኬታ ስልጣን እንዲለቁ ያስገደዱት ወታዳራዊ አመራሮች፤ ከመፈንቅለ መንግስቱ በፊት በሩሲያ ስልጠና ወስደዋል።

ያለፈው ነሐሴ 12  ቀን 2012 ዓ/ም በማሊ የተካሄደውን መፈንቅለ መንግስት ዋና  አቀነባባሪዎች ናቸው የሚባሉት፤ ኮሎኔል ማሊክ ዱያው እና ሳዲዮ ካማራ፤ ሞስኮ  በአንድ ከፍተኛ ወታደራዊ ኮሌጅ ውስጥ የአንድ ዓመት ስልጠና መውሰዳቸውን የአውሮፓ ደህንነት ተቋም አማካሪ ኢማኑኤል ዱፑ ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል።

ሩሲያ ኮለኔል ማሊክ ዱያውን በመስከረም ወር 2019  ዓ/ም  ከማሰልጠኗ ባሻገር  ከአምስቱ የሳህል ሀገራት ጋር  /ሞሪታኒያ፣ ቻድ፣ ቡርኪናፋሶ፣ ኒጀርና ማሊ/   ወታደራዊ ስምምነት ፈርማለችም ብለዋል አማካሪው። 

በጎርጎሪያኑ 2012 ዓ/ም አማዱ ቱማኒ ቱሬ በመፈንቅለ መንግስት  ከስልጣን መወገዳቸውን ተከትሎ በ2013 ዓ/ም ወደ መንበረ መንግስቱ የመጡት ፕሬዚዳንት ኪታ የፈረንሳይ የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ መስርተው ነበር።ከዚህ ጋር ተያይዞ የሰሞኑ መፈንቅለ መንግስት  ፈረንሳይ በምዕራብ አፍሪቃ ሀገራት ያላትን ተፅዕኖና ጠንካራ ይዞታዎች ለመገዳደር  የታቀደ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አሳድሯል። 

በሞስኮ  የምጣኔ ሀብት ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ኢሪና ፊላቶቫ ፤ምንም እንኳ በሩሲያና በማሊ መካከል ወታደራዊ ግንኙነት መኖሩን ባይሸሸጉም ሩሲያ ከመፈንቅለ መንግስቱ ጀርባ አለች የሚለውን መረጃ ግን አይቀበሉትም። 

«ይህ መረጃ ምን ያህል እምነት እንደሚጣልበት ለእኔ አስቸጋሪ ነው ። ምክንያቱም ሞስኮ በጉዳዩ ላይ በይፋ ምንም ያለችው ነገር የለም።በሩሲያ በመገናኛ ብዙሃንም ቢሆን ስለዚህ ጉዳይ ዝርዝር ሲዘገብ አልሰማሁም።»

በሀገሬው ሰው ዘንድ «ኢቢኬ» ተብለው የሚጠሩት ኢብራሂም ቦባካር ኪታ በማሌ ብዙም ተወዳጅ መሪ አይደሉም። ነገር ግን በሳህል አካባቢ ፅንፈኞችን በመዋጋት ረገድ፤ ለምዕራባውያን በተለይም ለፈረንሳይ ጥሩ አጋር ነበሩ።  

የአሜሪካ የአፍሪቃ ኮማንድ በምህፃሩ (AFRICOM) ሞስኮ ሰጠች ከተባለው ስልጠና በተጨማሪ የማሊ ወታደራዊ መሪዎች ከአሜሪካ እና ከጀርመን ስልጠና መውሰዳቸውን ገልጿል።ከዚህ በተጨማሪም ኮሎኔል አሚሲ ጎታ በጀርመን በጆርጅ ሲ ማርሻል የአውሮፓ ማዕከል በሽብርተኝነት እና በደህንነት ጥናት ስልጠና አግኝተዋል።

ወታደራዊ ተቋሙ፤ የመፈንቅለ መንግስቱ መሪ ኮሎኔል አሚሲ ጎታ በአሜሪካ ወታደራዊ ሥልጠና እንዳገኙ ቢገልጽም ነገር ግን በማሊ የተፈጸመው መፈንቅለ- መንግስት በጥብቅ የተወገዘና ከአሜሪካ ወታደራዊ ስልጠና እና ትምህርት ጋር ትስስር የለውም ሲል ከጉዳዩ ራሱን አርቋል። 

የአፍሪኮም የመገናኛ ቅርንጫፍ ሃላፊ የሆኑት ኬሊ ካሃላን እንደሚሉት መፈንቅለ-መንግስቱን ተከትሎ የአሜሪካ ወታደራዊ እርዳታ ተጽዕኖ ያሳድር እንደሁ የአሜሪካ የመከላከያ ክፍል  በማሊ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ እየገመገመ ነው።እኙሁ ሀላፊ አያይዘውም ይህ ግምገማ እስኪጠናቀቅ ድረስ ለማሊ ተጨማሪ ወታደራዊ ስልጠኛ ወይም ድጋፍ እንደማይኖር ገልፀዋል።

ቀደም ሲል ግን የአሜሪካ  ልዩ ኃይል የዘመቻ ክፍል ከ20 ለሚበልጡ የአፍሪካ የጦር አዛዦች የሽብር ቡድኖችን መመከት የሚያስችል የውጭ ሀገር ስልጠና ሰጥቷል ።

መቀመጫዉን አሜሪካ ያደረገው የአፍሪካ የዓለም አቀፍ ስትራቴጂክ ጥናቶች ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት ጁድ ዴቨርሞንት እንደሚሉት የአፍሪቃ ወታደራዊ መኮንኖች የውጭ ሀገር ስልጠናን ለተለዬ ዓላማ ይፈልጉታል።

«ብዙ የአፍሪካ ወታደራዊ መኮንኖች በውጭ አገር ስልጠና የሚወስዱት ጠንካራና በራስ መተማመን ያላቸው መሪዎች ሆነው ለመታየት ነው።ለውጭ  ሥልጠና እንዲመለመሉ የሚያደርጓቸው ብቃቶችም በተመሳሳይ ሁኔታ ውጤታማ የመፈንቅለ መንግስት መሪዎች እንዲሆኑ ያደርጓቸዋል ፡፡» ያምሆኖ ከመፈንቅለ-መንግስቱ ጀርባ ሩሲያ ልትኖር ትችላለች የሚለው ጥርጣሬ ለእርሳቸው ሚዛን የሚደፋ ነው።

የሞስኮዋ ተመራማሪዋ ኢሪና ፊላቶቫ  ግን የሩሲያን ወታደራዊ ድጋፍ ከዚህ ጋር አያያይዙትም ።ይልቁንም የምዕራብ ሀገራትና ቻይና ለአፍሪቃ  የንግድ ዕቃዎችን   እያቀረቡ በመሆኑ፤በወታደራዊ ዘርፉ ሩሲያ  ለአፍሪቃ ድጋፍ መስጠቷ ያላትን ጠንካራ ጎን መጠቀሟን ያሳያል ይላሉ።

«ከወታደራዊ መሣሪያዎች በስተቀር  ከአፍሪካ ጋር የንግድ ልውውጥ ብዙም ጉልህ ስፍራ የሚሰጠው አይደለም። በእርግጥ ሩሲያውያን በማዕድን ሀብቶች  ላይ ፍላጎት አላቸው። ነገር ግን ወታደራዊ ድጋፍ መስጠት ይችላሉ ፡፡ያ ነው የእነሱ ጠንካራ ጎን።»

በማሊ እና በሩሲያ መካከል ያለው ግንኙነት ማሊ ከፈረንሳይ ነፃነቷን ካገኘች ከ1960 ዎቹ  ጀምሮ ነው፡፡ ያምሆኖ የእስቶኮልም ዓለም አቀፍ የሰላም ምርምርና  ጥናት ተቋም  እንደሚያሳየው የሁለቱ ሀገሮች ግንኙነት  ያን ያህል ጠንካራ አይደለም።

 ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በተለይም የምዕራቡ ዓለም በሩሲያ ላይ ማዕቀብ ከጣለባት ከ2014  ዓ/ም ወዲህ  የሩሲያ የአፍሪቃ ተፅኖ እየጨመረ መምጣቱ ይነገራል።ሩሲያ ለአፍሪካ ከፍተኛ ትኩረት የምትሰጥበት አንዱ ምክንያት ከምዕራቡ ዓለም ጋር ለመፎካከር  መሆኑንም የፖለቲካ ተንታኞች ይገልፃሉ።

ከዚህ የተነሳ ከማሌ መፈንቅለ መንግስት ጀርባ ማንም ይኑር ማን አፍሪካ ለሩሲያ እና ለምዕራቡ ዓለም የኃይል ማሳያ መጫወቻ ሜዳ ልትሆን ትችላለች  የሚለው የብዙዎች ስጋት ነው። 

የጀርመን የቅኝ ግዛት ዘመንና የአፍሪቃ የካሳ ጥያቄ

የጀርመን የቅኝ ግዛት ዘመን ከአንድ መቶ ዓመት በፊት ቢያበቃም ጥሎት ያለፈው ጠባሳ ግን አሁንም ድረስ ጀርመንን እንደ ጥላ እየተከተላት ነው። ከጀርመን የቅኝ ግዛት አስተዳደር አንዷ የነበረችው ናሚቢያ ከጎርጎሪያኑ 2015 ዓ/ም ጀምሮ  በዚያን ወቅት በሄሮሮና የናማ ጎሳዎች ላይ በተፈፀው እልቂት ከጀርመን ጋር ድርድር ጀምራለች።ከናምቢያ በተጨማሪ  ታንዛኒያና ቡርድዲም ከአንድ ክፈለ ዘመን በፊት በጀርመን ለተፈፀመው ወንጀል ካሳ ይፈልጋሉ።ታንዛኒያ በቅኝ ግዛት ወቅት «ማጅ ማጅ» የተባለውን ንቅናቄ ለማፈን የተፈፀመውን ጥቃት ወደ ጦር ወንጀልነት እየገፋችው ሲሆን፤ቡሩንዲ በበኩሏ በተለያዩ ወረራዎች በቅኝ ገዥዎች የተፈፀመውን ጥቃት ማንሳት ጀምራለች። 

በሀምቡርግ ዩንቨርሲቲ የአፍሪካ ታሪክ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ዩርገን ሲመር ምንም እንኳ የጀርመን መንግስት በእነዚህ ጥያቄዎች የተደነቀ ቢመስልም ሁኔታዉ ግን የሚጠበቅ ነበር ይላሉ።ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት ይህ ምዕራፍ ለረዥም ጊዜ ምንጣፍ ስር ሊደበቅ  የሚችል አይነት አልነበረም።

እንዲያውም ይላሉ « ሁኔታዉን የምመለከተው እባብን  አትኮሮ የማየት ያህል ነው።» ይላሉ።

«እኔ ያለኝ ስሜት ልክ እባብን አትኮሮ የመመልከት ያህል ነው። አትኩሮ ማየት ግን ለመፍትሄው  መወላወል ይመስላል። በአንድ በኩል ጀርመን ካለፈ ታሪኳ ጋር መስማማትና መርምሮ ፍትህ መስጠት የፌደራል መንግስቱ ይፈልጋል።በሌላ በኩል በአፍሪካ የቅኝ ግዛት ወንጀል ፊት በዝምታ  ቆመዋል። ትክክለኛ መልስ መስጠትም አይፈልጉም ፡፡»

የጀርመን የቅኝ ግዛት አስተዳደር ከጎርጎሪያኑ 1885 እስከ 1919 ዓ/ም የቆየና በአንፃሩ አጭር የሚባል ጊዜ ነበር።ያም ሆኖ ከእንግሊዝና ከፈረንሳይ ቀጥሎ በሶስተኛ ደረጃ የሚቀመጥ በአውሮፓ ትልቁ  የቅኝ ግዛት ሀይል ነበር። የጀርመን ቅኝ ግዛት አስተዳደር  የአሁኗን ናሚቢያ የጀርመን ደቡብ ምዕራብ አፍሪካ በሚል  ፣ የዛሬዎቹን  ታንዛኒያ ፣ ቡሩንዲ እና ሩዋንዳን ደግሞ የጀርመን ምስራቅ አፍሪካ በሚል ያስተዳድር የነበረ ሲሆን ፤የዛሬዎቹን ቶጎ እና ካሜሩንም ግዛቱ ያጠቃልላል።

ምንም እንኳ የጀርመን የቅኝ ግዛት አስተዳደር ጊዜው አጭር ቢሆንም እንደ ፕሮፌሰር ዩርገን ሲመር ግፍ የበዛባቸው አመታት ነበሩ። 

«በእውነቱ እነዚህ መደበኛ የጀርመን 30 የቅኝ ግዛት አመታት በጣም ጭቆና የበዛባቸው ነበሩ።በየትኛውም ቦታ የቅኝ ግዛቶቻቸውን ማሸነፍ ነበረባቸው። ምክንያቱም በየትኛውም ቦታ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ነበሩ።በጀርመን በኩል እነዚህ እንቅስቃሴዎች በጭካኔ  ይታፈኑ ነበር ።ይህ ተጨባጭ ነው።»

 የታሪክ ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት እጅግ ደም አፋሳሽ የነበረው አመፅ  በምስራቅ አፍሪካ በጎርጎሪያኑ  ከ1905 እስከ 1907 ዓ/ም «ማጂ ማጂ» የተባለው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ሲሆን፤ ይህንን አመፅ ለማፈን በምስራቅ አፍሪቃ 300,000 ያህል ሰዎች ተገድለዋል።ሌላው ከ1904 እስከ 1908  ዓ/ም በደቡብ ምዕራብ አፍሪካ የነበረው የሄሬሮ እና የናማ ጎሳዎች አመጽ ሲሆን ፤80,000 ሰዎች የሞቱበትና በ20 ኛው ክ/ዘመን የመጀመርያው የዘር ማጥፋት ወንጀል የተፈፀመበት መሆኑ ይነገራል፡፡ 

ጀርመን በቅኝ ግዛት ወቅት የተፈፀሙ ወንጀሎችን በተመለከተ ከዓምስት አመታት በላይ ከናሚቢያ ጋር በመደራደር ላይ ትግኛለች።ሆኖም ግን ድርድሩ እስካሁን ውጤት አላመጣም።ምክንያቱ ደግሞ በሄሬሮና በናማ ጎሳዎች የተፈፀመው ወንጀል ይቅርታ ብቻ ሳይሆን ካሳም ይፈልጋል የሚለው ሁለቱን ሀገሮች አላስማማቸውም ።ላላፉት አምስት አመታት ከናሚቢያ ጋር በሚደረገው ውይይት የጀርመን መንግስት ልዩ ተወካይ የሆኑት ሩፐርት ፖለንዝ ፤ጀርመን ከ1904 እስከ1908 በናምቢያ ለተፈፀሙ ወንጀሎች የፖለቲካና የሞራል ሀላፊነቷን መወጣት ትፈልጋለች።ነገር ግን በፌደራል መንግስቱ ዕይታ ጉዳዩ የህግ ጉዳይ አይደለም ይላሉ።

« በፍርድ ቤት ብዙ ጊዜ የሄሬሮና የናማ ክስ በተመሰረተበት ወቅት ተገልጿል።የህግ ጥያቄ ሳይሆን ይህ የሞራልና የፖለቲካ ጥያቄ ነው።እናም ከዚህ በመነሳት የፌደራል መንግስቱ የምንመርጠው  ይህንን የሚገልፁ ፅሁፎች እና መግለጫዎችን እንጂ ጠባብ አገላለፅ ያላቸውን ሕጋዊ ውሎች አይደለም።ጀርመን ለነዚያ ወንጀሎች ከነገ ይልቅ ዛሬ ይቅርታ መጠየቅ ትፈልጋለች።»

የናሚቢያን ድርድር ተከትሎ ቡሩንዲም ከቀድሞዎቹ ቅኝ ገዥዎቿ ከጀርመንና ከቤልጄም 30 ቢሊዮን ዩሮ ካሳ ለመጠየቅ እየተዘጋጀች ነው።ታንዛኒያም  በወቅቱ በምስራቅ አፍሪቃ ለተፈፀመው የጦር ወንጀል ጀርመን ሀላፊነት እንድትወስድ ግፊት እያደረገች ነው።

የቡሩንዲው የታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር አሎይስ ባቱንግ የቡሩንዲ ካሳ መጠየቅ  ፍትሃዊ ነው ይላሉ። እንደ ታሪክ ተመራማሪው ከአንድ መቶ ዓመት በፊት የነበረው የቅኝ ግዛት ፖሊሲ በቡሩንዲ  ያስከተለውን ተፅዕኖ ቀላል ባለመሆኑ ጀርመን ይህንን በጥልቀት መመርመርና ለወደፊቱም መፍትሄ መፈለግ ለሁለቱ ሀገራት አስፈላጊ ነው። 

ከዚህ በተጨማሪ የታንዛኒያ መንግስት በቅኝ ግዛት ወቅት ተወስደው በጀርመን ቤተ-መዘክሮች ውስጥ የሚገኙትን በርካታ ቅርሶች ለማስመለስም ውይይት ጀምሯል።ቅርሶቹ የሰው ቅሪት አካሎችና ባህላዊ ቁሳቁሶችን የሚያጠቃልል ሲሆን አብዛኛዎቹ በማጅ ማጅ ጦርነት የተካፈሉ አፍሪቃውያን ንብረት መሆኑንም መረጃዎች ያሳያሉ።

ፀሐይ ጫኔ

እሸቴ በቀለ