1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከህወሓት ነፃ የሆኑ የአማራ ክልል አካባቢዎች መደበኛ እንቅስቃሴ ጀመሩ

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 11 2014

ህወሓት ይዟቸው በነበሩና አሁን ነፃ በሆኑ የአማራ ክልል አካባቢዎች መደበኛ እንቅስቃሴዎች እየተጀመሩ መሆናቸውን የየአካባቢዎቹ ነዋሪዎችና ባለስልጣናት ተናገሩ፣ በትራንስፖርት በኩል ህገወጥ የታሪፍ ጭማሪ ግን ነዋሪዎቹን እያማረረ ነው፡፡

https://p.dw.com/p/44ZkM
Äthiopien | Bürgerkrieg | Tigray | Dessie
ምስል Maria Gerth-Niculescu/DW

የህወሓት ኃይሎች በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ወረራ በፈፀሙበት ወቅት የግልና የመንግሰት ተቋማት መዘረፋቸውን፣ መውደማቸውንና እንዲበላሹ መደረጋቸውን የአማራ ክልል መንግስት በተለያዩ ጊዜዎች ገልጧል፡፡ 
ሰሞኖኑ በርካታ የክልሉ አካባቢዎች ነፃ መሆናቸውን ተከትሎ የተለያዩ ከተሞች ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ እየተመለሱ እንደሆኑ ነዋሪዎቹ እየተናገሩ ነው፡፡ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የሸዋ ሮቢት ከተማ ነዋሪ ለዶይቼ ቬለ በስልክ እንደገልፁት ንግድ ባንኮችና ሌሎችም ቢሮዎች ተከፍተው አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡ 
በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር የከሚሴ ከተማ ነዋሪ በበኩላቸው፣ የገበያ እንቅስቃሴ የተጀመረ ሲሆን ቢሮዎችም ለስራ አመቺ እየሆኑ ነው ብለዋል፡፡ 
የደሴ ከተማ ነዋሪው የእርሳቸው ቢሮ ሙሉ በሙሉ በመውደሙ ሥራ መጀመር ባይችሉም በደሴ ከተማ የመንግስት ሰራተኞች ወደ ቢሮ እየገቡ እንደሆነ አረጋግጠዋል፡፡  በኮምቦልቻ ከተማም ግማሽ በግማሽ የሚሆኑ መስሪያ ቤቶች ሥራ እየጀመሩ ቢሆንም ትምህርት ቤቶች ግን ስራ እንዳልጀመሩ አንድ የከተማዋ ነዋሪ ገልፀዋል:: የትራንስፖርት አገልግሎት በብዙ አካባቢዎች ቢጀምርም ክፍያው ግን ከመደበኛ ታሪፉ በብዙ እጥፍ እንደጨመረባቸው ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡ 
በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ጀማል ሁሴን በከሚሴ ከተማ የመንግስት ስራ መጀመሩን፣ ትምህርት ቤቶች መከፈታቸው አመለክክተዋል፡፡ የትራንስፖረት ታሪፍን በተመለከተ የችግሩን ምንጭ ጠቅሰው መፍትሔ እየተፈለገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም የደቡብ ወሎ ዞን ሥራ አስኪያጅ አቶ እሸቱ ስርዎ መንግስት ዛሬ መስሪያ ቤታቸው ሥራ መጀመራቸውን ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል፡፡ 


ዓለምነው መኮንን


ልደት አበበ
ኂሩት መለሰ