1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተቃውሞው ወደ ነውጥ ተቀይሮ ለ81 ሰዎች ሞት እና ለንብረት ውድመት ምክንያት ኾኗል

ረቡዕ፣ ሰኔ 24 2012

ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ሞት በኋላ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ከተሞች ተቃውሞው ወደ ነውጥ ተቀይሮ ለ81 ሰዎች ሞት እና ለንብረት ውድመት ምክንያት መሆኑን የኦሮሚያ ክልል መንግስት አስታወቋል። የክልሉ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ለዶይቸ ቬለ በተለይ እንዳለው በክልሉ አምቦ እና ባሌ አካባቢዎች የሰዎች ሕይወት አልፏል። በርካቶች ቆስለዋል።

https://p.dw.com/p/3eeju
Äthiopien Unruhen in Shashemene
ምስል Privat

በኦሮሚያ ክልል በተቀሰቀሰው ነውጥ ከሰማንያ በላይ ሰዎች መገደላቸውን የክልሉ መንግሥት አስታወቀ

ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ሞት በኋላ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ከተሞች ተቃውሞው ወደ ነውጥ ተቀይሮ ለ81 ሰዎች ሞት እና ለንብረት ውድመት ምክንያት መሆኑን የኦሮሚያ ክልል መንግስት አስታወቋል። የክልሉ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ለዶይቸ ቬለ በተለይ እንዳለው በክልሉ አምቦ እና ባሌ አካባቢዎች የሰዎች ሕይወት አልፏል። በርካቶች ቆስለዋል። ዛሬ በአምቦ ከተማ በአርቲስቱ ቤተሰቦች መኖርያ አካባቢ አንድ የአርቲስቱን የስጋ ዘመድ ጨምሮ አምስት ሰዎች መገደላቸውን የአይን እማኝ ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል።ከትናንት ወዲያ ሰኞ ምሽት አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ በተሽከርካሪው ውስጥ እንዳለ በተቶከሰበት ጥይት መገደሉ ከተነገረ ወዲህ መዲናዋ አዲስ አበባን ጨምሮ በኦሮሚያ ክልል አብዛኛው አካባቢዎች ውጥረት መንገሱም እየታየ ነው ።  ከትናንት ሰኞ ማለዳ ጀምሮ መዲናይቱ አዲስ አበባን ጨምሮ በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ ከተሞች ለተቃውሞ የወጡ ሰዎች እርስ በእርስ እና ከመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ጋር ተጋጭተው ከ50 በላይ ሰዎች መሞታቸውን የክልሉ የኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ ተናግረዋል። የአርቲስቱን ሞት ተከትሎ «የራሳቸውን ፍላጎት ለማሳካት የሚፈልጉ ኃይሎች ሁከት እንዲቀሰቀስ ማድረጋቸው የሰው ሕይወት መጥፋትም ሆነ ለንብረት መውደም ምክንያት ሆኗል » ይላሉ አቶ ጌታቸው።እንደ አቶ ጌታቸው የአርቲስቱ ሞት ሁሉንም የማሳዘኑን ያህል «የብሔር እና የኃይማኖት መልክ እንዲኖረው የፈለጉ ሰዎች ግጭቱ መልኩን እንዲቀይር አድርገዋል» ሲሉ ይከሳሉ።በኦሮሚያ ክልል ከትናንት ጀምሮ የሕይወት እና የንብረት ጥፋት ያስከተለው ተቃውሞው እየተባባሰ በመሄዱ መንግስት የጸጥታ ኃይሎችን ለማሰማራት መገደዱን አቶ ጌታቸው ተናግረዋል። በዚህም  በአርቲስቱ የትውልድ ስፍራ በአምቦ ከተማ እና በባሌ ሮቤ ለጊዜው ቁጥራቸው ያልተገለጸ ሰዎች መገደላቸውን እና የንብረት ውድመት መድረሱን አቶ ጌታቸው ይናገራሉ።የአምቦ ከተማ  ነዋሪ የሆነው ወጣት ወቢ እንደሚለው ከሆነ ግን በአምቦ ከተማ ዛሬ የተፈጠረው ግጭት የከተማዋ ወጣቶች የአርቲስቱ የቀብር ስፍራ አዲስ አበባ መሆን አለበት የሚል ከፍተኛ ፍላጎት በመፈጠሩ እና ይኸንኑ ተከትሎ  የጸጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ አምስት ሰዎች መገደላቸውን በአይኑ ማየቱን ነግሮናል። በአርቲስቱ ወላጆች መኖርያ ቤት አካባቢ ከተገደሉት ሰዎች ውስጥ የአርቲስቱ የስጋ ዘመድ እና ጓደኛ እንደሚገኙበትም ገልጿል።የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ የቀብር ስፍራ አምቦ እንዲሆን የተወሰነው  «በአርቲስቱ ቤተሰቦች ፍላጎት ብቻ» መሆኑን የክልሉ የኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ ይናገራሉ። «መንግስት የአርቲስቱን ቤተሰቦች ፍላጎት መሰረት በማድረግ በጀግና አሸናኘት ቀብሩን ከማስፈጸም ውጭ ቦታውን የመወሰን መብት የለውም »ሲሉም ያክላሉ።የአምቦ ከተማ ነዋሪ እና ለአርቲስቱ ቤተሰቦች ቅርበት ያለው ወጣት ወቢ ግን መንግስት የቀብሩ ስፍራ አምቦ እንዲሆን ያደረገው የአርቲስቱን «ቤተሰቦች በማስፈራራት »ሳይሆን እንዳልቀረ  ይናገራል። የከተማዋ ወጣቶች አርቲስቱ አሁንም ድረስ አዲስ አበባ እንዲቀበር ፍላጎት እንዳላቸው ገልጿል።የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ የቀብር ስነስረዓት ነገ በአምቦ ከተማ እንደሚፈጸም የክልሉ መንግሥት አስታውቋል። 
ታምራት ዲንሳ
ኂሩት መለሰ