1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከ17ኛው ዓለም አቀፍ የበይነ-መረብ አስተዳደር ጉባኤ ኢትዮጵያ ምን አተረፈች?

ረቡዕ፣ ኅዳር 28 2015

ኢትዮጵያ ሰሞኑን 17ኛውን የዓለም አቀፍ የበይነ-መረብ አስተዳደር ጉባኤ በመዲናዋ አዲስ አበባ አስተናግዳለች።«የማይበገር በይነ-መረብ ለዘላቂ እና የጋራ የወደፊተ ጊዜ» በሚል መሪ ቃል የተካሄደው ይህ ጉባኤ፤የበይነ-መረብ ተደራሽነት 30 በመቶ ለሆነባት ኢትዮጵያ ጠቀሜታ ይኖረው ይሆን?

https://p.dw.com/p/4Kbmt
Äthiopien Addis Abeba | IGF Ethiopia 2022
ምስል Ethiopian Ministry of Innovation and Technology

ጉባኤው ኢትዮጵያ ለጀመረችው የዲጅታል ጉዞ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት

 
ኢትዮጵያ ሰሞኑን 17ኛውን የዓለም አቀፍ የበይነ-መረብ አስተዳደር ጉባኤ በመዲናዋ አዲስ አበባ አስተናግዳለች።የኢንተርኔት ተደራሽነት ከ30 በመቶ ባታች በሆነባት ኢትዮጵያ ይህ ጉባኤ መካሄዱ የተደራሽነት ችግርን ከመፍታት አንፃር ምን ጠቀሜታ አለው? የዛሬው የሳይንስና ቴክኖሎጅ ትኩረት ነው።
17ኛው ዓለም አቀፍ የበይነ-መረብ አስተዳደር ጉባኤ ከኀዳር 19 ቀን 2015 ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ  ቀናት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።በጉባኤው  የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች፣ የተለያዩ ሀገራት ሚኒስትሮች፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ እና የቴክኖሎጅ ባለሙያዎችን  ጨምሮ  ከ4 ሺሕ  በላይ ተሳታፊዎች መገኜታቸውን የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጅ  ሚንስቴር መረጃ ያመለክታል።
«የማይበገር ኢንተርኔት ለዘላቂ እና  የጋራ የወደፊተ ጊዜ» በሚል መሪ ቃል በኢትዮጵያ አዘጋጅነት ባለፈው ሳምንት የተካሄደው ይህ ጉባኤ  ከኢንተርኔት ዕድሎች እና ተግዳሮቶች ጋር በተያያዙ በርካታ ጉዳዮች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል። 

Äthiopien Addis Abeba | IGF Ethiopia 2022
17ኛው የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ ምስል Ethiopian Ministry of Innovation and Technology

በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የዲጅታል ትራንስፎርሜሽን ሀላፊ የሆኑት ዶክተር አብዮት ባዬ እንደሚሉት ጉባኤው በኢትዮጵያ መካሄዱ  ሀገሪቱ ለጀመረችው የዲጅታል ጉዞ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት።
«በኢትዮጵያ መካሄዱ አንደኛ የጉባኤው አጀንዳ በዋናነት በታዳጊ ሀገራት ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩር ትልቅ ዕድል ከፍቷል።ሌላው ለእኛም የዲጅታል ትራንስፎርሜሽን መንገድ እንደጀመረ ሀገር ከሌሎች ገሀሮች ብዙ ልምዶች ለማየት ችለናል።በዚህ ፎረሙ የሚሳተፉ በኢንተርኔትም ሆነ በዲጅታል ትራንስፎርሜሽን ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱ በሂደት ላይ ያሉም ይገኛሉ እና ከሁሉም ብዙ ልምዶች አግኝተናል።»ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት የዓለምን የኢኮኖሚ እድገት እና የሰዎችን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ የተቀላጠፈ ለማድረግ  የበይነመረብ ተደራሽነት ቁልፍ ሚና ይጫወታል።ያም ሆኖ  የበይነ-መረብ ተደራሽነት በኢትዮጵያ ዝቅተኛ በመሆኑ ከዚያ የሚገኘውን ትሩፋት ሙሉ በሙሉ መጠቀም አልቻለችም።
በመሆኑም ኢትዮጵያ እንደ ሌሎቹ ሀገራት በበይነመረብ ኢኮኖሚን የማሳደግ  እድል ቢኖራትም፤ በመላ ሀገሪቱ ያለው የበይነመረብ ተደራሽነት ክፍተት ያለበት እና እኩልነት የጎደለው እንዲሁም በዋጋ ደረጃ በጣም ውድ ነው። ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሀገሪቱ ህዝብ በተለይም በገጠሩ የሀገሪቱ ክፍል ከበይነመረብ  አገልግሎት  ሙሉ በሙሉ የተገለለ ነው።
በቅርብ የወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በኢትዮጵያ የበይነመረብ ተጠቃሚ ቁጥር ከ19 ወደ 30 ሚሊዮን ከፍ ብሏል። ሆኖም ግን 120 ሚሊዮን ሰዎች ለሚኖሩባት ኢትዮጵያ በቂ አይደለም።ይህንን ችግር ዶክተር አቢወትም ይጋሩታል።ነገር ግን ችግሩን  ለመፍታት በመንግስት በኩል የተለያዩ የመፍትሄ ርምጃዎች ተወስደዋል ይላሉ። 
«የኢንተርኔት ተደራሽነት 30 ሚሊዮን ደርሷል። ነገር ግን ለ120 ሚሊዮን አነደተባለው ህዝብ ዝቅተኛ ነው።በመጀመሪያ ኢንተርኔትን ለማዳረስ መንግስት የወሰደው የፖሊሲ እርምጃ የቴሌኮም ገበያውን «ሊቨራላይዝ» ማድረግ እና ተጨማሪ ኦፕሬተሮች ወደ ገበያው እንዲቀላቀሉ እና ዘርፉን በገበያ እንዲመራ ማድረግ ነው።ሌላው በዚህ በዲጅታል ትራንስፎርሜሽን ስርታቴጅ የያዝነው መሰረተ ልማቱን ማዳረስ ብቻ ሳይሆን ትርጉም ያለው ተደራሽነት ማድረግ ነው። ትርጉም ያለው ተደራሽነት ማለት መሰረተ ልማቱ ደርሶ ሰዎች የማይጠቀሙት ከሆነ ምናልባት ውድ ስለሆነ ሊሆን ይችላል ወይም ችሎታው ላይኖራቸው ይችላል።እነዚህን ችግሮች መፍታት ካልተቻለ ትርጉም ያለው ተደራሽነት አይኖርም።ኢንተርኔት በገበያ እየተመራም ቢሆን «አፎርዴብል» የሚሆንበትን የፖሊዚ መንገድ ማዘጋጄት።»ካሉ በኃላ ለተጠቃሚው የሚመጥን ይዘት ማዘጋጄትም ሌላው ስራ መሆኑን ገልፀዋል።

Abyiot Baye | Leiter Abteilung für digitale Transformation im Ministerium für Innovation und Technologie
ዶከተር አብዮት ባዬ በኢኖቬሽን አና ቴክኖሎጅ ሚነሰቴር የዲጅታል ትራንስፎርሜሽን ሃላፊ ምስል Privat

መረጃዎች እንደሚያሳዩት ኢትዮጵያውያን በአብዛኛው የበይነመረብ አገልግሎት የሚያገኙ  ከተንቀሳቃሽ ስልክ  ነው።ምንም እንኳ ዘመናዊው የአምስተኛው ትውልድ የበይነመረብ  ትስስር ወይም 5ጂ በአንዳንድ አካባቢዎች መጀመሩ አየተነገረ ቢሆንም፤ አሁንም ቁጥሩ ቀላል የማይባል ህዝብ  2ጂ ወይም ሁለተኛው ትውልድ የሚባለውን ደካማ የበይነመረብ ግንኙነት ይጠቀማል።በርካታ ህዝብ ደግሞ በሰከንድ እስከ 2 ሜጋ ባይት ግንኙነቶችን በሚያቀርበው 3ጂ በተባለው የተንቀሳቃሽ ስልክ ግንኙነት ክልል ውስጥ ይገኛል። በአዲስ አበባ ከሚኖሩ ከ10 ሰዎች አንዱ ደግሞ 4ጂ የበይነመረብ ግንኙነት ያገኛል። ከዚህም በተጨማሪ ባለፉት 5 ዓመታት ውስጥ በመላ ሀገሪቱ ቢያንስ 17 የተመዘገቡ ከፊል እና አጠቃላይ የበይነ መረብ መዘጋት ታይቷል። ባለፉት ሁለት አመታት ጦርነት በተካሄደባቸው የትግራይ፣ ከፊል አማራ እና የአፋር አካባቢዎች ደግሞ አገልግሎቱ ተቋርጦ ቆይቷል። 
መረጃን በመቆጣጠር እና ግላዊነትን በመጠበቅ፣ ደህንነትን እና ተጠያቂነትን ማስፈን፣ በኢንተርኔት ግንኙነት የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ፣ የተራቀቁ የቴክኖሎጂዎች ውጤቶችን ተደራሽነትን ማስፉት እና የኢንተርኔት መከፋፈልን (fragmentation) ማስቀረት የሚሉ ሀሳቦች በተነሱበት በዚህ ጉባኤ ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገሮች ምን ተሞክሮ ወሰደች። በበይነመረብ ተደራሽነትስ ከሌሎች ሀገራት አንፃር የት ደረጃ ላይ ትገኛለች? ዶክተር አብዮት ባዬ።
«እንግዲህ ኢትዮጵያ ባለፉት ሶስት አመታት በጣም ከፍተኛ የሆነ ለውጥ አሳይታለች።«የማርኬት ስትራክቸሩንም» በመቀየርም  ሆነ የሚያስፈልጉ የህግ እና የስራ ሁኔታዎችን በማስተካከልም  ሆነ አሁን ያለውን የኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎት አማካኝነት አመርቂ ውጤቶች ተገኝተዋል,። 30 ሚሊዮን ማለት ቀላል ቁጥር አይደለም። ተሰርተዋል።ነገር ግን ከህዝቡ ብዛት አንፃር አሁንም ብዙ ስራዎች የሚጠበቅባት እና በአንፃራዊነት ቢያንስ በፐርሰንት ወደ ኋላ የቀረን መሆኑን እሱን ለማየት ችለናል። በዚህ አይነት ሁኔታ የነበሩ አንዳንድ ሀገሮች ደግሞ በተለይ የማርኬት ስትራክቸሩን በምን ሁኔታ እንዴት እንደቀየሩ ልምድ አግኝተናል።»በማለት ከጉባኤው የተገኘውን ልምድ ገልፀዋል።

Äthiopien Addis Abeba | IGF Ethiopia 2022
17ኛውን የዓለም አቀፍ የበይነ-መረብ አስተዳደር ጉባኤ በአዲስ አበባ ኢትዮጵያ ምስል Ethiopian Ministry of Innovation and Technology

ከዚህ በተጨማሪ በዲጂታላይዜሽን፣ በግል ዴታ ጥበቃ እና ከበይነ-መረብ ግንኙነት ውጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን የማገናኘት እና በሌሎችም የትብብር ዘርፎች ላይ የጉባኤው ተሳታፊ ከሆኑ የተለያዩ ዓለም አቀፍ አጋር አካላት ጋር ውይይት መደረጉንም ተናግረዋል። በመሆኑም ከጉባኤው የተገኘውን ልምድ እና የዓለም አቀፍ አጋሮችን ትብብር  እንደ ግብዓት በመጠቀም፤ ባለፉት ሁለት አመታት የበይነመረብ ግንኙነት  የተቋረጠባቸውን የትግራይ አካባቢዎች በተፋላሚ ወገኖች መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ አገልግሎቱን መልሶ ለመጀመር  የሚደረገውን ስራ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚቻል አመልክተዋል። ከረዥም ጊዜ ግብ አኳያ ደግሞ እስካሁን አገልግሎት ውጭ ሆኖ የቆየውን የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ለማድረግ ያስችላል። 
በሀገሪቱ ዲጅታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጅ  አካታች የዲጅታል ኢኮኖሚ መገንባት  መሰረት ያደረገ መሆኑን የገለፁት ሃላፊው፤አካታችነት ደግሞ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ሲጠቀምበት በመሆኑ፤ በተለይ በገጠር የሚገኘውን የህብረተሰብ ክፍል የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ የተለያዩ ስራዎች እንደሚሰሩ ገልፀዋል። 
«የመንግስት ትልቁ ትኩረት ምንድነው በሁሉም አካባቢ እንዲዳረስ ነው።አሁን ባለንበት ሁኔታ ከ65 በመቶ በላይ በሆኑ አካባቢዎች የ3ጂ ሽፋን አለ።የሞባይል ተጠቃሚ ቁጥር ወደ 68 ሚሊዮን ድርሷል።»ካሉ በኋላ የበይነ መረብ አገልግሎት በዚሁ ቁጥር ላይ የሚጨመር መሆኑን አመልክተዋል።
በሌላ በኩል የዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት ሀገሪቱ «ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025»የሚል ሀገራዊ ስልት ነድፋ በጎርጎሪያኑ ሰኔ መጨረሻ 2022 ዓ/ም  ወደ ስራ ገብታለች። ይሁን እንጅ የበይነመረብ አገልግሎት በቅጡ ባልተዳረሰባት  እና ባለፉት ሁለት አመታት አውዳሚ ጦርነት ባካሄደችው ኢትዮጵያ ይህ ዕቅድ ስኬታማነቱ ምን ያህል ነው?ለዶክተር አቢወት ባዬ ያቀርብንላቸው ጥያቄ ነበር። 
«የዲጅታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጅ ዕቅዱን ወደ መሬት ለማውረድ ከመሰረተልማት አንፃር የሚሰሩ ናቸው።ሁለተኛው አስቻይ ስርዓት መዘርጋት ነው።እነዚህ አስቻይ ስርዓቶች ደግሞ እንደ ዲጅታል መታወቂያ፣ የዲጅታል የክፍያ ስርዓት እና የሳይበር ደህንነት ስራዎችንም ያጠቃልላል።የዲጅታል መታወቂያው ተጀምሯል።እስከ 2025 አብዛኛው ህብረተሰብ እንዲኖረው ይደረጋል።»በሌላ በኩል የዲጅታል ክፍያን በተመለከተ በርካታ የህግ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን ገልፀው፤ ለአብነትም እንደ ቴሌ ብር ያሉ የዲጅታል ክፍያ ስርዓቶችን ጠቅሰዋል። 
የዲጅታል ኢትዮጵያ 2025 ዋና ግቡ ለዲጅታል ኢኮኖሚው የመሰረተ ልማቶችን መገንባት እና አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር ነው የሚሉት ሃላፊው፤ ከዚህ አንፃር ድርሻ ያላቸው አካላት አቅም ኑሯቸው እንዲሳተፉ ለማድረግ በተለይም  ትምህርት ቤት ላይ ያሉ ወጣቶች የዲጅታል እውቀት እንዲኖራቸው ለማድረግ የስርዓተ ትምህርት ማሻሻያ መደረጉን አመልክተዋል። ከህግ እና ቁጥጥር አንፃርም የኮሚንኬሽን ህግ፣፣የኤለክትሮኒክ ትራንዛክሽን ህግ ወጥቶ ስራ ላይ መሆኑን ገልፀዋል። የግል መረጃ ጥበቃ እና ጀማሪ ኩባንያዎችን የሚመለከት ህግም በሂደት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።ከዚህ አንፃር የዲጅታል ኢትዮጵያ 2025 ዕቅድ ይሳካል የሚል ተስፋ እንዳላችው ገልፀዋል ። 


ፀሀይ ጫኔ 
አዜብ ታደሰ