1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከ10ኛዉ ክፍለ ዘመን የጀመረዉ የብሪታንያ ንጉሳዊ ሥርዓት

ሐሙስ፣ ግንቦት 3 2015

የብሪታንያ ንጉሳዊ ቤተሰብ በጭራሽ ፖለቲካ ዉስጥ አይገባም። ዘዉድ የሃገሪቱ ባህል የአንድነትና የሃገሪቱ የህልዉና ምልክት ነዉ። ሥነ-ስርዓቱ በጣም አስደሳች ነበር። በታላቅዋ ብሪታንያ ይህ የንጉሳዉያን አስተዳደር ባይኖር ኖሮ፤ ምናልባትም ስኮትላንድ፤ ዌልዝ፤ እንዲሁም ሰሜናዊ አየርላንድ ከብሪታንያ ዉስጥ ከብዙ ዓመታት በፊት በወጡ ነበር።

https://p.dw.com/p/4RD4O
BdTD London Krönung von König Charles und Königin Camilla
ምስል LEON NEAL/AFP

የ 800 ዓመት ታሪክን ዛሬም እንደቀድሞዉ ሲከበር ማየት ያስደስታል

«የብሪታንያ ንጉሳዊ ቤተሰብ በጭራሽ ፖለቲካ ዉስጥ አይገባም፤ የሃገሪቱ ባህል የአንድነት እና የሃገሪቱ የህልዉና ምልክት ነዉ። ይቅርታ ይደረግልኝና በታላቅዋ ብሪታንያ ይህ የንጉሳዉያን አስተዳደር ባይኖር ኖሮ፤ ስኮትላንድ፤ ዌልዝ፤ እንዲሁም ሰሜናዊ አየርላንድ ከብሪታንያ ዉስጥ ከብዙ ዓመታት በፊት በወጡ ነበር። ይዞ ያስቀመጣቸዉ ለዘዉድ ያላቸዉ አስተሳሰብ ነዉ።»  የታሪክ ምሁሩ ልዑል ዶ/ር አስፋ ወሰን በብሪታንያ ባለፈዉ ቅዳሜ የተካሄደዉን የንግሥና ሥነ ስርዓት በተመለከተ ከተናገሩት የተወሰደ ነዉ።

London | Krönung König Charles III.
የታላቅዋ ብሪታንያ ንጉሥ ቻርለስ ሣልሳዊ እና ባለቤታቸው ንግሥት ካሚላ የንግሥና ሥነ-ስርዓት በለንደንምስል Andrew Matthews/AP/picture alliance

ሚያዝያ 28 ቀን 2015 ዓም የታላቅዋ ብሪታንያ ንጉሥ ቻርለስ ሣልሳዊ እና ባለቤታቸው ንግሥት ካሚላ ዘዉድ የደፉበት የንግሥና ሥነ-ስርዓት በለንደን ዌስትሚኒስተር አቤ በደማቅ ሥነ-ስርዓት ተካሂዷል። ዘዉድ በመጫን ሥነ-ስርዓቱ ላይ ከሁለት ሺህ በላይ ሰው ታድሟል። ሌሎች ብሪታንያዉያን ብሎም ከተለያዩ የአዉሮጳ ሃገራትን  ጨምሮ የዓለም ሃገራት የተሰባሰቡ በ 10 ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ጥንዶቹን ለማየት በለንደን ጎዳናዎች ላይ ተሰልፈዉ የታሪኩ ተካፋይ ለመሆን በዝናባማዉ እለት ቆመዉ ይከታተሉ ነበር። በዚህ ዝግጅት ላይ ከ 22 የተለያዩ ዓለም ሃገራት የመጡ ፎቶግራፍ አንሽዎች ፊልም ቀራጮች፤ ፀሐፍትን ጨምሮ ወደ ስድስት ሺህ ጋዜጠኞች ተገኝተዋል። „ንጉሴ አይደለህም“ ያሉ  ጥቄት ሰዎች ደግሞ መፈክራቸዉን እያሰሙ በንግስናዉ ሥነ-ስርዓት ነገሥት አደባባይ ላይ መፈክር ይዘዉ ሲቃወሙም ታይተዋል።

Großbritannien London | Krönung Charles III. | Menschenmenge
በለንደን ህዝብ የታላቅዋ ብሪታንያ ንጉሥ ቻርለስ ሣልሳዊ እና ባለቤታቸው ንግሥት ካሚላ የንግሥና ሲያከብር ምስል Bruce Adams/AP Photo/picture alliance

በጀርመን ሃገር ባሳተሟቸዉ አምስት ስድስት መጻሕፍቶች ከፍተኛ እዉቅናን ያገኙት እና በጀርመን የአፍሪቃ እና የመካከለኛዉ ምስራቅ ጉዳዮች አማካሪ እንዲሁም የታሪክ ምሁሩ ልዑል ዶ/ር አስፋ ወሰን አስራተ፤ እንደነገሩን የእንግሊዝ የዘዉድ ሥነ-ስርዓት ባህላዊ ፤ ቀጣይነት ያለዉ የብሪታንያ ህዝብ አክብሮ የሚጠብቀዉ የሚወደዉ ባህሉ እና እሴቱ ነዉ። እንደ ልዑል አሳፋ ወሰን ባለንበት በ 21ኛዉ ክፍለ ዘመን ታላቅዋ ብሪታንያ ላይ የታየዉ የዘዉድ ሥነ-ስርዓት ሃገሪቱን ብቻ ሳትሆን አዉሮጳዉያንን ያስደሰተ ታሪካዊ  ሥነ-ስርዓት ነበር።

«ብሪታንያ ላይ የተካሄደዉ የዘዉድ ሥነ-ስርዓት ነዉ በጣም አስደሳች ነበር። አንድ ሃገር ከ800 ዓመታት በላይ ያለዉን ባህል በ 21ኛዉ ክፍለ ዘመን እንዲህ ሲያከበር ማየቱ በጣም ያስደስታል። አንድ የታወቀ የእንጊሊዝ የታሪክ ተመራማሪ ስለ እንጊሊዝ ነገስታት ጉዳይ እንደተናገረዉ„እንጊሊዝ ሃገር በዘዉድ የምትገዛ ሪፓብሊክ ናት“ ብሏል። ይህ ልክ ነዉ ። በአንድ በኩል ዴሞክራሲ የሚታይበት በሌላ በኩል የዘዉድ ስርዓትም በመኖሩ ነዉ። ሃገሪቱ ከተመሰረተችበት እና ዘዉድ የሚባል ነገር ከመጣ በኋላ በብሪታንያ ዉስጥ አንድ ጊዜ ብቻ አብዮት ተካሂዷል። ይህ አብዮት የተካሄደዉ በ 1641 ዓ.ም ነበር። የመጀመርያዉን ንጉስ አብዮት አካሂደዉ አንገቱን ቆረጡ። ከዝያን በኋላ ለጥቂት ግዚያት ክሮምዌል የሚባል አምባገነን አገሪቱን ገዛ። ከዝያዉ በኋላ የመጀመርያዉ ንጉስ ቻርልስ ልጅ፤ ቻርልስ ዳግማዊ ከነበረበት ከፈረንሳይ ሲመለስ ብሪታንያዉያን ዘዉድ እና መንግሥት መለየት እንዳለበት ገባቸዉ። ቻርልስ ከሞተ በኋላ ሜሪ የሚባሉ ሁለት ነገስታት ወደ ሃገሪቱ ሲመጡ ትልቁ አብዮት „The Glorious Revolution“ በሚል ዘዉድ እና መንግሥት የሚለይ ለዉጥ ያለ ደም መፋሰስ ስራ ላይ መዋል ጀመረ። የአዉሮጳዉያን ነገስታት ሁሉ ሲጠፉ እንጊሊዝ ይህን ህግ ተግባራዊ በማድረግዋ የዘዉድ ስርዓት እስከዛሬ ሊቀጥል ችሏል። እርግጥ ነዉ በአዉሮጳም ቢሆን ከአራት የበለጡ ንጉሳዉያን ያሉባቸዉ ሃገራት ይገኛሉ። ይሁንና ልክ እንደ እንጊሊዙ ባህሉን አስቀጥለዉ የመጡ አይደሉም።»       

London | Anti-Monarchie-Demonstranten bei der Krönungsprozession
ንጉሴ አይደለህም ያሉ ተቃዋሚዎች በንጉሥ ቻርለስ ሣልሳዊ እና ባለቤታቸው ንግሥት ካሚላ የንግሥና እለት ያሳዩት ተቃዉሞ ምስል Piroschka van de Wouw/AP/picture alliance
London Krönung König Charles
የታላቅዋ ብሪታንያ ንጉሥ ቻርለስ ሣልሳዊ እና ባለቤታቸው ንግሥት ካሚላ የንግሥና ሥነ-ስርዓት በለንደንምስል GARETH CATTERMOLE/AFP

የሚገርመዉ የዘዉድ መድፋቱ ሥነ-ስርዓት የንጉሥ ቻርለስ ሣልሳዊ ብቻ ሳይሆን ባለቤታቸው የንግሥት ካሚላም አክሊል ተጭኖላቸዋል ። ንግሥት ተብለዋል። የቀድሞ ባለቤት ልዕልት ዲያና በመኪና አደጋ ከሞቱ በኋላ፤ ካሚላ የዚያንግዜዉ ልዑል ድብቅ ፍቅረኛ ስለነበሩ፤ ልዕልት ዲያና ከሞተች በኋላ ካሚላ የልዑል ቻርልስ ጓደና ከዝያም ሚስት ሆነዉ በይፋ ሲወጡ ህዝብ እንትፍ ብሎ ጠልቷቸዉ ነበር። ይኸዉ ዛሬ ትዳር ይዘዉ ለንግሥና ዘዉድ ለመድፋትም በቁ።

BdTD Spanien Benidorm Britische Touristen bei Krönung König Charles
በለንደን ህዝብ የታላቅዋ ብሪታንያ ንጉሥ ቻርለስ ሣልሳዊ እና ባለቤታቸው ንግሥት ካሚላ የንግሥና ሲያከብር ምስል EVA MANEZ/REUTERS

« በእርግጥ ነዉ የብሪታንያን ንጉሳዉያን ቤተሰብን ታሪክ የማያዉቁ ናቸዉ ስለ ንግሥት ካሚላ ያልሆነ ነገር የሚያስቡት። ንጉሥ ቻርለስ ሣልሳዊ ከልጅነታቸዉ ጀምሮ ይወድዋቸዉ ያፈቅሯቸዉ የነበሩት የአሁንዋን ባለቤታቸዉን ንግሥታ ካሚላን ነበር። ልዕልት ዳያናን ያገቡት ተገደዉ መሆኑን መርሳት የለብንም። ምክንያቱም የዝያን ጊዜዉ ልዑል ቻርልስ አልጋ ወራሽ እንደመሆናቸዉ መጠን፤ ልጅ መዉለድ አለባቸዉ፤ ካሚላ መጀመርያ ቻርልስን ለማግባት ያደረጉት ጥረት ባለመሳካቱ አግብታ ልጆች ወልዳለች። የዝያን ጊዜዉ ልዑል ቻርልስም ካሚላን ላግባ ብለዉ ተከልክለዉ ነበር። ትልቁ ስህተት የተሰራዉ እዚህ ላይ ነዉ። በፍቅር የወደዳትን ካሚላን ከመጀመርያዉ ቢያገባ ኖሮ ይህ ሁሉ መከራ ዉስጥ ባልተገባ ነበር። የፈጣሪ ፈቃድ ሆነና መጀመርያ ላይ ሳይሆን ቀረ ዳያናም በሚያሳዝን ሁኔታ ህይወትዋ አለፈ። ለማንኛዉም ሁለት ልጆች አትርፋለታለች።  በመጨረሻ ካሚላን አግብቶ ዛሬ ለንግሥትነት በቅታለች። ንግሥት ካሚላ ባሳዩት ጠባይና ክብር ዛሬ በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትን አግኝታለች።»

BdTD Vanuatu Dorfbewohner mit Porträt vom britischen König Charles
በደቡብ ፓሲፊክ ላይ የሚገኘዉ በቫኑቱ ሪፓብሊክ ገጠር ንግሥናዉን ሲያከብሩ ምስል BEN BOHANE/AFP

የዲያናን ሞት ተከትሎ ለዓመታት ህዝብ የንጉሣዉያኑ ቤት መግብያ ላይ የሃዘን መግለጫ ይጽፍ ነበር አበባ ያስቀምጥ ነበር ። ህዝብ ከሚችፈዉ እና ንጉሳዉያኑ መኖርና ቤት ደጃፍ ላይ ከሚያስቀምጠዉ ጽሑፍ መካከል የዛሬዋን ንግሥት ካሚላን በጣም የሚያንቋሽሽ ጽሁፍ ነበር።   

እንደዉ በ 21ኛዉ ክፍለ ዘመን በዚህ ለኢንተርኔት ትዉልድ የወርቅ ሰረገላ፤ የወርቅ ካባ መልበሱ ፤ንጉሰ ቅባት መቀባቱ የፀሎት ሥነ-ስርዓቱ ወዲህ ወድያዉ ይገባዋል ይላሉ?

«በደንብ። እርግጥ ነዉ፤ ለንደን ጎዳናዎች ላይ ይህን የዘዉድ ሥነ ስርዓት ለመከታተል ከተሰበሰበዉ ከ 200 ሺህ ከሚጠጋ ህዝብ መካከል 100 እና 50 ሰዎች ንጉሡን አንቀበልም ብለዉ ለተቃዉሞ ወጥተዉ ነበር። ነገር ግን ዘዉድ ግን የእያንዳንዱ እንጊሊዛዉ ባህሉ እና ማንነቱ ነዉ።»

Großbritannien London | Krönung Charles III. | Buckingham Palace
የታላቅዋ ብሪታንያ ንጉሥ ቻርለስ ሣልሳዊ እና ባለቤታቸው ንግሥት ካሚላ የንግሥና ሥነ-ስርዓት በለንደንምስል Leon Neal/AP Photo/picture alliance

ዶ/ር ልዑል አስፋ ወሰን አስራተ እንደተናገሩት ንጉስ ቻርልስ ሳልሳዊ በገቡት ቃለ-ማህላ መሰረት ከማንኛውም ፖለቲካዊ ውግንና ገለልተኛ ናቸው። ንጉሱ የብሪታንያ ምልክት ተደርገው ይወሰዳሉ፤ በታላቅዋ ብሪታንያ ህግን በማጽደቅ ብቸኛው ሰውም ናቸው። ንጉስ ቻርልስ ሳልሳዊ ከዚህ በተጨማሪ  የብሪታንያን መሪ ሹመትን ያፀድቃሉ፤ የሀገሪቱን ምክር ቤት በመክፈት የዓመት እቅዶችንም ያጸድቃሉ። ንጉሱ በብሪታንያ የቀውስ ጊዜ ከተከሰተ እና መንግስቱ ያንን መቆጣጠር ካቃተው አዲስ መንግስት እንዲመሰረት የማድረግ ስልጣንም አላቸው። ንጉሱ የእንግሊዝ ቤተክርስቲያን የበላይ ገዢም በመሆናቸዉ ጳጳሳትን እና የቤተክርስቲያን አገልጋዮችን የመሾም ስልጣን አላቸው።

ከዚህ በተጨማሪ ንጉሱ የቀድሞ የእንግሊዝ ቀኝ ግዛት የነበሩ ሃገራትን ጨምሮ በዓለማችን ላይ የሚገኙ የ 15 ሉዓላዊ ሀገራት ርዕሰ ብሄር ናቸው።

Großbritannien Krönungskonzert Windsor Castle
በለንደን የታላቅዋ ብሪታንያ ንጉሥ ቻርለስ ሣልሳዊ እና ባለቤታቸው ንግሥት ካሚላ የንግሥናን በተመለከተ የተዘጋጀ የሙዚቃ መድረክ ምስል Leon Neal/AP Photo/picture alliance

የቀድሞ የእንግሊዝ ቀኝ ግዛት የነበሩ ሲሆን፤ ከቀኝ ግዛት ከተላቀቁ በኋላም ግን ሀገራቱ የብሪታኒያ ንጉሳውያንን በሀገራቸው ርእሰ ብሄር አድረገው ሾመዋል።

የብሪታኒያ ንጉስ ርእሰ ብሄር የሆኑባቸው 15 ሀገራት የትኞቹ ናቸው። ጃማይካን ጨምሮ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተለያዩ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ሃገሮች የብሪታኒያ ንጉሳውያንን ከሀገራቸው ርዕሰ ብሔርነት የማንሳት እንቅስቃሴ መጀመራቸዉ ይታወቃል። ባለፈዉ ዓመት ህዳር ወር ደቡብ አሜሪካዊቷ ሀገር ባርቤዶስ  የብሪታኒያ ንጉሳዊነት አልፈልግም ብላ ከርዕሰ ብሔርነት በማንሳት ሪፐብሊክ ሆኛለሁ ስትል ማወጅዋ የሚታወስ ነዉ።

Großbritannien Krönungskonzert Windsor Castle
ንጉሥ ቻርለስ ሣልሳዊ እና ባለቤታቸው ንግሥት ካሚላ ከንግሥና ሥነ ስርዓቱ በኋላ በተካሄደዉ የሙዚቃ ድግስ ላይ ምስል Chris Jackson/AP Photo/picture alliance

ልዑል አስፋ ወሰን ይህን የታላቅዋ ብሪታንያን የዘዉድ ንግሥና ክብረ በዓልን ኢትዮጵያ ከነበረዉ ጋር ማወዳደር ይቻላል? ለሚለዉ ጥያቄ ሰፋ ያለ መልስ ሰጥተዉናል።

የዘወትር ተባባርያችንን ዶ/ር ልዑል አስፋ ወሰን አስራተን ለሰጡን ቃለ-ምልልስ በዶቼ ቬለ ስም በማመስገን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።  

አዜብ ታደሰ

ሸዋዩ ለገሠ