1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከኦሮሚያ ክልል ተፈናቅለው አማራ ክልል የተጠለሉ ቀያቸው እንዲመለሱ ግፊት መኖሩን ተናገሩ

ሐሙስ፣ ኅዳር 13 2016

ከኦሮሚያ ክልል ተፈናቅለው በአማራ ክልል የተጠለሉ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ግፊት መሆኑን ተናገሩ። ተመለሱ የተባሉት ሁለቱ ክልሎች ተፈናቃዮችን ለመመለስ “ሥምምነት ፈጥረዋል” በመባሉ ነው። ተፈናቃዮቹ ለመመለስ የጸጥታ ሥጋት አለባቸው። እርዳታ የሚሰጣቸው ሲመለሱ መሆኑ እንደተገለጸላቸው የሚናገሩት ተፈናቃዮች ለችግር መዳረጋቸውን አቤት ይላሉ ።

https://p.dw.com/p/4ZMps
ከኦሮሚያ ተፈናቅለው በአማራ ክልል የተጠለሉ
ከኦሮሚያ ተፈናቅለው በአማራ ክልል የተጠለሉ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ግፊት እየተደረገባቸው መሆኑን ተናገሩ።ምስል Privat

ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ግፊት እየተደረገባቸው መሆኑን ተናገሩ

ከኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ጃርደጋ ጃርቴ ወረዳ በ2013 ባጋጠመው የጸጥታ ችግር ተፈናቅለው ወደ ደቡብ ወሎ በማቅናት የተፈናቃዮች መጠለያ ውስጥ መቆየታቸውን አንስተው አስተያየታቸውን የሰጡን አንድ ተፈናቃይ የሁለቱ ክልሎች አመራሮች ተፈናቃዮች ወደ ቀዬያቸው እንዲመለሱ በመስማማታቸው ግፊት እየተደረገ ነው ይላሉ።  

“አሁን የምንገኝበትን ኑሮ ብለን አይደለም። እኛም መልሱን ብለን ነበር። ግን አሁን በዚያ ያለውን የሰላም አየር ስናይ በዚያ የቀሩ ወገኖቻችንም የምቸገሩበት ነው። ትምህርት የለ ህክምና የለም፡፡ በዚህ ሁኔታ የክልል መንግስታቱ ስለተስማሙ ብቻ ወደ ቦታችሁ ተመለሱ የሚል ደረሰን” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

 ከኦሮሚያ ክልል ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬያቸው ለመመለስ ውይይት

ከዚያው ከምዕራብ ኦሮሚያ ተፈናቅለው በተፈናቃዮች ካምፕ የተጠለሉት ሌላ ግለሰብ “ተገደን የመመለስ እድል እንዳለን ተነግሮናል” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ግፊት እየተደረገ እንደሆነ አረጋግጠዋል። “ማንነት ላይ ባተኮረ ጥቃት ተፈናቅለን መጣን” ያሉት አስተያየት ሰጪ አሁንም ቢሆን በዚያ የቀሩት መልካም ሊባል የማይችል የተረጋጋ ጸጥታ ውስጥ ባሉበት ወደዚያው እንዲንመለስ የሚደረግ ግፊት ተቀባነት የሌለው ነው ሲሉም በአስተያየታቸው ይሞግታሉ።

 

የተፈናቃዮች መጠለያ
ከኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉ ዜጎች በአማራ ክልል ተጠልለው ይገኛሉምስል Privat

ተፈናቃዮቹ ወደ ቀድሞ ቀዬያቸው እንዲመለሱ የላላው የእርዳታ አቅርቦት

ተፈናቃዮቹ እንደሚሉት ቀደም ሲል የሚቀርብላቸው እርዳታም ወደ ቀድሞው ቀዬያቸው እንዲመለሱና ወደዚው እንደተዘዋወረላቸው እንደተነገራቸውም ያስረዳሉ። ይህ ደግሞ አሁን ባሉበት መጠለያ እንኳ ዋስትና እንዳይሰማቸው ማድረጉንም ያነሳሉ። 

“ምግብ በዚያው ታገኛላችሁ በሚል አሁን ከስድስት ወራት ወዲህ ቀለብ ላልቶብናል” ያት ተፈናቃዮቹ ያለ ምግብ ለረጅም ጊዜ ለመቆየት እየተገደዱ መሆናቸውንም ነው በአስተያየታቸው ያነሱልን፡፡ ተፈናቃዮቹ አክለውም ከምግብ አቅርቦት መቀዛቀዝ ጋር ተደቅኖብናል ያሉት የመራብ ስጋት የጸጥታ ስጋቱ ባላስተማመነበት ወደ ቀደመ ቀዬያችሁ ተመለሱን መባሉ ሰቀቀን ሆኖብናል ነው ያሉን። 

በተፈናቃዮች ላይ የሚደርሱ የሰብዓዊ መብቶችት ጥሰቶች

በኦሮሚያ ተፋላሚዎች መካከል ያልሰመረው የሰላም ድርድር ያጠላው ስጋት

ተፈናቃዮቹ ከጸጥታ ስጋቱ ጋር ተያይዞ በሰጡት ተጨማሪ አስተያየታቸው፤ ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስት እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር - የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነግ-ኦነሰ) ብሎ ከሚጠራው የታጠቀ ሸማቂ ቡድን ጋር በታንዛንያ ያደረገው የሰላም ስምምነት ጥረት አለመሳካቱ ሌላው ስጋት እንደሆነባቸውም ያስረዳሉ፡፡

“በዚህች ሳምንት ብቻ በሆሮጉዱሩ ወለጋ ዞን ፍንጫ ወረዳ በታጣቂዎች እና የመንግስት ፀጥታ ኃይሎች መካከል ቀከታታይ ሶስት ቀን የፈጀ ውጊያ ተደርጓል፡፡ ተፋላሚዎቹ ከሰሞኑ ድርድር ላይ ናቸው መባሉ ተስፋን አሰንቆን የነበረ ቢሆንም አሁን ግን ሁለቱ መፋረሳቸው የመመለሱን ሃሳብ በስጋት እንድናየው አድርጎናል” ሲሉ አንድ ተፈናቃይ ተናግረዋል።

 በመንግስት እና የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት የሰላም ድርድር የተፈናቃዮች ተስፋ

በቅርቡ ባህርዳር ከተማ ውስጥ የኦሮሚያ እና አማራ ክልል የጸጥታ አስተዳደር ኃላፊዎችን ጨምሮ የሁለቱ ክልሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት የታደሙበት ውይይት ተደርጎ ተፈናቃዮችን ወደ ነባር ቀዬያቸው የመመለስ ስምምነት ላይ መደረሱን ባለስልጣናቱንም ጭምር ዋቢ አድርጎ ዶቼ ቬለ መዘገቡ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የስደተኞች፣ አገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና ፍልሰተኞች ጉዳይ ኃላፊ እጉዳይ መስቀሌ
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የስደተኞች፣ አገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና ፍልሰተኞች ጉዳይ ኃላፊ እጉዳይ መስቀሌ “ቀድሞ ተፈናቃዮችን ያፈናቀላቸው መሰረታዊው መንስኤ ተቀርፏል ወይ?” የሚለው ጥያቄ መልስ ማግኘት እንደሚገባው ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋልምስል Seyoum Getu/DW

ይህ ውጥን በምን አይነት መንገድ ተግባራዊ ሊደረግ ነው በሚልና ስለ ተፈናቃዮቹ ስጋት ምላሽ ለማግኘት ለሁለቱም ክልሎች የአደጋ ስጋት እና ኮሚዩኒኬሽብ ቢሮ ኃላፊዎች ለመጠየቅ ያደረግነው ጥረት አልሰመረም። 

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የስደተኞች፣ አገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና ፍልሰተኞች ጉዳይ ኃላፊ እጉዳይ መስቀሌ በሰጡን አስተያየት ግን ባሁን ወቅት ኮሚሽኑ ምልከታ ባደረገባቸው አከባቢዎች ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬያቸው ለመመለስ የሚያስችል ሁኔታ አልተስተዋለም፡፡

“እኛ ለመንግስት የምናሳስበው፤ ታሳቢ መደረግ ያለባቸው ቀድሞ ተፈናቃዮችን ያፈናቀላቸው መሰረታዊው መንስኤ ተቀርፏል ወይ ነው፡፡ ተፈናቃዮችን ስንመልስ ፈቃደኝነታቸውና ኑሯቸውን የሚመሩበት ነገር መሟላት ተገቢ ነው” ያሉት ኃላፊዋ ኮሚሽኑ ምልከታ ባደረገባቸው አከባቢዎች አስፈላጊው ነገር አልተስተዋለም። 

ሥዩም ጌቱ 
እሸቴ በቀለ
ዮሐንስ ገብረእግዚዓብሔር