1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እየሩሳሌም ነጋሽ፤ ሴቶችን ለማብቃት እየተጋች ያለች ወጣት

እሑድ፣ ጥር 8 2014

በእንቛ ታብራ ድርጅት ሴቶችን ለማብቃት ጥረቷን እየቀጠለች ያለች ወጣት እየሩሳሌም ቀደም ሲልም የብሔራዊ ቡድንና የቡና ክለብ ተጫዋችና አሰልጣኝ ነበረች

https://p.dw.com/p/45TsZ
Äthiopien Äthiopische Fußballnationalspielerin Eyerusalem Negash
ምስል Eyerusalem Negash

ሴት በመሆኔ ኳስን ለመጫወት ብዙ ፈተናዎችን አይቻለሁ


``ሴት በዛ ጎመን ጠነዛ``፣ ``ሴትና አህያ ዱላ ...``፣ ``በሴት ቢጀመር በውንድ ያልቅ``፣ ብዙ ብዙ ማኅበረሰቡ የሚጠቀማቸው እና የሴቶችን ክብር ዝቅ የሚያደርጉ አባባሎችን መጥቀስ ይቻላል። ይህን አባባልና አደናቃፊ ተግባር በጥረቷ ሰብራ ቀደም ሲል በእግር ኳስ ሜዳ አሁን ደግሞ በአእምሮ መዋቅር ግንባታ ሜዳ ውስጥ ሆና እየታገለች ያለች ወጣት የመዝናኛ እንግዳችን አድርገናታል። እየሩሳለም ነጋሽን። ከእግር ኳስ ሕይወትና ሴቶችን የማብቃት ልምዷን ታካፍለናለች።

መቼስ ልጅ ሆኖ ኳስን ሳይለጋ ያደገ አይኖርም። የያኔዋ ህጻን እዮሩሳሌም ተወልዳ ያደገችው አዲስ አበባ ቂርቆስ ለገሃር አካባቢ  ነው። በአካባቢዋ በምትገኘው ትንሿ ሜዳ ኳስ ተጫውተው ለክለቦች እንዲያም ሲል ለብሔራዊ ቡድን የደረሱ ጠንካራ ተጫዋቾች የፈለቁባት ናት። እየሩሳሌም በዚያች መንደር ማደጓ በእግር ኳስ የስኬት ማማ ላይ እንድትቀመጥ እንደገፋፉት ትናገራለች።

ወደ እግር ኳስ ሜዳ ጠጋ ብላ ታላላቅ ወንዶች ሲጫወቱ ወደ ውጭ የወጣን ኳስ በማቀበል የተጀመረው የኳስ ፍቅር በህጻናት የእግር ኳስ ስልጠና ወደ መታቀፍ አደረሳት።

Äthiopien Äthiopische Fußballnationalspielerin Eyerusalem Negash
ምስል Eyerusalem Negash

ጀምራው በዋዛ  ላትመለስ  ውጤት ላይ ሳትደርስ ላለመለየት ከእግር ኳስ ጋ ተጋምዳለች ህጻኗ እየሩሳሌም። በእልህ የጀመረችው እግር ኳስ በኋላ ላስመዝገበችው ውጤት እንደ የይቻላል ማንጠሪያ የሆናት አንድ አጋጣሚን ታስታውሳለች። ነገሩ እንዲህ ነው። የ11 አመት ህጻን እያለች እንደልማዷ ኳስ ለመጫወት ወደ መስቀል አደባባይ ታመራለች። በመሃል ወደ ውጭ የወጣችን ኳስ ለማምጣት ስትሄድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የሚለብሰውን ቱታ ለብሰው የሚሮጡ ትልልቅ ሰዎችን ተመለከተች። ቆም ብላ እነሱን በመመልከት ውስጧ የሆነ ነገር ሲፍጠር እንደተሰማትና ይህን መለያ ለብሳ አገርን ወክላ ለመጫወት አንዳች ስሜት እንዳደረባት አጫውታናለች ።

የህችን አጋጣሚ ለአሁን የስኬቷን የመስረት ድንጋይ ያኖረችባት እንደሆንች በኩራት እምትገልጸው እየሩሳሌም ለመጀመሪያ ጊዜ በቡና ስፖርት ክለብ ታቅፋ ቡድኑን ለድል ካበቁት ተጠቃሽ የክለቡ አባላት አንዷ ለመሆን በቅታለች።
በ1994 ለብሔራዊ ቡድን የተመረጠቸው እየሩሳሌም የብሔራዊ ቡድኑ አስልጣኝ በመሆንም ጭምር እንዳገለገለች ታስታውሳለች። በተከላካይ መስመር የምትጫወተው እየሩሳሌም ክለቦችዋን ለውጤት ማብቃቷን ትገልጻለች። 
እየሩሳሌም ከቡና ክለብ እስከ ብሔራዊ ቡድን በነበራት የስኬት ማማ ላይ ለመቀመጥ ብዙ ለፍታለች። ብዙ ታግላለች። ምናልባትም ለየት የሚያደርገው የሕብረተሰቡ ለሴቶች ያለውን ዝቅተኛ አመለካከት ለመስበር ተፈጥሮአዊ ጾታዋን እረስታ የሄደችው ርቀት እጅግ አስገራሚ ነው። ወንድን ለመምሰል ጸጉሯን ተቆርጣለች። ርምጃዋን የወንድ ለማስመሰል ተገዳለች። ባጠቃላይ የወንድ ገጸባሕሪ ተላብሳ እንድትኖር ተገዳ እንደነበር ታስታውሰዋለች።

እልህኝነትና ላሰቡት ግብ ማንኛወም መስዋእት መክፈል መመሪያዋ ያደረገቸው እየሩሳሌም ለስኬት እንደ ማንጠርያ የተጠቀምችበት ወንድን የመምሰል ሂደት ጫማዋን ሰቅላ የትዳር ሕይወት መሰርታ በሌላ የትግልና የስኬት መድረክ ብቅ ስትል ይህ ሁኔታን ለማስተካከል ሌላ ፈተና ሆኖባት ነበር።

Äthiopien Äthiopische Fußballnationalspielerin Eyerusalem Negash
ምስል Eyerusalem Negash

በራሷ ደርሶባትና በሌሎች ሴት እህቶቿ ሲደርስ ያየችውን በሕብረተሰቡ ላይ ያለው ጎጂ ልማዳዊ አስተሳሰብ ጫማዋ ከሰቀለች በኋላ ሌላ የትግልና የስኬት ሜዳዋ እንደሚሆን ላፍታም አልተጠራጠረችም። በምሆኑም ``እንቋ ታብራ`` የሚል ለትርፍ ያልቆም መንግስታዊ ያልሆነ ድርጀት በመመስረትና በዋና ሥራ አስኪያጅነት በመምራት በሌላ ሴቶችን የማብቃት ሜዳ ብቅ ብላለች።
በዚህ ድርጅት በርካታ ሴቶች የማህበረሰቡን ጫና ተቛቁመው ለስኬት እንዲበቁ የአእምሮ ውቅር የማስተካከል መድረኮችን በማዘጋጀት ለለውጥ እየተጋች ትገኛለች። የተቸገሩትን በመርዳት ጭምር።

በእንቋ ታብራ ወንዶችም ታዳሚዎች ናቸው። ሴት ልጅ ብረት መዝጊያ እንድታመጣ ሳይሆን እራሷም ብረት መዝጋት እንደምትችል አውቃ እንድታድግ የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ በርካታ መድረኮችን አዘጋጅታለች። ታድያ ይህን የተቀደሰ ሃሳብን እምትደግፉ እጃችሁ ከምን ተብላችሃል።


ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር 


ማንተጋፍቶት ስለሺ