እንወያይ፤ የትግራይ ክልል ቀዉስ ወዴት እያመራ ነዉ? መፍትሔዉስ?
እሑድ፣ ሰኔ 28 2018
እንወያይ፤ ትግራይ ክልል ቀዉስ ወዴት እያመራ ነዉ?
መፍትሄዉ ምንድን ነዉ?
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግሥት እና በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ መካከል የሚደረገዉ ዉዝግብ እና ቁርቁስ አሁንም እንደቀጠለ ነዉ። ህወሓት በፕሪቶርያ ስምምነት መሰረት የተሰየመዉን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር፤ባለፈዉ ሚያዝያ ወር ከተቆጣጠረ ወዲህ ከአዲስ አበባዉ መንግሥት ጋር የነበረዉ ቂም እየተካረረ መምጣቱ እየተነገረ ነዉ። በቅርቡ ደግሞ ህወሓት የክልሉን ወጣቶች በግዳጅ ለወታደርነት እየመለመለ መሆኑ ሲዘገብ፤ አዲስ ያወጣዉ ደንብ ደግሞ ፤ ጦርነት ሊቀሰቅስ ይችላል ወደሚል ጭንቀት የክልሉን ህዝብ እያስገባ ነዉ። በፌደራል መንግሥት በኩልም ህወሓት ከኤርትራ እና ከሌሎች የአገር ዉስጥ ታጣቂዎች ጋር በመተባበር ኢትዮጵያ ዉስጥ የተደረገዉን ምርጫ ጭምር ለማወክ እና ሰላምን ለማደፍረስ እየተንቀሳቀሰ ነዉ የሚለዉ ወቀሳ በተደጋጋሚ ይሰማል። የኢትዮጵያ መንግሥትን እና ህወሓትን፤ ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም የግጭት የማቆም ስምምነት ደቡብ አፍሪቃ ፕሪቶርያ ከተማ ላይ ያስማማዉ የአፍሪቃ ህብረት የአደራዳሪዎች ቡድን መሪ የቀድሞዉ የናይጀርያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴንጎ ኦባሳንጆ አዲስ የሰላም ጥረት መጀመራቸዉ ቢነገርም ተጨባጭ ዉጤት ግን እስካሁን አልታየም። የኢትዮጵያ መንግሥት እና ህወሓት መሰረታዊ ችግራቸዉ ምንድን ነዉ?
-በሰሜን ኢትዮጵያ በተለም ከትግራይ ክልል የሚወጡ የተለያዩ ዜናዎች ነዉ የምንሰማዉ። ህወሓት፤ ከተለያዩ ታጣቂ ቡድኖች ጋር መደራጀቱ ፤ ወጣቶችን በግዳጅ ለዉትድር እና መመልመሉ፤ በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መንግሥት ቦታዉ ላይ ከአንድ ቦታ ጦር ሰራዊቱን እያንቀሳቀሰ ነዉ መባሉ፤ አልያም የድሮን ጥቃት አድርሷል፤ የጦርጀት ቅኝት እያደረገ ነዉ፤ የመሳሰሉ ወሪዎች ይሰማሉ።በትግራይ ክልል በተጨባጭ ምንድን ነዉ ያለዉ፤ ምንስ እየሰማችሁ ያላችሁት?
-በህወሓት እና በፌዴራሉ መንግስት መካከል የተፈጠረው ውጥረት መርገብ ባላሳየበት ወቅት አሜሪካ እና የአውሮጳ ህብረት በህወሓት ላይ የተከተሉት የዕቀባ እና ማስጠንቀቂያ አዘል መግለጫዎች በወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታ ላይ የሚያሳድረዉ አንድምታ ምንደነው ይላሉ?
-ህወሓት ከፌዴራሉ መንግስት የመደራደር ሁኔታ ቢፈጠር እንኳ በሦስተኛ ሀገር ካልሆነ በቀር እንዳማይሳተፍ ግልጽ አድርጓል፤ ይህ የህወሓት አቋም የመደራደር ተስፋን ያሟጥጣል ወይስ ጋባዥ ነዉ ትላላችሁ? የኢትዮጵያ መንግሥት እና የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ጠብ ወዴት ያመራ ይሆን?
በዚህ ዉይይት ላይ ሃሳባቸዉን እንዲሰጡ የተጋበዙት፤
1,አቶ መብርሂ ብርሃኔ ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች ኢትዮጵያ የተባለዉ ድርጅት ምክትል ዳይሬክተር
2, አቶ አወል ልጅ አለም - በትግራይ ክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያገለገሉ፤ የህግ ባለሙያ
3,አቶ ደያሞ ዳሌ - የፖለቲካ ተንታኝ - እንዲሁም
4, አምዶም ገብረስላሴ -- የትግራይ ለዴሞክራሲና ሉዓላዊነት መድረክ ሊቀመንበር ናቸዉ።
ሙሉዉን ዉይይት የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።