1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እንወያይ፤ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ቀዉስና የምዕራባዉያን ጫና

እሑድ፣ ነሐሴ 16 2013

በዲፕሎማሲዉ በሰብዓዊ እርዳታና፤ በሌሎች መስኮችም በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ምዕራባዉያን የሚያደርጉት ጫና ተጠናክሯል።የአሜሪካ የአፍሪቃ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማንን የመሳሰሉ ዲፕሎማቶች አዲስ አበባን ቢጎበኙም እስካሁን ድረስ ጦርነቱን ለማስቆምም ሆነ፤ ኢትዮጵያ ከምዕራባዉያን ጋር የገጠመችዉን የዲፕሎማሲ ዉዝግብ ለማስወገድ አልጠቀመም።

https://p.dw.com/p/3zKhP
Der Tigray-Krieg und die Herausforderungen der Diplomatie
ምስል Azeb Tadesse/DW

በተለያዩ ድክመቶች የሚተቸው የኢትዮጵያን ዓለምአቀፍ ግንኙነት እንዴት ማጠናከር ይቻላል ?

የትግራዩ ጦርነት ለኢትዮጵያ በዉግያዉ ግንባር ካደረሰው የሰብዓዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ቀዉስ በተጨማሪ የዲፕሎማሲ ዉጣ ዉረድ አስከትሎአል። በጦርነቱ ምክንያት ለኢትዮጵያ መንግሥት ለወትሮ ከፍተኛ ድጋፍ ይሰጡ ከነበሩት እና ጥብቅ ወይም ጠንካራ ግንኙነት ካላቸዉ ዩናይትድ ስቴትስን ከመሳሰሉ፤ ምዕራባዉያን ሃገራት ጋር የነበረዉ ግንኙነት በእጅጉ ሻክሮአል። ዩናይትድ ስቴትስ በኢትዮጵያ መንግሥት ባለስልጣናት ላይ የጉዞ ማዕቀብ ከመጣልዋም በላይ፤ ለኢትዮጵያ የምትሰጠዉን እርዳታም ቀንሳለች። ከአንድ ሳምንት በፊት እንደሰማነዉ ደግሞ፤ ፈረንሳይ ከኢትዮጵያ ጋር ወታደራዊ ስምምነት ሰርዛለች። በዲፕሎማሲዉ በሰብዓዊ እርዳታና፤ በሌሎች መስኮችም በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ምዕራባዉያን የሚያደርጉት ግፊት እና ጫና ተጠናክሯል። የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪቃ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማንን የመሳሰሉ ዲፕሎማቶች አዲስ አበባን ቢጎበኙም እስካሁን ድረስ ጦርነቱን ለማስቆምም ሆነ፤ ኢትዮጵያ ከምዕራባዉያን ጋር የገጠመችዉን የዲፕሎማሲ ዉዝግብ ለማስወገድ፤ የጠቀመዉ ነገር የለም። በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚ/ር ዐቢይ አህመድ በቱርክ የተሳካ ያሉትን ጉብኝት አድርገዉ ተመልሰዋል። ኢትዮጵያ እና ቱርክም በወታደራዊ ሳይንስ ዘርፍ የፋይናንስ ድጋፍ ትብብር የሁለትዮሽ ስምምነት መፈራረማቸዉ ተገልፆአል። ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ የትግራይ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ በዓለም የጦርና የፖለቲካ መድረክ ላቅ ያለ ተሰሚነት ያላትን ሃገር፤ በዚህ ሳምንት ሲጎበኙ የመጀመርያቸዉ ነዉ።     

የኢትዮጵያ መንግሥት ፤ ደጋፊዎቹ እና መገናኛ ዘዴዎቹ ምዕራባዉያን መንግሥታት ለሚያደርጉት ጫና፤ የኢትዮጵያ መንግሥት በአሸባሪነት የፈረጀውን ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት)ን ወደ ስልጣን ለማምጣት ካላቸዉ ፍላጎት የመነጨ ነዉ በማለት ይወቅሳሉ። ይሁን እና ገለልተኛ የሚባሉ ወገኖች፣ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫናዉ የበዛዉ ጦርነቱንም ሆነ በአጠቃላይ የሃገሪቱን ፖለቲካዊ ሁኔታ ለመምራት መንግሥት በቂ አቅም ብስለት እና ከሁሉም በላይ ዲፕሎማሲ ስለሌለዉ ነዉ ብለዉ ይከራከራሉ። የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ምን ደረጃ ላይ ነዉ ያለዉ? ከዚህስ በኋላ ምን መደረግ አለበት በሚሉ ነጥቦች ላይ የዛሬዉ ዉይይታችን ያተኩራል።

ለዚህ ዉይይት የጋበዝናቸው አቶ ፍፁም አረጋ በዩናይትድ ስቴትስ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ፣ዶክተር ዳርእስከዳር ታየ የፖለቲካ ሳይንስ የውጭ ግንኙነት እና ዲፕሎማሲ ጉዳዮች ምሁር፤ አቶ አክሊሉ ታደሰ በብልፅግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት የወጣቶች ሊግ ፕሬዚዳንት፤ እንዲሁም አቶ ክፍሉ ሁሴን የኢትዮጵያን የፖለቲካ ጉዳይ በቅርበት የሚከታተሉ የሕግ ባለሞያ ናቸዉ። እንግዶቻችን ጥሪአችንን አክብረዉ በውይይቱ ሃሳባችሁን ለማካፈል ፈቃደኛ በመሆናችሁ በዶቼቬለ ራድዮ ስም አናመሰግናለን። 

ሙሉ ዉይይቱን የድምጽ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ!

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ