1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እንወያይ፤ ከአዲሱ መንግሥት ምን እንጠብቅ ?

እሑድ፣ መስከረም 23 2014

የአዲሱ መንግስት ተግዳሮቶች በርክታዎች ናቸው የሚሉ ጥቂቶች አይደሉም። መቋጫ ባጣው ጦርነት ውስጥ ሆነን፤ የትግራይ ቀዉስ፤ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ሞትና መፈናቀሎች በሚታይበት፤ የሕገ-መንግስት ማሻሻያ ባልተደረገበት፤ የአገሪቱ ኢኮኖሚ መንገራገጭ ውስጥ በገባበት፤ የሚመሰረተው መንግሥት ምን ያህል ተስፋ ያለው ስራ ያከናውናል ?

https://p.dw.com/p/41C6E
 Äthiopien Neuer Ministerpräsident Abiy Ahmed Ali Kombobild AM

የአዲሱ መንግሥት ተስፋና ተግዳሮቶች ምንድን ናቸዉ ይላሉ?

በኢትዮጵያ ምርጫ  መንግስት ለመመስረት የሚያስፈገውን (410) አብላጫ ድምፅ ያገኘው የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ ብልጽግና ፓርቲ፤ ሰኞ መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ መንግሥት ይመሰርታል። ከእስከዛሬው የኢትዮጵያ ምርጫ ነፃ ነበር፤ የተባለዉን 6ኛዉ ሃገራዊ ምርጫ ያሸነፈዉ የብልፅግና ፓርቲ፤መንግሥት ሲመሰረት፤ የኢትዮጵያን የፖለቲካ መድረክ ለሦስት አስርተ ዓመታት ተቆጣጥሮት የነበረዉ የኢሕአዴግ ዘመን በይፋ ማብቃቱ የሚታወጅበት ነዉም ተብሎለታል። በሌላ በኩል የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ(ህወሓት) ከኢትዮጵያ ፖለቲካ መድረክ መዉጣት፤ ታዋቂ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች በእስር ላይ መሆናቸው እና  አንዳንድ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ አለመሳተፋቸው፤ የዶክተር ዐቢይ ብልፅግና ፓርቲ ጠንክሮ ምርጫዉን እንዲያሸንፍ እና ወደ ስልጣን እንዲመጣ ረድቶታል፤ የሚሉ አስተያየቶችም ይሰማሉ። ሰሞኑን የአዲስ አበባ እና የድሬደዋ መስተዳድርን ጨምሮ የአማራ፤ የኦሮምያ፤ የጋምቤላ ክልሎች መንግሥት መስርተዋል። ደቡብ ክልል የሚገኙ አምስት ዞኖችና አንድ ልዩ ወረዳ ከደቡብ ክልል ለመነጠል፤ አሊያም አብሮ ለመቀጠል የሚያስችላቸውን ሕዝበ ውሳኔ ባለፈዉ ኀሙስ አካሂደዋል። በምርጫ ወደ ስልጣን የመጣዉ ብልፅግና ፓርቲ በይፋ ኃላፊነቱን ለመሸከም እና መንግሥት ለመመስረት በሚዘጋጅበት በዚህ ወቅት ፣በኢትዮጵያ በተለይ በሰሜኑ ክፍል አንድ ዓመት ሊሞላዉ ጥቂት ጊዜያት የቀሩት ጦርነት፤ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች፤ ሞት የረሃብ አደጋ፤ መፈናቀል፤ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት፤ የሚደርስበት ወቅት ነዉ። ነገ የሚመሰረተዉ አዲስ መንግሥት እነዚህን ተግዳሮቶች መወጣት ይችል ይሆን? ከአዲሱ  መንግሥት ምን እንጠብቅ ?

Äthiopien | Premierminister Abiy Ahmed Ali
ምስል Minasse Wondimu Hailu/AA/picture alliance

በዚህ ዉይይት ላይ እዲሳተፉልን የጋበዝናቸዉ፤   

አቶ ኃይሉ አዱኛ፤ በአዲስ የተሾሙት የኦሮሚያ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ። ዶክተር መልሰዉ ደጀኔ፤ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና የልማት ጥናት መምህር እና ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር ናቸዉ። ኢንጂኔር ይልቃል ጌትነት የሕብር ኢትዮጵያ ዴሞክራስያዊ ፓርቲ ከፍተኛ አመራር። እንዲሁም ዶ/ር ብርሃኑ መገርሳ ሌጄሶ፤ የምሥራቅ አፍሪቃ ፖሊሲ ጥናት ተቋም ምክትል ሃላፊ ናቸዉ።

ተወያዮች በዉይይቱ የቀሩቡላቸዉ ጥያቄዎች

--በየደርጃው የተካሄዱትን የመንግስት ምስረታዎችን እና ነገም በዚሁ መንፈስ የሚመሰረተውን የፌደራል መንግስት ምስረታ እንዴት ታዩታላችሁ?

--የተቃዋዋሚዎች በአዲሱ መንግስት ውስጥ መካተት አንደኛ የተወሰኑትን ብቻ የሚያሳትፍ በመሆኑ፤ ሁለተኛ የብልጽግናና ፕሮግራም ለማሳካት ካልሆነ በስተቀር ሌላ ጥቅም የሌውም በማለት ብዙም ግምት የማይሰጡትን ሰዎች አስተያየት እንዴት  ታዩታላችሁ?

--የአዲሱ መንግስት ተግዳሮቶች በርክታዎች ናቸው የሚሉ ጥቂቶች አይደሉም። ኢትዮጵያ ባለችበት ነባራዊ ሁኔታ ማለትም መቋጫ ባጣው ጦርነት ውስጥ ሆነን ፤ የትግራይ ቀዉስ፤ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ሞትና መፈናቀሎች በሚታይበት፤ የሕገ-መንግስት ማሻሻያ ባልተደረገበት፤ የአገሪቱ ኢኮኖሚ መንገራገጭ ውስጥ በገባበት፤ የአገር ውስጥ ፍልሰት በተንሰራፋበት የሚመሰረተው መንግሥት ምን ያህል ተስፋ ያለው ስራ ያከናውናል ?   

--ብልፅግና ምን የሚለዉን መርህ ይዞ ነዉ ሃገሪቷን የሚመራዉ?

--የትግራይ ጉዳይ መፍትሄ እንዴት ነዉ የሚያገኘዉ?

-ዘርፈ ብዙ ችግሮችን በመቋቋም ለመዝለቅስ ምን መደረግ አለበት ወይም አዲሱ መንግስት ምን ማድረግ አለበት ትላላችሁ ምንስ እንጠብቅ?   

ተወያዮች ካነስዋቸዉ ነጥቦች መካከል  

--ኢትዮጵያ ዉስጥ አሁን የሚታየዉ ችግር፤ በአንድ ለሊት የተፈጠረ አይደለም። ለዘመናት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ነዉ። አሁን በምርጫ ወደ ስልጣን የመጣዉ መንግሥት ተስፋ የተጣለበት ነዉ። ሕዝቡም በምርጫ ያሳየዉ ይህንኑ ነዉ። ሕዝቡ ችግሩን ይፈታልኛል ያለዉን ፓርቲ በምርጫ አረጋግጦአል።  

--የአዲሱ መንግሥት ሥራ የሚሆነዉ፤ ሰላም ለማምጣት መፍትሄን መስጠት፤ የዲሞክራሲ ባህል እንዲስፋፋ ማድረግ እና ብልጽግናን ማስፈን ነዉ።

Äthiopien Addis Abeba | Wahlkampfbus Abiy Ahmed Ali Prosperity Party
ምስል Amanuel Sileshi/AFP

--አዲሱ መንግሥት ቅድምያ ሊሰጠዉ የሚገባዉ በሃገሪቱ የሚሰማዉን የጦር መሳርያ ድምፅ በአስቸኳይ ማስቆም ነዉ። ከዝያ ድርድር ከዝያ ድርድር በማድረግ ማኅበረሰቡ በሃገሩ ጉዳይ ላይ አስተዋፅኦ እንዲያደርግ ማሳተፍ ነዉ። ለዚህ ሁሉም ሰዉ አዎንታዊ መግባባት እንዲኖር መጣር እና መስራት ይኖርበታል።

--ጦርነቱን ለማስቆም መንግሥት በዉይይት ለመፍታት እንቅስቃሴዎችን ጀምሮአል። በዚህም አዲሱ መንግሥት አዲስ ተስፋ የተጣለበት አዲስ አወቃቀር የጀመረበት ይሆናል።

--እርዳታ ሰጭ ሃገሮች ባለፈዉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት፤ እነሱ ይረዱናል እንጂ፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ አይተኩም። ከዚህ አንፃር የዉጭ ግንኙነታችን ከወትሮዉ የተለየ አይደለም። አሁን ኢትዮጵያ ከእንግዲህ ወዲህ ስንዴ የምለምንበት ነገር የለም፤ ራሴን አልምቼ ራሴን እችላለሁ፤ በማለትዋ ነዉ፤ እንጂ ከሌሎች ሃገራት ጋር ግጭት ፈጥራ አይደለም።  

--የኢትዮጵያ መንግሥት ወደ ትግራይ እርዳታ እንዳይጓጓዝ አግዶ አያዉቅም። ወደፊትም አያግድም። ወደ ትግራይ እርዳታ ጭነዉ የገቡ ተሽከርካሪዎች ወደዚህ እንዳልተመለሱ እራሱ የተመድ ያስቀመጠዉ ጉዳይ ነዉ።

--በተመድ የሚሰሩ አንዳንድ የምዕራባዉያን ሰራተኞች ከተሰማሩበት ግልጋሎት ዉጭ አልፈዉ ጁንታዉን የሚደግፍ፤ የሃገሪቱን ፀጥታ የሚያደፈርስ፤ ሃገሪቱ እንዳትረጋጋ የሚያደርግ ተግባር ዉስጥ ስለገቡ ነዉ ከሃገር እንዲወጡ የተደረገዉ። ይህ በዓለም አቀፍ ሕግም እንደዚህ ያለ ተግባር ዉስጥ የተሳተፈ፤ ከሃገር ማባረር እና ከሃገር ለቆ እንዲወጣ ማድረግ የሚፈቅድ ነዉ። ስለሆነም ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ሕግ የሚፈቅደዉን ርምጃ ስላደረገች፤ ሉዓላዊነትዋን አንድነትዋን ፤ ሰላምዋን ለማስከበር የወሰደችዉ ርምጃ ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል። ኢትዮጵያ ደሃ ናት እና እንደፈለግን ማድረግ እንችላለን የሚለዉን፤ ኢትዮጵያ በፊትም አልተቀበለችም ፤ ወደፊትም አትቀበልም፤ ለመቀበልም ዝግጁ አይደለችም።

--መስተካከል ያለበት ነገር፤ ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚታየዉ፤ የእርስ በርስ ጦርነት ሳይሆን፤ ሃገሪቱ ህልዉናዋን ለማረጋገጥ ተገዳ የገባችበት ጦርነት ነዉ፤ እንጂ የእርስ በርስ ጦርነት አይደለም። አሸባሪዉ ሃይል የከፈተዉ ጦርነት ነዉ።

--የኢትዮጵያ ሕዝብ መርጦአል። ከመንግሥት ምስረታ በኋላ የልሂቃን ምክክር ይደረጋል።

--የእርስ በእርስ ጦርነት የሚለዉ በአንድ ሃገር ዉስጥ፤ በአንድ ሃገር ልጆች መካከል የሚደረገዉ ጦርነት ነዉ። ጦርነቱ ከዚህ ቀደም ፤ ሕግ ማስከበር ተብሎአል፤ ከዚያም የሕልዉና ጦርነት ተብሎአል። ይሁንና በየትኛዉም መንገድ እና አረዳድ ኢትዮጵያዉያን ከኢትዮጵያዉያን ጋር ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚያድርጉት ጦርነት ነዉ። ይህ የእርስ በእርስ ጦርነት ከመባል የሚያድነዉ ነገር የለም። ማነዉ ጥፋተኛ፤ ጦርነቱን ማን ጀመረዉ፤ የሚሉት ጥያቄዎች ሌላ ሆነዉ፤ ግን ይሄ በኢትዮጵያ ፤ በኢትዮጵያዉያን መካከል በከባድ መሳርያ የሚካሄድ ብዙ ሰዉ የሚሞትበት የሚፈናቀልበት በመሆኑ የእርስ በርስ ጦርነት ስለመሆኑ ሊካድ አይችልም። የእርስ በርስ ጦርነት ለመባል፤ የግድ የብሄር ወይም የሃይማኖት ጦርነት መሆን የለበትም።

--የመንግሥት ምስረታዉ ከወትሮዉ የተለየ አይደለም። ምርጫዉ በቁጥር ከአምስተኛ ወደ ስድስተኛ ምርጫ ተደረገ ካልተባለ፤ የተለየ ነገር አልታየም። ከንጉሱ ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያ የተካሄደዉ ምርጫ ለሕዝቡ መሰረታዊ የሆነ ለዉጥ አላሳየም፤ አላመጣም።

--ምርጫዉ ዋና ዋና የተባሉ የተቃዋሚ ፓርቲዎች አልተወዳደሩበትም። በሶማሌ፤ በኦሮምያ ተቃዋሚዎች አልተሳተፉም። በትግራይ ምርጫ አልተካሄደም። በትግራይ እና በአጎራባች ክልሎች የለየለት ጦርነት ዉስጥ ነዉ ያለነዉ። በዚህ ሂደት ዉስጥ፤ መንግሥት አለ ፤ መንግሥት ተፈጠረ ለማለት ካልሆነ በስተቀር፤ የኢትዮጵያን መሰረታዊ ችግሮች የሚፈታና፤ ከወትሮዉ የተለየ ነገር የሚያመጣ አይደለም።

-- አሁን ጦርነት ዉስጥ ገብተናል፤ የሃገሪቱ ከፍተኛ የኑሮ ዉድነት አለ፤ በሕዝብ መካከል የነበረዉ መተማመን ቀንሶአል፤ እናም አሁን ምንም የተለየ ነገር የለም።

--የደቡብ ምዕራብ ሕዝቦች ሕዝበ ዉሳኔ ተካሂዶአል። ሂደቱ ሰላማዊ ነበር። የክልሉ ሌሎች ሕዝቦች የክልል እንሁን ጥያቄን ለመፍታት መንግሥት ጥያቄዉ፤ ከአስተዳደራዊ አቅርቦት የሚመነጭ ነዉ፤ ወይስ ሌላ አላማ አለዉ ብሎ፤ በደንብ ማጤን ይጠበቅበታል። ለአዲሱ መንግሥት ከፈተናዎቹ አንዱ የሚሆነዉ ይህ ጉዳይ ነዉ።

--የአንድ መንግስት ጥንካሬ የሚለካዉ የሕዝብ ድጋፍ አለዉ ወይስ የሚለዉ ነዉ። ኢትዮጵያ ነፃነትዋን አስከብራ፤ ለሌሎችም ዓለም ሃገራት አረዓያ ሆና የኖረች ሃገር ናት። በኢትዮጵያ ላይ በፊትም ተፅኖዎች ነበሩ፤ ወደፊትም ይኖራሉ። የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን የሚፈልገዉ ነፃነቱን ሉዓላዊነቱን ነዉ።

Logo Prosperity Party Ethiopia

--በመንግሥት መዋቅር ዉስጥ የተሸናፊ ተቃዋሚ«ተፎካካሪ» ፓርቲ አባላት መካተቱ አዲስ ነገር አይደለም። ከዚህ በፊት ባለዉ መንግሥትም የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ሹመት አግኝተዋል።

--መንግሥት የተፊካካሪ ወይም የተቃዋሚ አባላትን በመንግሥት መዋቅር ዉስጥ ማካተቱ በአዎንታዊ የሚታይ እርምጃ ነዉ። በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ፤ የሃሳብ ልዩነት፤ በጠላትነት የሚሳፈርጅበት እና አንዱ አንዱን በጠላትነት የሚያይበት ነበር። አሁን ግን በሃሳብ ልዩነት በጠላትነት ከመፈላለግ ይልቅ፤ አብሮ ወደመስራት ማደግ እንደሚቻል የታየበት ነዉ። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል አንድ እርምጃ ያደገ መሆኑ የታየበት ነዉ።    

--ሰኞ በሚመሰረተዉ መንግሥት በክልል መንግስታት እንደታየዉ ሁሉ የተቃዋሚ አባላት መካከትትን እንጠብቃለን። ለኢትዮጵያ እድገት የሃሳብ ልዩነት ሳይሆን፤ የሰዎች ብቃት በጋራ የመስራት ብቃት የሚታይበት የመንግሥት ምስረታን እንጠብቃለን።

--የኢትዮጵያ ችግር ከአንድ ፓርቲ በላይ ነዉ። በመጀመርያ በሃገሪቱ የሚታየዉ ጦርነት መቆም አለበት። ይህን ለማድረግ በተፋላሚ ሃይላት መካከል፤ ስምምነት መፈጠር አለበት። ከዝያም ሃገር አአፍ ዉይይት ያስፈልጋል። የሽግግር ጊዜ ፍትህ መኖር አለበት። ሕገ መንግሥት ለመቅረፅ የሕገመንግሥት አርቃቂ ኮሜቴ መቋቋም አለበት።

--አዲሱ መንግሥት በሃገሪቱ የሚታየዉን፤ የነዋሪዎች መፈናቀል፤ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ማስቆም አለበት። በሕዝብ መካከል የሚታየዉን አለመተማመን በዉይይት መቅረፍ አለበት።

--አዲሱ መንግሥት ሌላዉ ቅድምያ መስጠት ያለበት በምግብ ራሳችን እንችል ማድረግ ነዉ።

--የኢትዮጵያ ሕዝብ በምርጫ ያሳየዉን ተስፋ፤ ተረባርቦ ከመንግሥት ጎን በመቆም ፤ ስህተት ሲኖር እያረመ፤ ጥሩ የተሰራዉን እያበረታታ፤ በጋራ የምንዘልቅበትን ሁኔታ መፍጠር አለብን። ይህ ሃገራዊ ንቅናቄን የሚጠይቅ ነገር ነዉ።

ሙሉ ዉይይቱን የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን ተከታትለዉ እርሶም አስተያየቶን ይስጡን!

አዜብ ታደሰ

ታምራት ዲንሳ