1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እንቦጭን ከጣና ሐይቅ የማስወገድ ጥረት

ሐሙስ፣ ጥር 27 2013

አረሙን በሰው ኃይል የማስወገድ ስራ ለ66 ቀናት ቀጥሎ 85 ከመቶ የአረሙን ክፍል ማስወገድ እንደተቻለ ወይም ከነበረው 4ሺህ 302 ኬክታር ሽፋን 3ሺህ 657 ሄክታር ማስወገድ መቻሉን የኢፌድሪ ውሀ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢንጂኔር ስለሺ በቀለ ሰሞኑን በተደረገ የማጠቃለያ ስነስርዓት ላይ አመልክተዋል፡፡

https://p.dw.com/p/3otX7
Äthiopien Entfernung von Wasserhyazinthen am Tana See
ምስል Alemneh Mekonnen/DW

በጣና ሐይቅ ላይ የተንሰራፋውን የእንቦጭ አረም የማስወገድ ለሁለት ወራት ሲካሄድ የቆየው ዘመቻ ሲጠናቀቅ የአረሙን 85 ከመቶ ማስወገድ መቻሉን መንግስት አስታወቋል፣ አንድ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህር የተሰራው ሥራ ውጤታማ መሆኑን መስክረዋል፣ አንዳንድ አርሶ አደሮች ደግሞ አረሙ አሁንም ለሐይቁ ስጋት መሆኑን ይናገራሉ፣ አረሙን ለማስወገድ ከ400ሺህ በላይ የሰው ኃይል የተሳተፈ ሲሆን 75 ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉም ተገልጿል፡፡ 
በጣና ሐይቅ ላይ ከዐመታት በፊት የተከሰተውን እምቦጭ አረም ለማስወገድ የተለያዩ ሙከራዎች ሲደረጉ የነበሩ ቢሆንም ብዙ ውጤት ሳመዘገብ ይልቁንም አረሙ በከፍተኛ ሁኔታ ተስፋፍቷል፡፡ አረሙን በሰው ኃይል ለማስወገድ ከጥቅምት 9 /2013 እስከ ህዳር 9/2013 ዓ ም በዘመቻ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ አረሙን በሰው ኃይል የማስወገድ ስራ ለ66 ቀናት ቀጥሎ 85 ከመቶ የአረሙን ክፍል ማስወገድ እንደተቻለ ወይም ከነበረው 4ሺህ 302 ኬክታር ሽፋን 3ሺህ 657 ሄክታር ማስወገድ መቻሉን የኢፌድሪ ውሀ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢንጂኔር ስለሺ በቀለ ሰሞኑን በተደረገ የማጠቃለያ ስነስርዓት ላይ አመልክተዋል፡፡ አረሙ ባለባቸው በ25 ቀበሌዎች ሥራው በሚገባ ተከናውኖ የመልቀምና የማሰባሰብ ስራ እየተሰራ መሆኑን አመልክተው በቀሪ 3 ቀበሌዎች ከፍተኛ ሽፋን በመኖሩ፣ በሌሎች 2 ቀበሌዎች ደግሞ የሐይቁ ከፍተኛ ጥልቀትና የአረም ማጠራቀሚያ ቦታ እጥረት እንቅፋት በመሆናቸው የተፈለገውን ያህል እንዳልተሄደ ግልፅ አድርገዋል።

Äthiopien Entfernung von Wasserhyazinthen am Tana See
ምስል Alemneh Mekonnen/DW

እምቦጭ አረም በሌሎች የአገሪቱ ሐይቆችም እየታየ እንደሆነና የሚያስከትለውን ችግርም ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡ ጉዳዩን በቅርበት የሚታተሉት በባሕር ዳር ዩኒቨረሲቲ የስነ ህይወት መመህር ዶ/ር ነጋ ጣሴ የተሰራውን ሥራ “ውጤታማ” ብለውታል፡፡ የዛምባ ቀበሌ ሊቀመንበር አቶ አቻም ፀጋ ህብረተሰቡን በማስተባበር ከሌላው ጊዜ የተሸለ ሥራ መሰራቱን ለዶይቼ ቬለ ገልፀዋል፡፡ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የጎንደር ዙሪያ ወረዳ ላምባ አርባይቱ ቀበሌ አርሶአደር አቶ ማሬ ገዛኸኝ “ትኩረት ሰጥተንን ብንሰራም አረሙን ሙሉ ለሙሉ ማስወገድ አልቻልንም” ብለዋል፡፡ የጣና ሐይቅና የሌሎች ውሀ አካላት ኤጀንሲ ዳይሬክተር ዶ/ር አያሌው ወንዴ ባለፉት 66 ቀናት አረሙን ለማስወገድ እስከ 400ሺህ የሰው ኃይል መሳተፉን፣ 75 ሚሊዮን ብር ደግሞ ወጪ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ እንደ ባለፉት ወራት ህብረተሰቡና አመራሩ ተናብቦና ተቀናጅቶ ከተሰራ አረሙን ሙሉ በሙሉ ከሐይቁ ማስወገድ እንደሚቻል አስተያየት ሰጪዎቹና ባለስልጣናቱ ተናግረዋል፡፡

Äthiopien Entfernung von Wasserhyazinthen am Tana See
ምስል Alemneh Mekonnen/DW

ዓለምነው መኮንን


ኂሩት መለሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ