1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

“እናስታውሳችሁ” በኪነጥበብ ባለሙያዎች!

ሰኞ፣ ጥቅምት 9 2013

ሕብረተሰቡ በኮሮና ላይ ያለው መዘናጋት የበለጠ ዋጋ እንዳያስከፈል የኪነጥበብ ባለሙያዎች አሳሰቡ፣ የመከላከያ ዘዴዎችን አለመጠቀም አዝማሚያ በስፋት እየታየ መሆኑን የአማራ ክልል ጤና ቢሮ አስታውቋል።

https://p.dw.com/p/3k86q
Äthiopien Addis Ababa | Coronavirus | Kunst schafft Bewusstsein
ምስል Alemenew Mekonnen/DW

ኮሮና መኖሩን ``እናስታውሳችሁ``

“እናስታውሳችሁ” በኪነጥበብ ባለሙያዎች!
ሕብረተሰቡ በኮሮና ላይ ያለው መዘናጋት የበለጠ ዋጋ እንዳያስከፈል  የኪነጥበብ ባለሙያዎች አሳሰቡ፣ የመከላከያ ዘዴዎችን አለመጠቀም አዝማሚያ በስፋት እየታየ መሆኑን የአማራ ክልል ጤና ቢሮ አስታውቋል። የክልሉ ትምህርት ቢሮ በበኩሉ የትምህርት ቤት መከፈቻ ወቅት በመሆኑ ሁሉም ተማሪዎች የመከላከያ ዘዴዎችን እንዲጠቀሙ አስጠንቅቋል፡፡በአማራ ክልል ህብረተሰቡ በኮሮና ላይ ያለው ጥንቃቄና ዝግጁነት ከእለት ወደእለት እየተቀዛቀዘ በመምጣቱ ከፍተኛ ስጋት መፈጠሩን የህክምና ባለሙያዎች እየተናገሩ ነው፡፡ በተለይ ትምህርት ቤቶች ሊከፈቱ ነው መባሉን ተከትሎ በሽታው የለም እስከ ማለት በመደረሱ ሕብረተሰቡ የመከላከያ ዘዴዎችን መጠቀም ማቆሙን ይገልፃሉ፡፡ይህን የተቀዛቀዘ የመከላከል ፍላጎት ወደ ነበረበት ለመመለስ ታዋቂ የኪነጥበብ ባለሙያዎችና ኮሜዲያን “እናስታውሳችሁ” በሚል መሪ ቃል ከአማራ ፖሊስ የሙዚቃ ባንድ ጋር በመተባበር በባሕር ዳር ከተማ ዋና ዋና ጎዳናዎች በመዟዟር ትናንት ቅስቀሳ ሲያደርጉ ውለዋል፡፡በእለቱ ከተገኙት የኪነጥበብ ባለሙያዎች መካከል ዳግማዊ ፈይሳ ቀደም ሲል የነበረው ጥንቃቄ እየተረሳ በመሆኑ በሙያቸው እናስታውሳችሁ በሚል ህብረተሰቡን ለመቀሰስቀስ ከአዲስ አበባ መምጣታቸውን አመልክቷል፡፡
በአብዛኛው አድናቂዎቹ ፍልፍሉ በሚል ስም የሚታወቀው ኮሜዲያን በረከት በቀለ “ቀደም ሲል ለኮሮና መከላከል አገልግሎት ይውሉ የነበሩ የመከላከያ ቁሳቁሶች ዛሬ ዞር ብሎ የሚመለከታቸው የለም” ሲል ተናግሯል፡፡የተቀዛቀዘውን የመከላከል ስራ በታዋቂ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ለማሳሰብ የተዘጋጀ ፕሮግራም መሆኑን ደግሞ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር መልካሙ አብቴ ተናግረዋል፡፡የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ይልቃል ከፋለ በበኩላቸው ዛሬ በታዋቂ የኪነጥበብ ሰዎች የተደረገው ቅስቀሳ ጠቃሚ መሆኑን ጠቁመው፣ ትምህርት ከዛሬ ጀምሮ የሚጀመር በመሆኑ ተማሪዎች የኮሮና መከላከያ መንገዶችን ሳያዛንፉ እንዲተገብሩ መክረዋል፡፡በቅስቀሳ ፕሮግራሙ ላይ ከአዲስ አበባ የመጡ በርከት ያሉ የኪነጥበብ ባለሙያዎችና የአማራ ክልል የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡


ዓለምነው መኮንን

ታምራት ዲንሳ

አዜብ ታደሰ