1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እርጥበት አዘል አየርና የኮሮና ተዋህሲ ስርጭት 

ረቡዕ፣ ነሐሴ 20 2012

የኮሮና ወረርሽኝ ስርጭትን ለመቆጣጠር ተመራማሪዎች በዓለም ዙሪያ በርካታ ጥናቶችን በማካሄድ አዳዲስ ግኝቶችን ይፋ ሲያደርጉ ቆይተዋል።ከሰሞኑም በጀርመንና በህንድ ተመራማሪዎች  አንድ  ጥናት ይፋ ሆኗል።በዚህ ጥናት  የኮሮና ተዋህሲ ስርጭት ከእርጥበት አዘል አየር ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው ተመልክቷል።

https://p.dw.com/p/3hYGy
Mann beim Niesen
ምስል picture-alliance/dpa/PA/Jordan

እርጥበት አዘል አየርና የኮሮና ተዋህሲ ስርጭት 

በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለህመም በመቶ ሺህ የሚቆጠሩትን ደግሞ ለሞት እየዳረገ ለሚገኘው የኮሮና ወረርሽኝ፤ ማርከሻ መድሃኒት እንዲሁም መከላከያ  ክትባት ለማግኜት  በርካታ ተመራማሪዎች ጥናት በማድረግና በመሞከር ላይ ይገኛሉ።ከዚህ ጎን ለጎንም  በተዋህሲው ባህሪና የመተላለፊያ መንገዶች ላይ የሚደረገው ምርምርና ጥናትም ቀጥሏል።ለአብነትም በቅርቡ የደች ተመራማሪዎች የተዋህሲውን ባህሪ በሚመለከት ባወጡት ጥናት 5 ማይክሮ ዲያሜትር ያለቸው ከሰዎች ትንፋሽ የሚወጡ ጠብታዎች እስከ 9 ደቂቃ ያህል በአየር ላይ መቆየት እንደሚችሉ ማረጋገጥ ችለዋል። ያለፈው ሀምሌ ወርም ከ32 ሀገራት የተውጣጡ 239 ሊቃዉንት  ከሰው ለሰው ንክኪ በተጨማሪ የኮሮና ወረርሽኝ ስርጭትን ለመቆጣጠር  አየር ላይ ለሚንሳፈፉ የጠብታ ቅንጣቶች ወይም «ኤሮዞልስ»ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ የሚያሳስብ ጥናት ለዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት  አቅርበው  ነበር።ከሰሞኑ ደግሞ የጀርመንና የህንድ ተመራማሪዎች በጋራ ባደረጉት ምርምር የኮሮና ተዋህሲ ስርጭትን  በተመለከተ አዲስ ጥናት ይፋ አድርገዋል።
የኮሮና ወረርሽኝ  በበሽታው ከተያዙ ሰዎች  በሚስነጥሱበትና በሚያስሉበት ወቅት  በሚወጡና ተዋህሲውን በተሸከሙ ጠብታዎች  የሚተላለፍ በመሆኑ  በሽታው በሰው ለሰው ንክኪ በቀጥታ የሚተላለፍ ብቻ ተደርጎ ይወሰድ ነበር።በዚህ የተነሳ  ከበሽታዉ ራስን ለመጠበቅ  በዓለም ዙሪያ የእንቅስቃሴ ገደቦችን መጣል፣ አካላዊና ማኅበራዊ ርቀትን መጠበቅ፣  የፊትና የአፍንጫ መሸፈኛዎችን ማድረግ የመሳሰሉት የጥንቃቄ መርሆዎች ተደጋግመው ይሰማሉ። ይሁን እንጅ  ሰሞኑን ይፋ የተደረገው አዲሱ ጥናት እንዲሚያሳየው ግን እርጥበት አዘል አየር በኮሮና ተዋህሲ ስርጭት  ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አለው ።በጀርመን ላይፕዚግ  የላይበንዝ የምርምር ተቋምና በህንድ የኒዉ ደልሂ ብሄራዊ  ቤተ-ሙከራ  ተመራማሪዎች  የቀረበው  ይህ  ጥናት በተለይም ደረቅና የአየር ማቀዝቀዣ ያላቸው ቤቶች፣የመሰብሰቢያ አዳራሾችና የቤት ዉስጥ መዝናኛዎች የኮሮና ተዋህሲ ስርጭትን ከመጨመርና ከመቀነስ ጋር እርጥበት ወይም  በእንግሊዝኛው አጠራር« Humidity »ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው አመልክቷል። 
በዚህ የተነሳ  ወረርሽኙን ለመከላከል ከሚደረጉ መመሪያዎች እኩል የቤት ዉስጥ እርጥበት አዘል አየር ወሳኝ ነው ሲል ጥናቱ ያትታል።በዚህ መሰረት የወረርሽኙን ስርጭት ለመቀነስ በቤት ዉስጥ የአገልግሎት መስጫ ተቋማና ህዝብ በሚበዛባቸው ህንፃዎች ውስጥ የሚገኝ አየር  በውስጡ የሚይዘዉ የዕርጥበት መጠን ቢያንስ 40 በመቶ መሆን እንዳለበትም የጥናት ቡድኑ መሪና በጀርመን ላይፕዚግ የላይበንዝ የምርምር ተቋም ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር አልፍሬድ ቪደንዞላ ያስረዳሉ።
«ስለዚህ በቤት ውስጥ በጣም ጥሩ የሚባለው የእርጥበት መጠን  ከ40 እስከ 60 በመቶ ድረስ ነው።ለምሳሌ በሚያስለን ጊዜ  በጣም ጥቃቅን፤ማለትም የማይክሮ ሜትር  መጠን ያላቸው ጠብታዎች ከሳሉ ጋር ይወጣሉ።እነዚህ ጠብታዎች ተዋህሲ የተሸከሙ ሊሆኑ ይችላሉ።ግን ወዲያዉኑ በክፍሉ ውስጥ መትነን ይጀምራሉ።ጠብታዎቹ ውሃ  ያዘሉና ትልልቅ እስከሆኑ ድረስ ግን ወደታች ይወድቃሉ።»
 የምርምር ቡድኑ የጥናት ዉጤት እንደሚያሳየው የቤት ውስጥ የአየር እርጥበት፤ የኮሮና ተዋህሲ የተሸከሙ ጠብታዎችን ባህሪ በመወሰን፣ በገፀ-ቁሶች ላይ የተዋህሲውን በሕይወት የመኖር ወይም የአለመኖር ሁኔታን እንዲሁም  በቤት ውስጥ  ወደ ሌላ ሰው የመተላለፍ ዕድል በመወሰን በሦስት መንገዶች የኮሮና ተዋህሲ ስርጭት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል፡፡ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት ተዋህሲውን የተሸከሙ  የትንፋሽ ጠብታዎች አየር  ላይ የሚቆዩበትና በቁሶች ላይ የሚያርፉበት ጊዜ በአየር የእርጥበት መጠን ይወሰናል። በእርጥበት አዘል ቦታዎች ውስጥ  ተዋህሲውን የተሸከሙ የጠብታ ቅንጣቶች  በፍጥነት ወደ መሬት ስለሚወድቁ አየር ላይ የመቆየት ዕድላቸው ጠባብ ነው።ያ ማለት የቤት ውስጥ አየር ይበልጥ እርጥበት ያዘለ ሲሆን ቅንጣቶችም የበለጠ ውሃ ስለሚይዙና ክብደታቸው ስለሚጨምር በአየር ላይ ከመንሳፈፍ ይልቅ ወደ መሬት እንዲወድቁ ይሆናሉ ማለት ነው።በዚህ ጊዜ ሰዎች በሚተነፍሱት አየር ውስጥ የሚሰራጨው የተዋህሲ መጠን ስለሚቀንስ በወረርሽኙ የመያዝ ዕድላቸው ይቀንሳል ማለት ነው።ነገር ግን በደረቃማ የቤት ውስጥ ተዋህሲያኑ አየር  ላይ  የመቆየት ዕድላቸው ሰፊ በመሆኑ በዚያው መጠን ሰዎች በሚተነፍሱት አየር በተዋህሲው የመያዝ አደጋን ይጨምራል።የአተነፋፈስ ስርዓትንም ያውካል።
«ዝቅተኛ የእርጥበት መጠን ካለ የአተነፋፈስ ስርዓታችንን ይጎዳል።ያ ማለት ደረቅ አየር ካለ የበለጠ ተጋላጭ እንሆናለን።ተዋህሲዉም ወደ ህዋሶቻችን ዘልቆ ሊገባ ይችላል።ምክንያቱም በደረቃማው አየር ቀድመን  ተጎድተናልና።መጠነኛ እርጥበት ያዘለ አየር ካለ ግን ይህ ጉዳት በመጠኑ ይቀንሳል።»በማለት ገልፀዋል።
በሌላ በኩል ደረቅ አየር በአፍንጫችን ውስጥ  «ሙከስ ሜንብሬን» ተብሎ የሚጠራዉን የእርጥበት መጠን በመቀነስ ኮቪድ-19 በሽታን ለሚያመጣዉ ተዋህሲ  በእጅጉ ተጋላጭ ያደርጋል።ይህ ሁኔታ በሰሜናዊው ንፍቀ ክበብ መጭውን ቀዝቃዛ የክረምት ወቅት ለመቋቋም ክፍሎቻቸውን በሚያሞቁ  በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን  በተዋህሲው የመያዝ  አደጋ ከፍተኛ ሊያደርገው እንደሚችል ፕሮፌሰር ቪደንዞላ አሳስበዋል።ሰዎች የቤት ውስጥ ቀዝቃዛ አየርን ተስማሚ ወደ ሆነ ሙቀት ለመቀየር የሚጠቀሙት ሰው ሰራሽ ማሞቂያ የቤት ውስጥ አየርን አንፃራዊ እርጥበት ስለሚቀንስ ሰዎች በተዋህሲው እንዲያዙ  ያደርጋል። በሞቃታማ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎችም ሰው ሰራሽ ማቀዝቀዣን ከመጠቀም እንዲቆጠቡ መክረዋል።ምክንያቱም የቤት ውስጥ የሙቀት መጠንንን ምቹ ለማድረግ በሚደረገው የማቀዝቀዝ ሂደት የቤት ውስጥ የአየር ፍሰት እርጥበቱን እንዲያጣ ስለሚያደርግ እንደ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ቪንደርዞላ በክፍሉ ውስጥ የተዋህሲውን ቁጥር እንዲጨምር  ያደርጋል።
«የአየርን ማቀዝቀዝም ይሁን በክረምት ማሞቂያ መጠቀም የእርጥበት መጠንን ይቀንሳል።ጠብታዎችም በፍጥነት ይተናሉ።ያማለት ወደ መሬት የሚያርፉት የጠብታዎች ቁጥር  በጣም ይቀንሳል። በክፍሉ ውስጥ በአየር ላይ የሚንሳፈፉ ተዋህሲያን ቁጥር  ደግሞ ይጨምራል።»ብለዋል።
የመካከለኛው ምስራቅ የመተንፈሻ አካል በሽታን እንዲሁም ኢንፍሎዌንዛን  በመሳሰሉ  የመተንፈሻ አካል በሽታዎች ላይ  የተደረጉ ቀደምት ጥናቶችንና አሥር የቅርብ ጊዜ የዓለም አቀፍ ጥናቶችንና  መሰረት ያደረገው ይህ ምርምር ፤ መስኮቶችን በመክፈትና ሰው ሰራሽ አየር ማጣራያዎችን በመጠቀም  የቤት ውስጥ የአየር  እርጥበት መጠንን በመጨመር  በአንፃሩ ደግሞ የተዋህሲውን ክምችት መቀነስ እንደሚቻልም ጠቁሟል። 
«በአየር ማዘዋወሪያ ማዕከላዊ ስርዓቱ ውስጥ የቅንጣት ማጣሪያ ካለ ችግሩ ይቀንሳል።ሁለተኛውና  ጠቃሚው ነገር ክፍልን በተደጋጋሚ ማናፈስ ነው።ያ ማለት  በክረምት ወቅት መስኮቶችን ለአምስት ወይም ለአስር ደቂቃ በመክፈት አየሩን መቀየርና የተዋህሲውን ክምችት መቀነስ ነው።»በማለት ፕሮፌሰር አልፍሬድ ቪደንዞላ ገልፀዋል።
በአጠቃላይ የጥናት ውጤቱ እንደሚያሳየው እርጥበታማ አየር ባለበት ቦታ በአንፃራዊነት የጠብታዎቹ ክብደት  ስለሚጨምር ብዙም ሳይጓዙ ቶሎ መሬት ላይ ስለሚወድቁ አየር ላይ የሚቆዩበት ጊዜ አጭር ይሆናል።የአንድ ነጥብ አምስት ጫማ ወይም የሁለት ሜትር ርቀትን የመጠበቅ ሀሳብም ከዚህ የመነጨ ነው።  ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዚህ ርቀት ውስጥ ሆነውም ሰዎች አንድ ክፍል ውስጥ በመሆናቸው ብቻ  በኮቪድ-19 በሽታ  መያዛቸውን  ተመራማሪዎቹ አመልክተዋል። በመሆኑም በማረፊያና በእስር ቤቶች፣በቤተ-እምነቶች፣በህዝብ መጓጓዣዎች፣በሆስፒታሎች፣በትምህርት ቤቶች፣ በመሰብሰቢያ አዳራሾችና ብዙ ሰራተኞች አንድ ላይ በሚሰሩባቸዎ ቢሮዎች  ርቀትን መጠበቅና የፊት መሸፈኛ ማድረግ ብቻ በቂ ባለመሆኑ ጤናማና በቂ እርጥበት ያዘለ አየር በክፍሉ ውስጥ እንዲኖር ማድረግ የተዋህሲውን ስርጭት ለመግታት ወሳኝ መሆኑን ተመራማሪዎቹ አስምረውበታል።


ፀሐይ ጫኔ/ኮኖር ዲሎን
እሸቴ በቀለ