1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እምንቦጭን የማረሙ ዘመቻ የአንድ ሰሞን ይሆን?

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 14 2011

የጣና ሐይቅን 50 ሺህ ሄክታር  የሚሆን የውኃ አካል የሸፈነው እምቦጭ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚገኘው እና በኢትዮጵያ በሁለተኛነቱ የሚታወቀውን የአባያ ሐይቅንም እንዲሁ መውረሩ ተሰምቷል። አረሙ የአባይ ወንዝንም አዳርሷል። እምቦጭን የማስወገዱ የአንድ ሰሞኑ የማፅዳት ዘመቻ አሁን የረገበ መስሏል።

https://p.dw.com/p/3ODrv
Wasserhyazinthen  Lake Tana Äthiopien
ምስል Adugnaw Admas

ዛሬም አረሙ ትኩረት ይሻል

ከሁለት ዓመት በፊት ጣና ሐይቅን  ስለወረረው መጤ የውኃ ላይ አረም ምንነት እና ስጋት አንስተን ምሁራንን ስናነጋግር ሀገሬው እምቦጭ የሚለው ይህ ተክል ወደ ሀገር ከገባ ዘመናት መቆጠራቸውን ሰማን። ገና በቆቃ ግድብ እና ሐይቅ አካባቢ ሲታይ እንዲህ ይዛመታል ተብሎ ባለመገመቱ የተወሰደ ርምጃ ባለመኖሩ ውሎ አድሮ በስስት የሚታዩትን የኢትዮጵያን የውኃ አካላት ማዳረሱም ተነገረን። ጣና ታሟል እንድረስለት ተብሎ የአካባቢው አርሶ አደር እና ወጣቶች ሲረባረቡበት የነበረውን እምንቦጭን ከጣና ላይ የማረም ዘመቻ ሌሎችም ተቀብለውት አንድ ሰሞን ወሬው ሁሉ ጣና፣ ዘገባው ሁሉ እንቦጭን የማጥፋት ጥረት ሆኖ ሰነበተ። እንቦጭን ለማጥፋት የሚያግዙ ማሽኖች ተሠሩ፣ ገንዘብ ከየቦታው ተዋጥቶም ተገዙ ተባለ። እንቦጭ ግን ዛሬም ጣና ላይ እንደተንሰራፋ፣ አባይንም እያዳረሰ፣ በደቡብም እነሻላ እና አብያታንም እንደወረሰ አለ።

በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ ስልቶች ሊጠፋ ጥረት ሲደረግበት የነበረው እምቦጭ አሁን በምን ደረጃ ላይ ይገኛል በማለት ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ወገኖችን በጠየኩበት አጋጣሚ ያገኘሁት መረጃ የአንድ ሰሞኑ ዘመቻ እና እንቅስቃሴ አሁን ተቀዛቅዟል የሚል ነው። ባሕር ዳር ፖሊ ቴክኒክ የሚገኙት መምህር ብሩክ ግርማ  «አረሙ አሁን ተንሰራፍቷል» ነው የሚሉት።

በነገራችን ላይ አድማጮች በማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃን በተሰራጩ ፎቶዎች አማካኝነት የጣና ቂርቆስ ገዳምን ዙሪያ ገባ ወርሶ  የተመለከትኩት እምቦጭ ባለፈው ጥር ወር ወደ ጣና ሐይቅ ብቅ ባልኩበት አጋጣሚ  በግል እንዳስተዋልኩት በአንዲት ኢትዮጵያዊት አስተባባሪነት ሰዎች ርብርብ እና ጥረት ፀድቶ ለማየት ችያለሁ። ይህን ገለጽኩላቸው ለመምህሩ፤

 «ልክነሽ ያኔማ በጣም እንቅስቃሴ የነበረበት ትኩረትም የተሰጠበት ጊዜ ነበር።»

Wasserhyazinthe in Äthiopien Lake Tana
እምቦጭ ከቅርበት ሲታይምስል DW/S. Legesse

ሀገሬው የበኩሉን ጥረት እንደሚያደርግ የሚናገሩት መምህር ብሩክ ሌላው ቀርቶ አንድ ሰሞን ብዙ የተወራላቸው ማሽኖች ሁሉ ከሥራ ውጭ መሆናቸውን ነው የገለፁልን።

ጣናን ለመታደግ ተገቢው እንቅስቃሴ እየተደረገ እንዳልሆነ በአፅንኦት የገለፁት መምህር በዚህ ሐይቅ ላይ የደረሰው ችግር ለታላቁ አባይ ወንዝ መትረፉ እንግዳ ነገር ተደርጎ ሊታይ እንደማይገባም ያመለክታሉ። እምቦጭን ከሐይቁ ላይ በመሰብሰብ የሚያስችል ማሽን በግሉ ሠርቶ ማቅረቡን በመጥቀስ ከዚህ ቀደም በዚሁ መሰናዶ እንግዳ ያደረግነው የሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ምሩቅ የሆነው አራጋው ደስታም ማሽኖችን ተጠቅሞ አረሙን ለማስወገድ ያለመው ፕሮጀክት ባለበት ቆሟል ይላል።

«እኛ ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የጀመርነው ፕሮጀክት ነበረ ባልታወቀ ምክንያት እንዲቆም ተደርጓል። ሌሎች ሥራዎች በጥቅሉ ከእኛ ጋር ያላቸው ነገሮች ቆመዋል። እነሱም የሚሞክሩት ነገር የለም። ዝምብሎ ቁሞ ነው ያለው ፕሮጀክቱ በሙሉ። ምንም ነገር የለም በቃ የሆነች ቀረጻ ነገር ስትኖር ያችን ያስመጣሉ። ያቺ ቀረጻ ካለፈች በኋላ የሚሠራ ሥራ የለም ይቆማል ማሽኑ በሙሉ ቆሞ ነው ያለ ከውጭ የገባውም ቆሞ ነው ያለ አይሠሩም ሥራ።»

አራጋው ሌሎች ሃገራት እንደእምቦጭ ያለውን የውኃ ላይ አረም ለማስወገድ የተጠቀሙበትን ስልት ተመልክቶ የሠራው ማሽን አረሙ ከሐይቁ ላይ የመጠጠውን ውኃ መጭመቅ የሚያስችል ነው። እሱ በወቅቱ እንደታዘበው የአረሙ 95 በመቶ ውኃ ነው። በሀገር ውስጥ ከተሠሩት ማሽኖች ሌላ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት ለማሽን መግዢያ ገንዘብ ሲያዋጡ አንዳንዶቹም ዋጋውን ሁሉ ሲገልፁ መዘገባችን ይታወስ ይሆናል።

Äthiopien - Tana See - Kleine Maschine
አራጋው የሠራው ማሽንምስል Aragaw Desta

ከጣና ላይ አረሙን ለማንሳት ወጣቶችን አስተባብሮ ይንቀሳቀስ የነበረው የጣና ሐይቅ እና አካባቢው እንክብካቤ እና ጥበቃ በጎ አድራጎት ማሕበር አሁን በዚህ ተግባር ላይ እንደሌለ ነው ለመረዳት የቻልኩት። የዛሬ ሁለት ዓመት በጉዳዩ ላይ ያነጋገርኩትን የማሕበሩን የባሕር ዳር አስተባባሪ ቃልኪዳን ፀናን ለምን ? አልኩት።

«አሁን በእኛ በዚህ በወጣቶች እና በበጎ አድራጎት ሥራ ላይ ምንም እየተሠራ አይደለም። ከዚህ በፊት የተጀመረው ፕሮጀክት ወጣቶች ነበርን ያቋቋምነው የበጎ አድራጎት ማሕበር ያው ባለው ፖለቲካዊ ሁኔታ በመሀልም ደግሞ የነበረው ይኼ ኮማንድ ፖስት የታወጀው በዚያ ምክንያት በቃ ወጣቱ እየተሰባሰበ እንደልብ መሥራት አልተቻለም። ከአካባቢ ጥበቃም ጋር አንዳንድ ነገሮች ነበሩ ያው ወጣቱም ሢሠራ ከራሱ ከኪሱ ገንዘብ ነው፤ በተጨማሪ ደግሞ የበጎ አድራጎት ማሕበሩ ከተለያዩ ቦታዎችም አንዳንድ ገቢዎችን በማሰባሰብ የተለያየ ማሽኑንም የማስገዛት፤ አለያ ደግሞ በእጅ የሚሆነው አዋጪ ስለሆነ በእሱ እንሠራለን ብለን ነበር። ያው አንዳንድ ነገሮች ከመንግሥትም የሚወጡ ሕጎች ነበሩ በዚያ ምክንያት ያው መቀጠል አልቻልንም።»

በተለይ እምቦጭ ተስፋፍቶ ይገኝበት ከነበረበት አካባቢ አንዱ በጎርጎራ በኩል ያለው የጣና ሐይቅ ክፍል ነው። ወደ አካባቢው ለሥራ ተጉዞ ገና መመለሱ እንደሆነ የገለፀልኝ የአካባቢ ተፈጥሮ ተቆርቋሪው አቶ አዱኛው አድማስ የእምቦጭ አረሙ ይዞታ ያለበትን እንዲህ ገልፆልኛል።

«ሰኔ ጀምሮ ሐምሌ ነሐሴ ሸሽቶ የነበረው ውኃ ገና እየተመለሰ ነው። ድሮ የነበረው የእምቦጩ እንትን የለም። ምክንያቱም ውኃው በደረቀ ቁጥር አብሮ ይደርቃል። ነገር ግን እምቦጩ ዘሩ ተቀብሮ ስለነበረ የመብቀል የመስፋፋት ነገር አለ። ምናልባት አሁን በትክክል ሰፍቷል ለማለት እስከ መስከረም እስከ ጥቅምት ነው ውኃው ተመልሶ የሚመጣው። በዚያ ሰዓት የእምቦጭ መጠን ከድሮው መቀነስ እና አለመቀነሱን ያኔ ነው መታዘብ የሚቻለው።»

ጣና ሐይቅን እና ሌሎች ስም ያላቸው የኢትዮጵያን የውኃ ሃብቶች የወረረው የእምቦጭ አረምን ማስወገድ ባይቻል እንኳን መስፋፋቱ እንዲገታ ለማድረግ የሚረዱ እንቅስቃሴዎች ባሉበት የቆሙ መሆኑን ነው በቅርበት ከሚከታተሉት እማኞች ለመረዳት የቻልነው። በዚህ መሃል አሁንም አረሙ የሚጠፋበት አልያም ወደሌላ ጥቅም ለመለወጥ እንዲቻል የሚያግዙ ሙከራ እና ፕሮጀክቶችን በትኩረት የሚሠሩ አልጠፉም። በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ ተመራማሪ እምቦጭን በስነሕወታዊ ዘዴ ለማጥፋት ጥንዚዛዎችን በማርባት ያዘጋጁ ምሁር ጥረታቸውን ማቅረባችን ይታወሳል። ይህንም ምርምር በበላይነት የሚመሩት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ጌታቸው በነበሩ  እንደሚሉት ይህ ስልት በአፍሪቃ እና በሌሎች ሃገራት የሚገኙ በእንቦጭ የተወረሩ ሐይቆችን ከአረሙ ማላቀቅ ተችሏል። በምሳሌነትም የዩጋንዳው ቪክቶሪያ ሐይቅ ላይ የተደረገው ሙከራ ዉጤታማ መሆኑንም ያነሳሉ። አንዳንዶች ጥንዚዛዎቹ ሌላ ችግር ቢሆኑስ የሚል ስጋት ያነሳሉ፤ ተመራማሪው ግን ይህ አሳሳቢ እንዳልሆነ ነው ያረጋገጡት። ምርምሩ ተሰርቶ፤ የት ቦታ ጥንዚዛዎቹ ይለቀቁ የሚለው ሁሉ ተለይቶ ቢጠናቀቅም ገና ተግባራዊ አልሆነም።

Äthiopien Kampagne Save Lake Tana
የያኔው የጣና ሐይቅ እና አካባቢው እንክብካቤ እና ጥበቃ በጎ አድራጎት ማሕበር ዘመቻ ምስል Kalkidan Tsena

ጣና ሐይቅ ላይ ብቻ ሳይሆን በአባይ ወንዝም ሆነ በኢትዮጵያ በትልቅነቱ ሁለተኛ በሆነው በአባያ ሐይቅ ላይ የተንሰራፋው እምቦጭ አረም፤ በሰዎች ርብርብ ሆነ በማሽኖች ርዳታ ብቻ ፈፅሞ ማስወገድም ሆነ ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሆን  ማድረግ አዳጋች እንደሆነ የሚናገሩ አሉ። ጉዳዩን በቅርበት ከሚያውቁት ባለሙያዎች አንዱ የሆኑት ዶክተር ዋሴ አንተነህ ሌሎች ስልቶችን መጠቀም ያስፈልጋል ባይናቸው።

የውኃ ላይ አረም የሆነውን በእኛ ሀገር እምቦጭ የሚል መጠረያ የተሰጠውን ተክል ለተለያዩ ነገሮች መሥሪያ የተጠቀሙ ሃገራት መኖራቸውን መረጃዎች ያሳያሉ። ኢትዮጵያ ውስጥም ለአካባቢው ኅብረተሰብ ጥቅም ሊውል የሚችልበትን ስልት የቀየሰ ሌላ ምርምር እንደተካሄደ ለመረዳት ችለናል። ምርምሩ ምን ይሆን? ለምላሹ ለሳምንት እንቅጠራችሁ።

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ