1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እምቦጭ ለጣና አሁንም ሥጋት ነው ተባለ

ቅዳሜ፣ ግንቦት 7 2013

ባለፉት 7 ወራት በጣና ሐይቅ ላይ የተንሳፈፈውን የእምቦጭ አረም ለማስወገድ የተሰራው ስራ መልካም ቢሆንም የተጠራቀመው አረም መወገድ ባለመቻሉ አሁንም ለሐይቁ ስጋት እንደሆን የአካባቢው አርሶ አደሮች ተናገሩ። የጣና ሐይቅና ሌሎች ወሀ አካላት ጥበቃ ልማት ኤጀንሲ በበኩሉ በበጀት እጥረት አረሙን ማንሳት አልቻልሁም ብሏል። 

https://p.dw.com/p/3tR1z
Äthiopien Entfernung von Wasserhyazinthen am Tana See
ምስል Alemneh Mekonnen/DW

እምቦጭ ለጣና አሁንም ሥጋት ነው ተባለ

የጣና ሐይቅ ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ በእምቦጭ አረም መወረር ጀምሯል። አረሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ አድማሱን በማስፋት ለሐይቁ ህልውና አደጋ ሆኖ ቆይቷል። አረሙን በሳይንሳዊና በባህላዊ መንገድ ለማጥፋት በርካታ ሙከራዎች ሲደረጉም ቆይተዋል።  ካለፈው ጥቅምት 2013 ዓ ም ጀምሮ ግን በሰው ኃይልና በማሽን ጭምር በመታገዝ አብዛኛውን የሐይቁን ክፍል ከአረሙ ማፅዳት መቻሉን የሸሐ ጎመንጌው አርሶ አደር  አቶ ማረው መክበብ ይናገራሉ።

ይሁን እንጂ በተለያዩ ሰበቦች አረሙን ከተከማቸበት ቦታ ላይ ማንሳት ባለመቻሉ እንደገና እየበቀለ ወደ ሐይቁ ተመልሶ ይንሰራራል  የሚል ስጋት እንዳላቸው አስረድተዋል። አረሙ ከአንድ ቀበሌ ላይ ብቻ የተነሳ ሲሆን ደንባ አርባይቱ፣ ምጥረ አባዋርካ፣ ቀሀና ፈርቃ ዳንጉሬ ቀበሌዎች ላይ አልተነሳም ብለዋል።

የጣና ሐይቅና ሌሎች ወሀ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አያለው ወንዴ በጉዳዩ ዙሪያ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ እስካሁን አረሙን ለማስወገድ 100 ሚሊዮን ብር ወጪ መሆኑን ጠቅሰው የተከማቸውን አረም ለማስወገድ የፋይናንስ እጥረት አጋጥሟቸዋል።

አሁን የቀረው የማሽን ስራ ብቻ ነው ያሉት ዶ/ር አያሌው ሥራውን ለማጠናቀቅ እስከ 20 ኤክስካቫተር ቢያስፈልግም አሁን ስራ ላይ ያሉት ከ6 አይበልጡም ብለዋል። 
ጥልቀት ባለባቸውና በሰው ኃይል ማስወገድ ባልተቻለባቸው ቀበሌዎች በማሽን የታገዘ ሥራ እየተከናወነ እንደሆነም አብራርተዋል።
የእምቦጭ አረም በ3 ዞኖች፣ በ9 ወረዳዎችንና በ35 ቀበሌዎች በ4ሺህ 300 ሄክታር ላይ ተንሳፍፎ የነበረ ሲሆን 85 ከመቶው መወገዱንም ከኤጄንሲው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ዓለምነው መኮንን

ታምራት ዲንሳ