1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚኢትዮጵያ

ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮች በመጪው ምርጫ ቦታቸው የት ነው?

ረቡዕ፣ መጋቢት 29 2013

በ6ኛው የኢትዮጵያ ምርጫ ለመሳተፍ የተመዘገቡ 47 ፓርቲዎች የአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም ለሚጫነው ገበያ፣ የዋጋ ንረት፣ ሥራ አጥነትና የውጭ ምንዛሪ እጥረትን የመሳሰሉ ሥር የሰደዱ ችግሮች ለበረቱበት ኤኮኖሚ አማራጭ ፖሊሲ እንዲያቀርቡ ይጠበቃል። ሞት፣ ግጭትና መፈናቀል በበረታበት ነባራዊ ሁኔታ አማራጭ የኤኮኖሚ ፖሊሲ ምን ያህል ትኩረት ያገኛል?

https://p.dw.com/p/3rghM
Äthiopien Parlamentswahlen
ምስል Getty Images/AFP/Z. Abubeker

ከኤኮኖሚው ዓለም፦ ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮች በመጪው ምርጫ ቦታቸው የት ነው?

ምጣኔ ሐብታዊ ኹናቴዎች ዴሞክራሲ ሥር በሰደደባቸው አገራት የምርጫን ውጤት ቅርፅ ያስይዛሉ። የአንድ አገር መልካም ምጣኔ ሐብታዊ ይዞታ ለፓርቲዎች እና ፖለቲከኞቻቸው በሥልጣን የመቆየት ዕድልን ያጠናክራል። በምርጫ ዋዜማ ኤኮኖሚያዊ ዕድገት ለፖለቲከኞች በጎ ዜና ነው። የአገሩ ገበያ ዕድል ፈጥሮ የሥራ አጥ ቁጥር ሲቀንስ ሥልጣን የያዙት ዳግም የመመረጥ እና የማሸነፍ ዕድላቸው ከፍ ይላል። የተሳሳቱ ኤኮኖሚያዊ ፖሊሲዎች፣ የሚዋዥቁ እና ሥራ አጥነት የበረታባቸው ገበያዎች በተለይ በምርጫ ሰሞን ለፖለቲከኞች መልካም ዜና አይደሉም።

ዥንጉርጉሩ የኢትዮጵያ 6ኛ አገራዊ ምርጫ

በትግራይ 6ኛው አገራዊ ምርጫ አይካሔድም። በኦሮሚያ ከገዢው ፓርቲ ብርቱ ፉክክር ያደርጋሉ ተብለው ይጠበቁ የነበሩት የኦሮሞ ነፃነት ግንባር እና የኦሮሞ ፌድራላዊ ኮንግረስ እጩ ሳያስመዘግቡ ቀርተዋል። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መረጃ መሠረት 47 የፖለቲካ ፓርቲዎች 8 ሺሕ 209 እጩዎችን አስመዝግበዋል። ከ47ቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች 32ቱ በብሔር የተሰየሙ ናቸው። ሌሎች 125 ግለሰቦች በግል ይወዳደራሉ።

"በዚህ ሶስት አመት የተፈጠሩ ጉዳዮች፤ ሶስት አመቱ እንዲወለድ ያደረጉትም ምክንያቶች ከዚህ ምርጫ ጋር አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ትስስር ይኖራቸዋል። እንደየ አካባቢያችን፣ እንደየ ፖለቲካ አማራጫችን ለምርጫው ያለን የልብ ትርታ፣ ስሜት እና ተሳትፎ በዚህ ሶስት አመት ውስጥ እየተከሰቱ ባሉ ነገሮች ይወሰናል።" የሚሉት የፖለቲካ ሳይንስ መምህር እና ተመራማሪው ዶክተር ዮናስ አሽኔ 6ኛው የኢትዮጵያ አጠቃላይ ምርጫ ከቦታ ቦታ፤ ከክልል ክልል የተለያየ መልክ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

"በኦሮሚያ አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከምርጫው ስለወጡ ሰዎች በምርጫው ያላቸው ተሳትፎ አነስተኛ ሊሆን ይችላል" የሚሉት ዶክተር ዮናስ ሕዝበ-ውሳኔ በሚካሔድበት የደቡብ ክልል በአንፃሩ "ክልል ከመሆን ራስን ከማስተዳደር ጋር የተሳሰረ ስለሆነ" የመራጮች ተሳትፎ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል በምሳሌነት ይጠቅሳሉ።

Äthiopien Addis Abeba im Bau
በ6ኛው አገራዊ ምርጫ ለመሳተፍ የተመዘገቡ 47 የፖለቲካ ፓርቲዎች የአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም ለሚጫነው ገበያ፣ የዋጋ ንረት፣ ሥራ አጥነት እና የውጭ ምንዛሪ እጥረትን የመሳሰሉ ሥር የሰደዱ ችግሮች ለበረቱበት ኤኮኖሚ አማራጭ ፖሊሲ እንዲያቀርቡ ይጠበቃልምስል DW/E. Bekele

ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮች ቦታቸው የት ነው?

የኢትዮጵያ ፖለቲካ "የብሔር ጥያቄን ወደ ፊት እንወስደዋለን፤ የብሔርን ጥያቄዎች እንመልሳለን በሚሉ ፓርቲዎች የተሞላ ስለሆነ የማንነት ፖለቲካ ወሳኙ ጥያቄ ነው" የሚሉት ዶክተር ዮናስ የኤኮኖሚን ጨምሮ ሌሎች ጉዳዮች በማንነት ፖለቲካ ውስጥ ተሳስረው የሚታዩ እንደሆነ ተናግረዋል። "አሁን ያለንበት ዘመን የብሔር ፖለቲካ ጣራ ላይ የወጣበት ስለሆነ ማንኛውም ጥያቄ ከሱ ጋ ተሳስሮ ነው የሚመጣው። በእሱ ቋንቋ፣ በእሱ ሰዋስው፣ በእሱ ጽንሰ-ሐሳብ ውስጥ ነው የሚወጣው" ይላሉ ዶክተር ዮናስ።

እንደ ፖለቲከኞች እና ተንታኞች ሁሉ ነባራዊው ሁኔታ ለመጪው ምርጫ ምቹ ስለመሆኑ የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎችም ጥያቄ አላቸው። ከእነዚህ መካከል "ፖለቲካ ማለት መግባባት ማለት ነው" የሚሉት በኩዌት ሳይንሳዊ ጥናት ማዕከል የምጣኔ ሐብት ተመራማሪው ዶክተር አየለ ገላን ይገኙበታል።  ምርጫን በቅጡ ባልተዘጋጀ ሜዳ እግር ኳስ ከመጫወት እያነጻጸሩ የሚያስረዱት ዶክተር አየለ "አባጣ ጎባጣ የሆነ ጫካ እና ሳር ባለበት ኳስ ወርውረህ ጨዋታ አይጀመርም። ስምምነት ያለበት እና እንዲህ ነው የምንጫወተው ተብሎ ሜዳው ባልተስተካከለበት አገራዊ መግባባት በሌለበት ምርጫ ማካሔድ ማለት አይገባኝም።" ሲሉ ይናገራሉ።

Äthiopien | Traditioneller Markt in Debre Markos
የዋጋ ግሽበት አንገብጋቢ መፍትሔ ከሚሹ የኢትዮጵያ ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮች አንዱ መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉምስል DW/E. Bekele

ዶክተር አየለ ገላን የጠቀሱት ጉዳይ መፍትሔ ባያገኝም ኢትዮጵያ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ በማካሔድ ቆርጣለች። ከነገ ሐሙስ ጀምሮ በመገናኛ ብዙኃን አማካኝነት የምረጡኝ ቅስቀሳ ይጀመራል። የኤኮኖሚ ባለሙያው አቶ እስራኤል ወልደዮሐንስ "አሁን ያለንበት የአገሪቱ የኤኮኖሚ ኹኔታ እጅግ አሳሳቢ ከሚያደርጉት ጉዳዮች የመጀመሪያው የዋጋ ግሽበቱ ነው። ከዚያ የብር የመግዛት አቅም መዳከም (devolution) ኹኔታ አለ። በዚህ ላይ የኮሮና ቫይረስ ያመጣው ተፅዕኖ እና ትግራይን ጨምሮ በየቦታው የምንሰማቸው ግጭቶች የአገሪቱ ኤኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድረዋል።" ሲሉ ይናገራሉ።

"የምርጫ ቅስቀሳ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምን ያህል ይኸንን እንደ አጀንዳ አማራጮችን ይዘው ይቀርባሉ የሚለው ነገር ወሳኝ ነገር ነው።" የሚሉት የኤኮኖሚ ባለሙያው ከ5ኛው ጠቅላላ ምርጫ ስድስት አመታት በኋላ ኢትዮጵያውያን ካርዶቻቸውን ይዘው በመጪው ግንቦት 28 እና ሰኔ 5 ቀን 2013 ዓ.ም.  ድምጽ ለመስጠት ወደ ምርጫ ጣቢያ ሲያመሩ የጸጥታ እና የኤኮኖሚ ጉዳዮች ወሳኝ ይሆናሉ ብለው እንደሚያምኑ አስረድተዋል።

ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ