1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሽሮደር ከፓርቲያቸው ኤስ ፔዴ እንዳይባረሩ ተወሰነላቸው

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 3 2014

ከጎርጎሮሳዊው 1998 እስከ 2005 የጀርመን መራሄ መንግሥት የነበሩት ሽሮደር የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የቅርብ ወዳጅ ተደርገው ይቆጠራሉ።ራሳቸውን ከፑቱን እንዲያርቁ ከዩክሬኑ ጦርነት በኃላ ግፊቱ የተጠናከረባቸው ሽሮደር በቅርቡ ከአንድ የጀርመን የግል ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባካሄዱት ቃለ ምልልስ ራሳቸውን ከፑቲን እንደማያርቁ ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/4FL06
Bildkombo | Wladimir Putin und Gerhard Schröder
ምስል Mikhail Klimentyev/Christoph Hardt/picture alliance

ጌርሀርድ ሽሮደር ከፓርቲያቸው ኤስ ፔዴ እንዳይባረሩ ተወሰነላቸው

 

የቀድሞ የጀርመን መራሄ መንግሥት ጌርሀርድ ሽሮደር ከጀርመኑ የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ በጀርመንኛው ምህጻር ኤስ ፔዴ አባልነት እንዲባረሩ የቀረቡትን የውሳኔ ሃሳቦች ፓርቲው ውድቅ አድርጓል። ጉዳዩን ሲከታተል የቆየው የፓርቲው የሀኖቨር ቅርንጫፍ «ጥፋት አላገኘሁባቸውም» ሲል ሽሮደር በአባልነት እንዲቀጥሉ ትናንት ወስኗል።ውሳኔውና አንድምታው የዛሬው አውሮጳና ጀርመን ዝግጅታችን የሚያስቃኘን ጉዳይ ነው። ኂሩት መለሰ አዘጋጅታዋለች።የቀድሞ የጀርመን መራኄ መንግሥት ጌርሀርድ  

የቀድሞ የጀርመን መራኄ መንግሥት ጌርሀርድ ሽሮደር ከሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ባላቸው ግንኙነት ምክንያት 60 ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ በአባልነት ከቆዩበት የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ በምህጻሩ ኤስ ፔዴ እንዲባረሩ  ጥያቄ መቅረብ የጀመረው ከዛሬ አምስት ወር ወዲህ ነው። በዚህ ዓመት በየካቲት ወር ሩስያ ዩክሬንን ከወረረች በኃላ የ78 ዓመቱ ሽሮደር ከፑቲን ጋር ወዳጅነታቸው ባለመቋረጡ እና የሩስያ መንግሥት ለሚያስተዳድራቸው ኩባንያዎች መስራታቸው

ክፉኛ ሲያስተቻቸው የቆየ ጉዳይ ነበር። በሂደትም የመሀል ግራ አቋም የሚያራምደው የጀርመኑ ኤስፔዴ ፓርቲ የአካባቢና የክልል  አካላት ሽሮደር ከፓርቲው እንዲባረሩ የሚጠይቁ 17 የውሳኔ ሀሰቦችን ካቀረቡ በኋላ ክሱ በሐምሌ ወር መስማት ጀመረ። ጉዳዩን ሲከታተል የቆየው፣ ሽሮደር ለፓርቲው አባልነት የተመዘገቡበት የሰሜን ጀርመኑ የሀኖቨር ከተማ የፓርቲው ቅርንጫፍ ትናንት ባሳለፈው ውሳኔ፣ «ከሩስያ መንግሥት ኩባንያዎች ጋር በመስራታቸውም የፓርቲውን ህግጋት ጥሰዋል ተብለው የተከሰሱት ሽሮደር ጥፋተኛ አይደሉም ማስረጃ የተገኘለት የደንብ ጥሰትም የለም ሲል ወስኗል። የበርሊኑ ወኪላችን ይልማ ኃይለ ሚካኤል እንደሚለው  የኤስ ፔዴ አባላት ሽሮደር ለ60 ዓመታት ከቆዩበት ፓርቲያቸው እንዲባረሩ የጠየቁበት ምክንያት በሩስያ ላይ የሚከተሉት የፖለቲካ መርሀቸው ነው።  ይልማ እንደሚለው የሽሮደር ከሳሾች በጉዳዩ ላይ የውሳኔ ሀሳብ ይዘው የቀረቡበት ሌላም ዋነኛ  ምክንያት  አላቸው።

Schröder und Putin Umarmung
ምስል Yuri Kochetkov/epa/dpa/picture-alliance

የዩክሬኑ ጦርነት በተጀመረ በሳምንቱ ሽሮደር ከፑቲንና ከሩስያ ጋር ባላቸው ግንኙነት ምክንያት ስራ አስኪያጃቸውን ጨምሮ ሌሎች ሰራተኞቻቸው ስራቸውን ለቀዋል። ይህ በሆነ በሳምንቱ የሀገሪቱ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የሩስያ መንግሥት በሚቆጣጣጣራቸው ኩባንያዎች ውስጥ ባላቸው ሚና ሰበብ በሰብዓዊነት ላይ በተፈጸመ ወንጀል ውስጥ በመተባበር በሚል ተያያዥ የክስ ሂደት ተጀመረ ። የዚያኑ እለት ፓርቲያቸው እርሳቸውን ከአባልነት ለማባረር መንቀሳቀስ ጀመረ።ከዚህ በተጨማሪም እህትማማቾቹ የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረትና የክርስቲያን ሶሻል ኅብረት ፓርቲዎች የአውሮጳ ኅብረት ማዕቀብ ከፑቲን መንግሥት ጋር ባላቸው ግንኙነት ሰበብ ማዕቀብ ከጣለባቸው ግለሰቦች ውስጥ ሽሮደርም እንዲካተቱ ጠይቀው ነበር። ሆኖም ከፑቲን ጋር ባላቸው ቅርበት ሰበብ የተገለሉትና የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞቻቸውንም የተነፈጉት ሽሮደር ከፓርቲው እንዲባረሩ የሚያደርግ  መሠረት የለም ብሏል በሰሜን ጀርመኗ ከተማ ሀኖቨር የሚገኘው ጉዳያቸውን የተመለከተው ኮሚቴው። ውሳኔ ላይ በሁለት ሳምንት ውስጥ አቤት ማለት ይቻላል። ሽሮደር በኮሚቴው የከዚህ ቀደም  ሂደቶች ላይ አልተገኙም፤  ጠበቃም አልላኩም። ከጎርጎሮሳዊው 1998 እስከ 2005 ድረስ የጀርመን መራሄ መንግሥት የነበሩት ሽሮደር የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የቅርብ ወዳጅ ተደርገውም ይቆጠራሉ። ራሳቸውን ከፑቲን እንዲያርቁ ከዩክሬኑ ጦርነት በኃላ ግፊቱ የተጠናከረባቸው ሽሮደር ሮዝኔፍት ከተባለው የሩስያ ግዙፍ የኃይል አመንጪና አምራች ኩባንያ  የበላይ ተቆጣጣሪ ቦርድ እንደሚለቁ ባለፈው ግንቦት አስታውቀው ነበር።ለጋዝፕሮም የታጩበትን ተመሳሳይ ሃላፊነትም ሳይቀበሉ ቀርተዋል።ሆኖም በቅርቡ አር ቴ ኤል ከተባለው የጀርመን የግል ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ  ራሳቸውን ከፑቲን እንደማያርቁ ተናግረዋል።ከዚህ ሌላ ከዩክሬኑ ጦርነት በኋላ የታገደው አወዛጋቢው ኖርድ ስትሪም 2 የተባለው ከሩስያ ወደ አውሮጳ ጋዝ የሚያስተላልፈው መስመር ፕሮጀክት ስራ እንዲቀጥልም ሃሳብ አቅርበው ነበር።

Gerhard Schöder
ምስል Christoph Hardt/Geisler-Fotopress/picture alliance

ኂሩት መለሰ

እሸቴ በቀለ