1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢዳይ ማዕበል ያስከተለው ጉዳት

ዓርብ፣ መጋቢት 13 2011

የሞዛምቢካን የወደብ ከተማ አጥለቅልቆ ወደ ዚምባቡዌ የተዛመተው የባሕር ማዕበል ያስከተለው ከባድ ዝናብ እና ጎርፍ ያስለከተለው ጉዳት የደቡብዊ አፍሪቃ ሃገራት ችግር ውስጥ ከቷል።  በአካባቢው ታሪክ ከፍተኛ ጉዳት እንዳስከተለ የተነገረለት ኢዳይ የተባለው ማዕበል ያመጣው ጎርፍ የማዕከላዊ ሞዛምቢክ መንደሮችን ቤቶች እና መላ ከተሞች አጥለቅልቋል።

https://p.dw.com/p/3FVGv
Mosambik Zyklon Idai | Zerstörung und Hilfe
ምስል Reuters/S. Sibeko

«የሟቾች ቁጥር እየጨመረ ነው»

 ከአካባቢው ሰዎችን ሄሊኮፕተር የማውጣቱ ተግባር የቀጠለ ሲሆን የምግብ እና የመድኃኒት ርዳታም ወደ ስፍራው እየተላከ ነው። የሟቾች ቁጥር እየጨመረ፤ የገቡበት ያልታወቀ ሰዎችም መኖራቸው ተገልጿል።

ለሁለት ሣምንታት ገደማ የደቡባዊ አፍሪቃን ሦስት ሃገራት ያስጨነቀው ኢዳይ ማዕበል ያስከተለው ጉዳት ከባድ ነው። ሞዛምቢክ ውስጥ የሟቾች ቁጥር 217 ደርሷል፤ ዚምባቡዌ 139። ማላዊ ደግሞ 39 ዜጎቿ ማዕበሉ ባስከተለው ጎርፍ መሞታቸውን አረጋግጣለች። ለጉዳቱ ሰለባዎች ምግብ ከአየር የሚወረውረው የዓለም የምግብ ድርጅት 200 ሺህ የዚምባቡዌ ዜጎች ለቀጣይ ሦስት ወራት የምግብ ርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው አስታውቋል። 15 ሺህ ሕዝብ ደግሞ ሞዛምቢክ ውስጥ አፋጣኝ ሕክምና ፈላጊ ነው። በስተደቡብ አፍሪቃ በሕንድ ውቅያኖስ ላይ ባለፈው የካቲት ወር መገባደጃ የተከሰተው ማዕበል በክፍለ ዓለም አፍሪቃ የታየ ከባድ ውድመት ያስከተለ ማዕበል በሚል ተመዝግቧል።  የረድኤት ድርጅቶችም ላለፉት 20 ዓመታት ያላጋጠመ የተፈጥሮ አደጋ ብለውታል። ዛሬ ከሰሞኑ ቀናት ዝናቡ ተግ ብሎ በመዋሉ የዕለት ደራሽ ርዳታ አቅራቢዎች በተሻለ ሲንቀሳቀሱ መዋላቸው ተዘግቧል። በአየር ጠባይ ትንበያው መሠረት ግን ዝናቡ እስከ መጪው ማክሰኞ ሊቀጥል እንደሚችል ይጠበቃል።

Mosambik Beira Zyklon Sturm  Idai
ምስል picture-alliance/AP Photo/D. Onyodi

ማዕበሉ ጉዳት ካደረሰባቸው የደቡብ አፍሪቃ ሃገራት በተለይ የሞዛምቢክ የወደብ ከተማ በይራ ጎርፉ የመሬት መናድ ሁሉ አስከትሎባታል። በዚህ ምክንያት የሕይወት አድን ሠራተኞች የሟቾች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ስጋታቸውን እየገለፁ ነው። ጎርፉ አካባቢውን ሲያስጠቀልቅ ሰኞ ዕለት የሀገሪቱ ፕሬዝደንት ፊሊፐ ናዩሲ 500 ሺህ ሕዝብ የሚኖርባት ባይራ ከተማንበሄሊኮፕተር ከቃኙ በኋላ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን እና ሰለባዎችም እጅግ ሊበረክቱ እንደሚችሉ አስጠንቅቀው ነበር። እስካሁንም በሞዛምቢክ የሟቾቹ ትክክለኛ ቁጥር እንዳልተገኘ ነው የሚነገረው። እስካሁንም ዝናቡ የቀጠለው ዝናብ የህክምና ርዳታውን እያስተጓጎለ በመሆኑ በጎርፍ የተከበቡትን ሰዎች የማዳኑን ሥራ አወሳስቦታል።  ነዋሪዎቿ በጎርፍ የተጥለቀለቀው አካባቢያቸው የሚጠጉበት እንዳሳጣቸው ይናገራሉ።

«ቤቴ ሙሉ ለሙሉ ወድሟል፤ ንብረቴን አጥቻለሁ፤ የልብስ ማጠቢያው ማሽን፣ ቴሌቪዥኑ፣ የሙዚቃ ማጫወቻው፣ ወንበሮች፣ ሌላው ቀርቶ አልጋ እና ፍራሼ ሁሉ ተጠራርጎ ሄዷል። የት እንደምተኛ አላውቅም፣ ትናንት በአቅራቢያው ባሉ ሰዎች ቤት አደርኩ፤ ሆኖም ሌሊቱን ጎርፍ ነበር፤ በዚህ ምክንያትም መተኛት አልቻልንም።»

Mosambik Zyklon Idai | Zerstörung und Hilfe
ምስል Reuters/Josh Estey/Care International

በሞዛምቢክ የሕፃናት አድን ድርጅት ባልደረባ ዳይዚ ሲቶይ የወደብ ከተማዋ አብዛኛው ክፍል እንዳልነበረ መሆኑን ይናገራሉ።

«ባለን መረጃ መሠረት 90 በመቶ የሚሆነው የከተማዋ ክፍል ወድሟል። መንገዶቹ የማያንቀሳቅሱ ሆነዋል። ወደከማዋ ለመግባት አዳጋች ነው። ወደ ሶፋላ ክፍለ ሀገር ለመግባት ያለው ብቸኛ መንገድ በአየር ወይም በባሕር መጓዝ ብቻ ነው።»

በዚያም ላይ የስልክ እና ኢንተርኔት መገናኛዎች ከጥቅም ውጭ ሆነዋል። ጎረቤት ዚምባቡዌም ማበሉ ባስከተለው ጎርፍ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባታል። 30 ሺህ ነዋሪ እንዳላት የተነገረው ቺማኒማኒ የተባለችው ከተማ የባሕር ማዕበሉ በቀጥታ ያጠቃት ግዛት ናት። የDW ዘጋቢ ፕሪቪሌጅ ሙስቫንሂሪ በመሬት መናድ ምክንያት ቤታቸው የፈረሰ የ83 ዓመት አዛውንት ሥርዓተ ቀብር ላይ ተገኝቷል። የከተማዋ ነዋሪዎችም ልጆቻቸው ትምህርት ቤት መሄድ እንዳልቻሉ እና እነሱም በጎርፍ የተጥለቀለቀ አካባቢያቸውን እያዩ ከመተከዝ በቀር ምንም ማድረግ እንዳልቻሉ ተናግረዋል። ድልድዮች በጎርፍ በመወሰዳቸው እና በመፈራረሳቸው ምክንያትም አስቸኳይ ርዳታ እንደሚያሻቸውም ያሳስባሉ። ድንበር የለሽ የሃኪሞች ቡድን በአካባቢው የህክምና ርዳታ፣ የመጠጥ ውኃ እና የንፅሕና መጠበቂያ ስልቶችን ለማዳረስ እየጣረ መሆኑን አመልክቷል።

Mosambik Wirbelsturm Idai
ምስል Getty Images/AFP/M. Vermaak

ማዕበሉ በቀጥታ ባያገኛትም ማላዊም ያስከተለው ዝናብ ወንዞቿን ከገደብ እንዲያልፉ አድርጎባታል። በተለይም በጎርፍ ክፉኛ ወደተጎዳችው ማክሃንጋ ከተማ አንድም በጀልባ ወይም በሄሊኮፕተር ብቻ ነው ሊደረስባት የሚችለው። በሺህዎች የሚቆጠሩት ነዋሪዎቿ ከአደጋው ለማምመለጥ ቤታቸውን ትተው ወደ አጎራባች ሃገራት ሸሽተዋል። በየጊዜው በማዕበል እና ጎርፍ የምትጠቃው ማዳጋስካር ከዚህኛው አደጋ ተርፋለች። የሀገሪቱ የአአካባቢ ግንኙነት ሚኒስትር ሃጆ ሂሪቫሎና አንድሪአናይናሪቬሎ በሕንድ ውቅያኖስ ዳርቻ የሚገኙ ሃገራት በአየር ንብረት ለውጥ መዘዝ ለሚከተሉ የተፈጥሮ አደጋዎች የተጋለጡ በመሆናቸው ብሔራዊ የተፈጥሮ አደጋ መቋቋሚያ ስልት ሊኖራቸው እንደሚገባ አመልክተዋል። በዚህ የተፈጥሮ አደጋ ክፉኛ ለተጎዱት ሦስቱ ሃገራት ደቡብ አፍሪቃ ሕይወት ለማዳን ተግባር ወታደሮቿን ስታሰማራ፣ ታንዛኒያ የምግብ እና መድኃኒት ርዳታ አቅርባለች። በዛሬው ዕለትም ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ርዳታ ወደየሃገራቱ እየገባ መሆኑ ተገልጿል።

ሸዋዬ ለገሠ /ፊሊፕ ዛንድነር

አዜብ ታደሰ