1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢዜማ፤ አብንና ጀዋር፤ የአሜሪካን አቋም ተቃወሙ

ሰኞ፣ የካቲት 23 2012

ኢዜማ የአሜሪካን መግለጫ «ኢትዮጵያ ሳትሳተፍበት የተፈጸሙ የቅኝ ግዛት ጊዜ ስምምነቶችን የሚያስታውስ» ሲል አብን በበኩሉ «ያልተጠበቀና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የተዳፈረ» ብሎታል። አቶ ጀዋር መሐመድ ድርድሩ ነሐሴ 23 ቀጠሮ ከተያዘለት ምርጫ በኋላ እንዲቀጥል ጠይቀዋል። 98 ቢሊዮን ብር ገደማ የወጣበት ግድብ ድርድር መቼ እንደሚቀጥል አልታወቀም

https://p.dw.com/p/3YgwO
Karte Grand-Ethiopian-Renaissance-Talsperre DE

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ፤ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ እና በቅርቡ የኦሮሞ ፌድራሊትስት ኮንግረስን የተቀላቀሉት ፖለቲከኛው ጀዋር መሐመድ በታላቁየኅዳሴ ግድብ ድርድር ጉዳይ አሜሪካ የተከተለችውን አቋም ነቀፉ።

የአሜሪካ ግምዣ ቤት ባለፈው የካቲት 19 እና 20 ቀን 2012 ዓ.ም ኢትዮጵያ ያልተሳተፈችበት የግድቡ ውይይት ከተካሔደ በኋላ «ሥምምነት ሳይፈረም የታላቁ የኅዳሴ ግድብ የመጨረሻ ሙከራ እና የውኃ ሙሌት ሊከናወን አይገባም» ሲል ያወጣው መግለጫ በርካታ የአገሪቱ ዜጎችን አስቆጥቷል።

የውጭ ጉዳይ ምኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የአሜሪካ መንግሥት ያወጣው መግለጫ "ተቀባይነት የሌለው እና እጅጉን ለአንድ ወገን ያደላ ነው" ሲሉ ኮንነዋል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትኅ ፓርቲ በበኩሉ መግለጫው «ሦስቱ ሀገራት አስቀድመው የደረሱበትን የፍትሃዊ ተጠቃሚነት መርህ ከግምት ውስጥ ያላስገባ እና ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ሳትሳተፍበት የተፈጸሙ የቅኝ ግዛት ጊዜ ስምምነቶችን የሚያስታውስ» ብሎታል።

ፓርቲው አዲስ አበባ፣ ካይሮ፣ ኻርቱም እና ዋሽንግተን ዲሲ የተደረጉ ድርድሮችን በታዛቢነት የተቀላቀለችው አሜሪካ በስተመጨረሻ ያወጣችው መግለጫ «የኢትዮጵያን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ከግምት ያላስገባ ጫና በሀገራዊ ሉዓላዊነታችን እና ጥቅማችን ላይ የሚሰነዘር ጥቃት» ሲል አሳሳቢነቱን ገልጿል።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የአሜሪካን መግለጫ «ያልተጠበቀና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የተዳፈረ» ብሎታል። አብን የኢትዮጵያ «የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የሰጠውን ምላሽ የምናደንቅ ሲሆን ፓርቲያችን በእንዲህ አይነቱ ሃገራዊ ጉዳይ ከምንግዜም በላይ ከመንግሥት ጎን እንቆማለን» ብሏል። 

በቅርቡ የኦሮሞ ፌድራሊስት ኮንግረስን የተቀላቀሉት አቶ ጀዋር መሐመድ በበኩላቸው አሜሪካውያን ለኢትዮጵያ የሰጧቸውን ብድሮች እና በመጪው ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ይካሔዳል ተብሎ የሚጠበቀውን ምርጫ በጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ላይ ጫና ለማሳደር እንደመሳሪያ እየተጠቀሙ ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ምኒስትሩ ከአሜሪካ በኩል የሚደርስባቸውን ጫና ሊቋቋሙ ይገባል ያሉት አቶ ጀዋር በግል የፌስቡክ ገፃቸው ባሰፈሩት አጭር መልዕክት ድርድሩ ከምርጫው በኋላ እንዲቀጥል ሐሳብ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያን ከግብፅ ያቃቃረው እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጉባ በተባለ ቦታ እየተገነባ የሚገኘው ታላቁ የኅዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ ዘጠኝ አመታት ገደማ ሆኖታል። 

የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚህ ቀደም ብረታ ብረት እና ኢንጂኔሪንግ ኮርፖሬሽን ተብሎ ይጠራ ለነበረው የመከላከያ ሰራዊት ኩባንያ የተሰጡ የኤሌክሮ ሜካኒካል ሥራዎችን በመንጠቅ ለጣሊያን፣ ፈረንሳይ እና ጀርመን ኩባንያዎች ሰጥቷል።

ግንባታው ሲጀመር በ80 ቢሊዮን ብር ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረ ቢሆንም እስካለፈው ታኅሳስ 2011 ዓ.ም. ድረስ ብቻ 98 ቢሊዮን ብር ወጪ እንደሆነበት የኣኢትዮጵያ መንግሥት አስታውቋል። በግድቡ አስተዳደር እና የውኃ ሙሌት ጉዳይ ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን የሚያደርጉት ድርድር ከዚህ በኋላ እንዴት እንደሚቀጥል በይፋ የታወቀ ነገር የለም።

ባለፈው ጥር የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ በታላቁ የኅዳሴ ግድብ ጉዳይ ኢትዮጵያና ግብፅን እንዲያሸማግሉ ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጠይቀዋል።