1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያውያን ድርጅቶች የተሳተፉበት ዓውደ ርዕይ በጀርመን

ሐሙስ፣ መስከረም 29 2012

የአኑጋ የምግብ እና የመጠጥ አውደ-ርዕይ በጀርመን የኮሎኝ ከተማ በየሁለት ዓመቱ ይካሄዳል። የዘንድሮው አውደ ርዕይን ለየት የሚያደርገው አኑጋ 100ኛ ዓመቱን ያከበረበትም ነበር። ለአምስት ቀናት የዘለቀው እና ትናንት የተጠናቀቀው አውደ ርዕይ ላይ ከ107 ሃገራት የመጡ ድርጅቶች ምርታቸውን ለማስተዋወቅ ችለዋል። በርካታ ኢትዮጵያውያንም ተሳትፈዋል።

https://p.dw.com/p/3R28i
Deutschland Messe Anuga  in Köln Äthiopische Aussteller
ምስል DW/D. Adugna

ኢትዮጵያውያን ድርጅቶች የተሳተፉበት ዓውደ ርዕይ በጀርመን

የኢትዮጵያ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የንግድ ጥናት እና ማስፋፊያ ዳሬክቶሬት ዳሬክተር ወይዘሮ ሃይማኖት ጥበቡ « በጀርመን ገበያም ሆነ በተለያዩ ሀገራት የምንልካቸውን ምርቶችን ይዘን ነው የመጣነው» ይላሉ። 60 ካሬ ሜትር ስፋት ባለው ቦታ ላይ የጤፍ፣ የቅማቅመም፣ ቡና እና የቅባት ምርቶች ተዋውቀዋል። በዚህ የአኑጋ አውደ ርዕስ ላይ ከኢትዮጵያ 15 የሚጠጉ ድርጅቶች የማኅበራት ተወካዮች እንዲሁም ኃላፊዎች ተገኝተዋል። ከነዚህም መካከል ዳንኤል አዱኛ የሚሠሩበት የክሮታች ጣህኒ ድርጅት አንዱ ነው። ጣህኒ ከሰሊጥ የሚመረት የምግብ ዓይነት ሲሆን በብዛት በአረብ ሀገሮች በአሜሪካ እና አውሮፓ « ሁሙስ፣ ሀልቫ እና የሰላጣ ቅመሞችን ለመስራት ያገለግላል » ይላሉ ዳንኤል።

Deutschland Messe Anuga  in Köln Äthiopische Aussteller
ምስል DW/D. Adugna

የኢትዮጵያ ቡና  በመጠጥ ደረጃ  ከኢትዮጵያ የተሳተፉ ድርጅቶች ይዘውት የቀረቡት ብቸኛው የመጠጥ አይነትም ነበር። የጌቱ ተፈራ ቡና እና የቅባት እህሎች አስመጪ እና ላኪ እንደገለፁልን የኢትዮጵያን ቡና፣ የአፈላል ስነ ስርዓቱን ጨምሮ ለማስተዋወቅ ቢሞክሩም በቦታ ምክንያት የጠበቁትን ያህል ትኩረት አላገኘም። « የተያዘልን ቦታ ገዢዎች በቀላሉ ሊያገኙን የሚችሉበት ድብቅ ቦታ ነበር» ይላሉ።

የአኑጋ አውደ ርዕይ ላይ ነባር ከሆኑ ምርቶች ይልቅ አዳዲስ ምርቶች የሚተዋወቁበት መድረክ ነው። ዘመን አመጣሹ ምግብ እና መጠጥ በተፈጥሮ ሂደት የተመረቱ የምግብ እና የመጠጥ አይነቶች (የBIO ምርቶች) ሲሆኑ ከዚህም ሌላ ከጥራጥሬዎች ስጋን አስመስሎ የተሰሩ ምግቦች ተዋውቀዋል። ከእንስሳት ተዋፅዖ ውጪ የሆኑ የፆም የምንላቸው ምግቦችም በቂ መድረክ አግኝተዋል። ይሁንና በዚህ አውደ ርዕስ ላይ ከተዋወቁት ዓለም አቀፋዊ ምርቶች ምን ያህሉ በእየመደብሮች ለመሸጥ እንደሚበቁ ከሳምንት እና ከወራት በኋላ የሚታይ ይሆናል።

እንደ የጀርመን የምግብ እና መጠጥ ኢንዱስትሪ ማኅበር ከሆነ በእያመቱ 40,000 የሚጠጉ አዳዲስ የምግብ አይነቶች በገበያ ላይ ይውላሉ። ቁጥራቸው ተመሳሳይ የሆኑ እና ብዙ ሸማቾች ያላገኙ ምርቶችም ከገበያ ይወጣሉ። ይህ ለክሮታች ጣህኒ ድርጅት ጥሩ አጋጣሚ ነው። « ሰሊጥ እንደዚህ ተፈጭቶ አይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ተጠቃሚዎች አሉት። ይሁንና ዋና ኢላማችን የኢትዮጵያ ገበያ ሳይሆን የውጭ ገበያ ነው። ወደ ውጭ ልከን ለሀገራችን የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ነው አላማችን።» ይላሉ ዳንኤል አዱኛ ።በዚህ በአኑጋ አውደ ርዕይ በዓለም አቀፍ ደረጃ 7,500 የሚጠጉ ድርጅቶች ምርቶቻቸውን አቅርበዋል።

Deutschland Messe Anuga  in Köln Äthiopische Aussteller
ምስል DW/D. Adugna

ሌላው ከኢትዮጵያ ምርታቸውን ያስተዋወቁት አዲሱ አለማየሁ ናቸው።ወክለው የመጡት ድርጅት የኢትዮጵያ የቅማቅመም ማዓዛማና ሀመልማላማ አምራቾች እና አቀነባባሪዎች ማኅበር ነው። እሳቸውም የማኅበሩም መስራች እና ሥራ አስኪያጅ ናቸው። ይዘው የቀረቧቸው ጠቅላላ ቅመማ ቅመሞች ኢትዮጵያ ውስጥ ምግብ የሚሠራባቸው ናቸው። እርድ፣ ዝንጅብል፣ኮሰረት፣ ኮረሪማ በርበሬ ጥቂቶቹ ናቸው። ማህበሩ በዚህ አውደ ርዕስ ሲሳተፍ ይህ የመጀመሪያው ነው።« ከዚህ በፊት እነዚህ ቅመማ ቅመሞች የኢትዮጵያን ባህላዊ ምግቦች በአነባበሮ እና በእንጀራ ላይ እያደረግን እንዲቀምሱ እና እንዲያጣጥሙ እናደርግ ነበር በዚህ አውደ ርዕይ ላይ ስንሳተፍ የመጀመሪያ ጊዜያችን ስለነበር በዚህ መልክ ተዘጋጅተን አልመጣንም። ለመጀመሪያ ተሳትፎዋችን ግን ያገኘነው ምላሽ ጥሩ ነበር» ይላሉ  አዲሱ አለማየሁ ።

Deutschland Messe Anuga  in Köln Äthiopische Aussteller
ምስል DW/D. Adugna

165,000 ከሚጠጉ እና ከ 198 ሀገራት ከመጡ ጎብኝዎች አንዱ የአዲስ አበባ ነዋሪ አሜን ሰለሞን ነው። « ኢትዮጵያን ከመላው ሀገሮች አንዷ ሆና በዚህ ትልቅ የንግድ አውደ ርዕይ ላይ የራሷን ምርቶች ይዛ መቅረቧ ደስ የሚል ነገር ነው። ብሏል።

 

ልደት አበበ

ማንተፋፍቶት ስለሺ