1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያውያን በኬንያ እና ታንዛንያ እስር ቤቶች

ዓርብ፣ ግንቦት 26 2014

በኬኒያ እና ታንዛኒያ በሚገኙ እሥር ቤቶች በሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ተገቢ ባልሆነ አያያዝ እየተሰቃዩ እንደሚገኙ ትናንት በኢትዮጵያ ሞያሌ በኩል ወደ አገር የገቡ ተመላሾች ገለፁ፡፡

https://p.dw.com/p/4CGUP
Äthiopische Flüchtlinge kehren aus Kenia zurück
ምስል Tariku Bezabehi/SNNPR workers and social affairs Bureau

ከስደት የተመለሱት እማኝነት

በኬኒያ እና ታንዛኒያ በሚገኙ እሥር ቤቶች በሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ተገቢ ባልሆነ አያያዝ እየተሰቃዩ እንደሚገኙ ትናንት በኢትዮጵያ ሞያሌ በኩል ወደ አገር የገቡ ተመላሾች ገለፁ፡፡ የእሥር ጊዚያቸውን አጠናቀው ወደ አገር ቤት ከገቡት ከ200 በላይ ተመላሾች መካከል ዶቼ ቬለ DW ያነጋገራቸው እንዳሉት ቁጥራቸው የበዛ ኢትዮጵያውያን አሁንም በተጠቀሱት ሃገራት በሚገኙ እሥር ቤቶች በሥቃይና በእንግልት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ የፌደራሉ መንግሥት በበኩሉ በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ኬኒያ እና ታንዛኒያ በመግባታቸው በእሥር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እንዲለቀቁ ለማድረግ ከየሃገራቱ መንግሥታት ጋር እየሠራ  እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

Äthiopische Flüchtlinge kehren aus Kenia zurück
አቶ ታሪኩ በዛብህ ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የሞያሌ ኬኒያ መስመር ኢትዮጵያውያን ከሚሰደዱባቸው የፍልሰት መስመሮች መካከል ከቀዳሚዎቹ ተርታ ይመደባል፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በዚህ መስመር  ደቡብ አፍሪካ ለመግባት አስበው የፍልሰት ጉዞ ከሚያደርጉት አብዛኞቹ በደቡብ ክልል ከሃድያ ፣ ከከንባታ እና ጠምባሮ ዞኖች የሚነሱ ወጣቶች ናቸው፡፡ በእርግጥ ጥቂቶች በመዳረሻነት ወደ አለሙት  ደቡብ አፍሪካ ቢገቡም አብዛኞቹ ግን ከሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪ በመሆኑ በፀጥታ አስከባሪዎች ተይዘው በየእስር ቤቱ የተወረወሩም  ቁጥራቸው የትየሌሌ ነው፡፡ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመግባት በመሸጋገሪያነት በሚጠቀሙባቸው የኬንያና ታንዛኒያ አገራት ተይዘው በእሥር ላይ የቆዩ ከ200 በላይ ኢትዮጵያውያን ትናንት በኬንያ ሞያሌ በኩል ወደ አገራቸው ገብተዋል፡፡ በእሥር ቆየታቸው ለሰው ልጆች የማይገባ ያሉትን ስቃይ ማየታቸውንም ለዶቼ ቬለ DW  ተናግረዋል፡፡ ከስደት ተመላሾቹ ወደ አገራቸው በመግባታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ቢናገሩም አሁንም በሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በየእሥር ቤቱ በስቃይና በእንግልት ውስጥ ይገኛሉ ብለዋል፡፡ አቶ ታሪኩ በዛብህ የአብዛኞቹ ፍልሰተኞች መነሻ የሆነው የደቡብ ክልል ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሥራ ሥምሪትና ማስፋፊያ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ናቸው ፡፡

Äthiopische Flüchtlinge kehren aus Kenia zurück
ከስደት የተመለሱት ኢትዮጵያውያንምስል Tariku Bezabehi/SNNPR workers and social affairs Bureau

በየሳምንቱ በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በሞያሌ ኬንያ መስመር ወደ አገራቸው እየገቡ መሆኑን የሚናገሩት ዳይሬክተሩ በመሸጋገሪያ ሃገራት ተይዘው በእስር ቤቶች ያሉ ቀሪ ዜጎችን ለማስለቀቅ በፌዴራሉ መንግሥቱ በኩል ተጨማሪ ጥረቶች ሊደረጉ ይገባል ይላሉ፡፡ ዶቼ ቬሌ DW በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች መከታተያ ኮሚሽንንም ሆነ የኢፊዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ለማነጋገር ያደረገው ሙከራ ሊሳካ አልቻለም፡፡ ይሁን እንጂ ሰሞኑን በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደጉት የታንዛንያው ፖሊስ አዛዥ ጄኔራል ሲሞን ኞኮሮ በታንዛንያ እሥር ቤቶች የሚገኙ ኢትዮጵያንን ጉዳይ በተለየ ሁኔታ ለማየት የሚያስችላቸውን ሥምምነት ከኢፊድሪ ፖሊስ ኮሚሽን ጄኔራል ደመላሽ ወ/ሚካኤል ጋር መፈራረማቸውን የመንግሥት የመገናኛ አወታሮች ዘግበዋል፡፡ በቅርቡ በፌዴራል ፖሊስ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር  መከላከል ቡድን ወደ ታንዛኒያ በመጓዝ ዜጎች ከእሥር ተፈተው ወደ አገራቸው የሚመጡበትን ሁኔታ እንደሚያመቻች ኮሚሽንር ጄነራል ደምላሽ በዚሁ ጊዜ ተናግረዋል፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ