1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያዊዉ የፎቶግራፍ ባለሞያ በደቡብ ኮርያ

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 15 2012

ደቡብ ኮርያ ሃገር እንደ ኢትዮጵያዊነት ቀና ብለን የምንሄድበት ትልቁ ነገር የሁለቱ ሃገራት ታሪክ ነዉ። በ1950 ዎቹ በነበረዉ የኮርያዉያን ጦርነት፤ የኢትዮጵያ የቃኘዉ ሻለቃ ጦር በመሳተፉ፤ አሁን በጣም ትልቅ ቦታ ትልቅ ክብር እንዲሰጠን አስችሎአል። በጦርነቱ ብቻ ሳይሆን በሰላም ማስጠበቁ ሂደት ከ 6 ሺህ በላይ የኢትዮጵያ ተሳትፈዋል።

https://p.dw.com/p/3bKYI
Berkete Alemayehu  Fotokünstler aus Äthiopien in Südkorea
ምስል privat

የሁለቱ ሃገራት ታሪክ እንደ ኢትዮጵያዊ ቀና ብለን የምንሄድበት ትልቁ ነገር ነዉ

 

በረከት አለማየሁ ይባላል። በደቡብ ኮርያ ሶኡል ከተማ መኖር ከጀመረ አምስት ዓመት እንዳለፈዉ ይናገራል። በያዝነዉ 2012 ዓመት ፤ ሚያዝያ ወር መጀመርያ ላይ በሃገሪቱ በተካሄደዉ የፓርላማ ምርጫ በሶኡል ከተማ ለፓርላማ የግል ተወዳዳሪ እጩ ለነበረችዉ ሺንጂዬ የተባለች ዜጋን በመደገፍ አደባባይ ወጥቶ ድጋፉን ሰጥቶአል።

Berkete Alemayehu  Fotokünstler aus Äthiopien in Südkorea
ምስል privat

«ወደ ደቡብ ኮርያ ከመመጣሁ ባለፈዉ መስከረም ወር አምስት ዓመት አለፈኝ። ሶኡል ከተማ ነዉ የምኖረዉ። ኮርያ ከመምጣቴ በፊት አራት ሃገሮችን አይቻለሁ። አፍሪቃ ዉስጥ ሁለት ሃገራት ነበርኩ። በእስያ ደግሞ ሕንድ እና ታይላንድን ነበርኩ። ኮርያ በጣም የሰለጠነ ሃገር ነዉ። ቴክኖሎጂዉ ፤ መሰረተ ልማቱ በጣም የረቀቀ ነዉ።

ደቡብ ኮርያ ዉስጥ ብዙ አፍሪቃዉያን አሉ?

«አፍሪቃዉያን ብዙ አይደለንም ። ግን ኮርያ ከ 2.5 ሚሊዮን በላይ የዉጭ ሃገር ሕዝብ የሚኖርበትም ሃገር ነዉ። አብዛኛዉን ምዕራባዉያን ይኖራሉ። እስያዉያንም ይኖራሉ። ብዙ ኮርያዉያን በተለይ ከእስያ ሃገር ዜጎች ጋር እንደ ታይላንድ ካሉ ዜጎች ጋር ተጋብተዋል።»

ከሁለት የአፍሪቃ ሃገራት በቀር አብዛኛ የዓለም ሃገራት የያዙትን የምርጫ ቀነ ቀጠሮ በወቅቱ በተከሰተዉ የኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የምርጫ ቀንን ሰርዘዋል ወይ አራዝመዋል። ደቡብ ኮርያ ግን በወረርሽኝ ወቅት የምክር ቤት ምርጫን ያካሄደች የመጀመርያ ሃገር ናት። በደቡብ ኮርያ ወረርሽኝ በጀመረበት በቀዉጢዉ ወቅት፤ ኢትዮጵያዊዉ በረከት አለማየሁ ለምረጡኝ ዘመቻ ለአንዲት የደቡብ ኮርያ የፓርላማ እጩ ድጋፍ ለመስጠት በአደባባይ የወጣዉ ከኢትዮጵያ ጀምሮ ይዞት የሄደዉ የፎቶግራፍ ጥበብን በማሳደግ በደቡብ ኮርያ የተለያዩ የፎቶ ኤግዚቢሽን በማዘጋጀት እዉቅናን ስላተረፈ፤ በሌላ በኩል በማያካሄዳቸዉ የተለያዩ የማኅበረሰብ ተሳትፎዎች ተቀባይነትን በማግኘቱ ነዉ።

«የፎቶ አርቲስት ነኝ። ፎቶግራፍ ላይ ከኢትዮጵያ ጀምሮ በጣም ፍላጎት ስለነበረኝ ፤ ኢትዮጵያዉስጥ ሳለሁ ብዙ ጉዜ ከከተማ ዉጭ በግልም ሆነ በስራ አጋጣሚ እወጣ ስለነበር ፎቶዎች አነሳ ነበር። ኢትዮጵያ እያለሁ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ዉስጥ እሰራ ስለነበር ፤ አብዛኛዉን ጊዜን አሳልፍ የነበረዉ በማኅበረሰባዊ ጉዳዮች ላይ ነበር። የማኅበራዊ ጉዳዮች ተቆርቋሪም ነኝ። ፎቶግራፍ ማንሳቱን ግን ልክ እንደ አንድ የምወደዉ ነገር ነበር የያዝኩት። ኮርያ ከመጣሁ በኋላ ግን በፎቶግራፍ ላይ የተለያዩ ሙከራዎች በማድረግ የሚሰራ አንድ ጥሩ እድል ገጥሞኝ ሰርቼ በጣም ጥሩ ዉጤትን አመጥቻለሁ። በዚህ ፕሮጀክት ባሳየሁት የፎቶግራፍ ኤግዚቢሽን በደቡብ ኮርያ መጠነኛ እዉቅናን አትርፍያለሁ። ከዚህ ፕሮጀክት በኋላ ባለፉት ሦስት ዓመታት በደቡብ ኮርያ የተለያዩ የፎቶግራፍ ኤግዚቢሽኖችን አሳይቻለሁ። እዚሁ ሃገር ሆኜ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተካሄደ ኤግዚቢሽን ላይም ተሳትፊያለሁ። ስለዚህም ሁለት ነገር እየሰራሁ የምገኘዉ አንድኛ የፎቶግራፍ ስራዎቼን ሌላዉ በማኅበረሰብ ተሳትፎ ላይ ብዙ ስራዎችን እሰራለሁ።

Berkete Alemayehu  Fotokünstler aus Äthiopien in Südkorea
ምስል privat

የማኅበረሰብ ተሳትፎ ስትል ምን ማለትህ ነዉ? በምን ጉዳዮች ላይ ነዉ የምትሳተፈዉ?

«በአብዛኛዉ የምሰራዉ ከአፍሪቃዉያን ከኢትዮጵያዉያን ጋር ነዉ። ኮርያ እንደአጋጣሚ ሆኖ ብዙም ከፈት ያለ ሃገር አይደለም። ስለዚህ የዉጭ ሃገራትን በማስተዋወቅ ፤ ማኅበረሰብን በማስተዋወቅ ኅብረተሰቡ ግንዛቤ እንሰጣለን። ለምሳሌ የኢትዮጵያ አልባሳትን በማሳየት ፤ ባህላዊዉን የቡና አፈላል ዘዴ በማሳየት፤ የምናከብራቸዉን በዓላት ሁሉ አጋጣሚዎችን እየተጠቀምን በማሳየት በመሳሰሉት ሃገራችን ብሎም አህጉራችንን ለማስተዋወቅ ጥረት እናደርጋለን ማለት ነዉ።»

በደቡብ ኮርያ በርካታ ኢትዮጵያዉያን ይኖራሉ?

« ኮርያ ዉስጥ በተለያየ ቦታ ወደ አንድ ሺህ የሚሆኖ ኢትዮጵያዉያን ይኖራሉ። ስደተኞች አሉ ተማሪዎች አሉ ፤ በስራ አጋጣሚ የመጡ ሁሉ አሉ። ኤንባስያችንም ሶል ዉስጥ ይገኛል »

ማኅበረሰቡ ለጥቁር ማኅበረሰብ ባጠቃላይ ለአፍሪቃዊ እንግዳ ነዉ? ባህላቸዉስ እንዴት ነዉ?

«እንግዶች እንኳ አይመስሉኝም። እንደምንናስታዉሰዉ በተለይ ካለፉት 70 ዓመታት ወዲህ ፤ ኮርያዉያን ሰሜንና ደቡብ ተብለዉ የተከፈሉበት ጦርነት ወደ 65 የዓለም ሃገራት ተሳትፈዋል። ደቡብ ኮርያን በማገዝ የተባበሩት መንግሥታት በአሜሪካ የተመራ ጥምር ጦ ር ልኮ ነበር። በዚህ ጦርነት ላይ ከአፍሪቃ ኢትዮጵያ ደቡብ አፍሪቃ ተሳትፈዋል። ስለዚህ በጣም ብዙ የዓለም ሃገራት ህዝቦች ወደዚህ ሃገር ይመጣሉ ይሄዳሉ። እንደዝያም ሆኖ የደቡብ ኮርያዉያን ባህል እምብዛም ለዉጭዉ ዓለም ክፍት አይደለም። የአኗኗራቸዉ ሁኔታም በጣም ለየት ያለ ነዉ። ጊዜ የላቸዉም በጣም ይሰራሉ። እንደዉም አንዳንድ ጊዜ መንግሥት ሕዝቡ ብዙ ስራ እንዳይሰራ እረፍ ት እንዲወስድ ይመክራል።»

ኢትዮጵያ በተለይ በኮሮያ ጦርነት በመሳተፍ ሃገሪቱን በመርዳትዋ ሁለቱ ሃገራት ያላቸዉ ታሪካዊ ትስስር ጥልቅ ነዉ። በደቡብ ኮርያ የኢትዮጵያዉያን ተቀባይነት ምን ያልህል ነዉ? ሕዝቡስ ስለኢትዮጵያ ያነሳል? እስቲ ንገረን !

Berkete Alemayehu  Fotokünstler aus Äthiopien in Südkorea
ምስል privat

«ኮርያ ሃገር እንደ ኢትዮጵያዊነት ትልቁ ነገር ቀና ብለን የምንሄድበት ነገር ይኸዉ የሁለቱ ሃገራት ታሪክ ነዉ። በ1950 ዎቹ በነበረዉ የኮርያዉያን ጦርነት ፤ የኢትዮጵያ ጦር በተለይ የቃኘዉ ሻለቃ ጦር በጦርነቱ በመሳተፉ ፤ አሁን በጣም ትልቅ ቦታ ትልቅ ክብር እንዲሰጠን አስችሎአል። በጦርነቱ ብቻ ሳይሆን በሰላም ማስጠበቁ ሂደት ከ 6 ሺህ በላይ የኢትዮጵያ ወታደሮች ተሳትፈዋል። በጦርነቱ 122 አልያም በ 123 ኢትዮጵያዉያን በኮርያ ጦርነት ተሰዉተዋል። በዚህ ጦርነት ከ 500 በላይ ኢትዮጵያዉያን ወታደሮች አካል ጉዳተኛ ሆነዋል። በዚህ ጦርነት ከሚገርመዉ ታሪካችን አንዱ አንድም የጦር ምርኮኛ ያልነበራት ሃገር ብትኖር ኢትዮጵያ ብቻ ናት። እና ለዚህ ወላታ የኮርያ መንግስት ኢትዮጵያን የሚከብር ለጦርነቱ የተሰዉትን እና የወታደሮቹን ገድል ማስታወሻ ከመዲና ሶል ወደ 87 ኮሎሚትር ርቀት ላይ በሚገኝ ቺንቾን ከተማ ላይ የመታሰብያ ቦታ አቁሞአል። ማንም ኢትዮጵያዊ ወደ ኮርያ ከመጣ ይህን ቦታ ሳይጎበኝ አይሄድም። ወደ ቺንቾን ከተማ የሚወስደ አንድ መንገድም የኢትዮጵያ መንገድ ተብሎ የተሰየመ አለ። በሌሎች ሁለት ቦታዎችም እንዲሁ ለኢትዮጵያዉያን ማስታወሻ የቆሙ ቦታዎች አሉ።  ኢትዮጵያን የሚወድስ ቦታ ነዉ።

የኮሮና ቫይረስ ጉዳይ በደቡብ ኮርያ የፓለቲካው ክርክር ድምቀት እንደነበር ነግረኸናል። ምርጫዉን የፕሬዝዳንት ሙንጄይን ፓርቲም አሸንፎአል። ከጎርጎረሳዊዉ 2000 ዓ.ም ወዲህ ከተገመተው በላይ መራጭ ወጥቶ እንዲመርጥ የኮሮና ወረርሽኝ ነገር ዜጋውን ገፋፍቶታል ነዉ የተባለዉ። የፕሬዚዳንት ሙንጄይ ኢን ፓርቲ ምርጫውን እንዲያሸንፍ ካደረጉት ውስጥም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል በሚሰራው ስራ ከህዝቡ ድጋፍ በማግኘቱ ነው ተብሏል። ይሁንና ደቡብ ኮርያ የኮሮና ተኅዋሲ በቅድምያ ከተዛመተባቸዉ ሃገራት የመጀመርያዋ እንደነበረች እንዲሁም ተኅዋሲዉ በሃገሪቱ ስጋት ማሳደሩ ነበር የተዘገበዉ።

Berkete Alemayehu  Fotokünstler aus Äthiopien in Südkorea
ምስል privat

ይህንኑ የኮሮና ወረርሽኙን ለመከላከል በሚደረግ ጥረት ደቡብ ኮርያ ልምድ መዉሰድ ይቻላል ትላለህ?

በስደት ደቡብ ኮርያ መዲና ሶል የሚኖረዉ ኢትዮጵያዊዉ ወጣት በረከት አለማየሁ ለሰጠን ቃለ ምልልስ በዶቼ ቬለ ስም አመሰግናለሁ። በኮርያንኛ ካምሳምኒዳ ብያለሁ። አመሰግናለሁ ማለት እንደሆን አብረን ሰምተናል። በረከት አለማየሁን ጤና ይስጥልኝ በኮርያንኛ መኖሩን ሳልጠይቅ ስልኩን ዘጋሁ። ብቻ ጤናይስጥልኝ የሚለዉ የሰላምታና የስንብት አሰጣጥ በኢትዮጵያዉያን ዘንድ ብቻ መኖሩን የሰማሁ መስሎኛል። አድማጮች ሙሉ ጥንቅሩን እንድታደምጡ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ

እሸቴ በቀለ