1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

ኢትዮጵያዊቷ ምሁር የሁምቦልት ድርጅት ሽልማትን አሸነፉ

ረቡዕ፣ ሰኔ 20 2010

በዕውቁ ጀርመናዊ ሊቅ አሌክሳንደር ፎን ሁምቦልት  ስም የተሰየመ ድርጅት በየዓመቱ ስብሰባ እና የሽልማት ስነስርዓት ያካሄዳል። ዛሬ አመሻሹ ላይ በተጀመረው እና በበርሊን እየተካሄደ በሚገኘው በዚህ ዓመቱ ዝግጅት ተሸላሚ ከሚሆኑት መካከል ኢትዮጵያዊቷ ምሁር ይገኙበታል።  

https://p.dw.com/p/30Q4f
Deutsche Meinungen zu Brexit-Verhandlungen
ምስል DW/J. Chase

ፕሮፌሰር የዓለምጸሐይ መኮንን የሁምቦልት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል

የጀርመኗ መዲና በርሊን ከ80 ሃገራት የተውጣጡ 600 ተመራማሪዎችን በአንድ ቦታ አሰባስባለች። ተመራማሪዎቹ በተለያዩ የጀርመን ዩኒቨርስቲዎች የተማሩ፣ ምርምር ያደረጉ እና አሁንም ጥናታቸውን እያከናወኑ ያሉ ናቸው። ለምርምር የሚሆናቸውን ድጋፍ የሰጣቸው የአሌክሳንደር ፎን ሁምቦልት ድርጅት በየዓመቱ እንደሚያደርገው ሁሉ ዘንድሮም ለተመራማሪዎቹ የመወያያ መድረክ ፈጥሮላቸዋል። በሥራቸው ለላቁት የሚበረከተውን ሽልማት ዘንድሮም አልዘነጋም። 

ድርጅቱ በስማቸው  የተሰየመላቸው ጀርመናዊው አሌክሳንደር ፎን ሁምቦልት በተለያዩ የሳይንስ ዘርፎች ስማቸው የሚነሳ ሊቅ ናቸው። ከፊዚክስ እስከ ሥነ ቅመማ፣  ከሥነ አራዊት እስከ ሥነ-ህይወት ፣ ከሥነ-ምድር እስከ ሥነ ፈለክ ድረስ ጥናቶችን አካሄደዋል። ህልፈተ ሕይወታቸውን ተከትሎ የዛሬ 158 ዓመት በስማቸው የተመሰረተው ድርጅት አሁን በመላው ዓለም በእርሱ ጥላ ስር የተሰባሰቡ 28 ሺህ ገደማ ተመራማሪዎችን የሚደግፍ ሆኗል። ከእነዚህ ተመራማሪዎች ውስጥ ኢትዮጵያውያንም ይገኙበታል። ዛሬ በበርሊን በተከፈተው የድርጅቱ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ እየተካፈሉ ከሚገኙ ስድስት ኢትዮጵያውያን ምሁራን መካከል ዶ/ር ቢኒያም ኃይሉ አንዱ ናቸው። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የመሬት ሳይንስ ትምህርት ክፍል በረዳት ፕሮፌሰርነት የሚያገለግሉት ዶ/ር ቢኒያም ካለፈው ኅዳር ወር ጀምረው በጀርመኗ ማርቡርግ ከትመዋል። ከሁምቦልት ድርጅት ባገኙት የምርምር ድጋፍ የማርቡርግ ከተማን ስያሜ በተዋሰው ዩኒቨርስቲ ውስጥ ጥናት እያደረጉ ይገኛሉ። በሁምቦልት ድርጅት ድጋፍ ከሀገራቸው ውጭ ጥናት ማድረጋቸው ጠቀሜታው ምን እንደሆነ ያስረዳሉ።

Alexander v.Humboldt Scharder
ምስል picture-alliance/akg-images

ዶ/ር ቢኒያም በጀርመን ቆይታቸው ጥናታቸው ላይ ብቻ ማተኮር ከመቻላቸው ባሻገር የሁምቦልት ድርጅት በሚያዘጋጃቸው ስብሰባዎች ለመሳተፍ መቻላቸው ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው ይናገራሉ። ባለፈው ሚያዝያ ወር ሬገን ስቡርግ በተሰኘችው አነስተኛ የጀርመን ከተማ በተደረገ የተመራማሪዎች የትስስር መድረክ መሳተፋቸውን በምሳሌነት ያነሳሉ። በመድረኩ ከሌሎች ሃገራት ከመጡ ተመራማሪዎች ጋር የልምድ ልውውጥ ማድረግ መቻላቸውን እና ስለ መሰል የምርምር ሥራዎች  ግንዛቤ ማግኘታቸውን ያስረዳሉ። ዛሬ በበርሊን የተጀመረው ዓይነት ስብሰባ ላይ መካፈል ያለውን ጠቀሜታ ደግሞ እንዲህ ያብራራሉ። 

ከዚህ ቀደም እንደተለመደው ሁሉ በዘንድሮው የሁምቦልት ስብሰባም የድርጅቱን ድጋፍ አግኝተው ወደ ጀርመን የመጡ ተመራማሪዎች ያገኙትን ልምድ የሚያካፍሉበት መርኃ ግብር ተካትቷል። የቁልፍ ተናጋሪነቱ ቦታ የተሰጠው በዓለም አቀፍ ደረጃ ዝናቸው ለናኘው የሆምቦልቱ ፕሮፌሰር ማቲያስ ቾፕ ነው። በሙኒክ ቴክኒካል ዩኒቨርስቲ የሚያስተምሩት ፕሮፌሰር ቾፕ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በጀርመን ትኩረት እየሳበ ስለመጣው የስኳር በሽታ ገለጻ ያደርጋሉ።

በበርሊኑ ስብሰባ ሁለት የሽልማት ስነ ስርዓቶች ይካሄዳሉ። በነገው ዕለት የጀርመን ፕሬዝዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር በተገኙበት የሚካሄደው አንደኛው የሽልማት ስነ ስርዓት በየዓመቱ ለጃፓን ተመራማሪዎች እና ምሁራን የሚበረከት ነው። በጎርጎሮሳዊው 1978 ጃፓንን በጎበኙት የጀርመን ፕሬዝዳንት ፊሊፕ ፍራንስ ፎን ዚቦልድ የተሰየመው ሽልማት በሁለቱ ሃገራት ባህል እና ማኅብረሰብ መካከል ያለውን የጋራ መግባባት ለማሻሻል ለጣሩ ሰዎች ዕውቅና የሚሰጥበት ነው። የ50 ሺህ ዩሮ የዚህ ዓመት ተሸላሚ ተደርገው የተመረጡት ካንኮ ታካያማ የተባሉ ጃፓናዊት የሕግ ባለሙያ ናቸው። 

Deutschland Bundespräsident Frank-Walter Steinmeier in Berlin
ምስል picture-alliance/abaca/M. Gambarini

ሁለተኛው ሽልማት ሁምቦልትያን ተብለው ለሚታወቁ ቀደም ሲል በድርጅቱ ድጋፍ ወይም ፌሎሺፕ ላገኙ ምሁራን የሚሰጥ ነው። ዛሬ ምሽት ሽልማቱ ከሚበረክትላቸው ምሁራን ውስጥ ኢትዮጵያዊቷ ፕሮፌሰር የዓለምጸሐይ መኮንን አንዷ ናቸው። ፕሮፌሰር የዓለምጸሐይ ሽልማቱን እርሳቸው ይቀበሉ እንጂ ከኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ እና በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ማሕበር ጋር ለመተግበር ላቀዱት ሥራ የተበረከተ እንደሆነ ይናገራሉ። ፕሮፌሰር የዓለምጸሐይ እርሳቸውን እና በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ማሕበር በተበረከተላቸው የ25 ሺህ ዩሮ ሽልማት ለማድረግ ያሰቡትን ያብራራሉ። 

ቀደምት ከሚባሉ የሁምቦልት ዕድል ተጠቃሚዎች አንዷ የሆኑት ፕሮፌሰር የዓለምጸሐይ የደረሱበት ደረጃ ለተተኪዎቹ ለእነ ዶ/ር ቢኒያም ተምሳሌት ነው። ፊንላንድ ከሚገኘው የሂልሲንኪ ዩኒቨርስቲ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በጫኑ በሁለተኛ ዓመታቸው የሁምቦልትን ድጋፍ ያገኙት ዶ/ር ቢኒያም ይህ የድርጅቱ ሽልማት ለወጣት ምሁራን መነቃቃት ይፈጥራል ይላሉ።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምጽ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።  

ተስፋለም ወልደየስ

ሸዋዬ ለገሠ