1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መኖሪያ ቤቶችን ቀለም የመቀባትና ምልክት የማድረግ ስጋት

ማክሰኞ፣ መስከረም 15 2011

በኢትዮጵያ ለዉጥ ከተጀመረ ካላፉት ጥቂት ወራት ወዲህ በርካታ የኅብረተሰብ ክፍል ለውጡን የደገፈና በለውጡ ተስፋ የሰነቀ መሆኑን በተለያዩ የድጋፍ ሰልፎች ሲገልፅ ቆይቷል። ያም ሆኖ ግን ለውጡን ተከትለዉ የተከሰቱ ግጭቶች ባደረሱት የሰው ሕይወት መጥፋት፣ የንብረት ውድመትና መፈናቀል የተነሳ ፤

https://p.dw.com/p/35U6A
Karte Sodo Ethiopia ENG

Threat in Hawassa City. - MP3-Stereo

ኅብረተሰቡ ለውጡን በጥርጣሬና በስጋት ማየት መጀመሩን ብዙዎች ይናገራሉ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ማንነታቸዉ ያልታወቀ ሰዎች በተለያዩ አካባቢዎች የግለሰቦችን ቤት በርና አጥር ቀለም በመቀባትና ምልክት በማድረግ በኅብረተሰቡ ዘንድ ስጋትና ጥርጣሬ እየፈጠሩ መሆኑ እየተነገረ ነው።
ከዚህ ቀደም በጅግጅጋ ጥቃት ከመፈፀሙ በፊት ታይቷል የሚባለዉ ባልታወቁ ሰዎች የመኖሪያ ቤቶችን በር ቀለም የመቀባትና ምልክት የማድረግ ጉዳይ ያለፈዉ ሳምንት በድሬዳዋ ከተማ በመታየቱ ትልቅ ስጋትና  መነጋጋሪያ ሆኖ ነዉ የሰነበተው።

Äthiopien Dire Dawa City
ምስል DW/Y. Gebreegziabher

ካለፉት ሦስት ቀናት ወዲህ ደግሞ በደቡብ ክልል ሀዋሳ ከተማ አንዳንድ አካባቢዎች ይሄው ምልክት በመታየቱ የከተማዋን ነዋሪዎች ለጥቃት እንጋለጣለን በሚል ስጋት ውስጥ ከትቶ መሰንበቱን ነው ነዋሪዎች የሚገልፁት። ስማቸውን መግለፅ ያልፈለጉ አንድ የከተማዋ ነዋሪ ለDW እንደገለፁት ስጋቱ የመነጨዉ ምልክቱ የሚደረገው ማንነት ላይ ባነጣጠረ መልኩ በመሆኑ ነበር።
በተፈጠረው ሁኔታም ነዋሪው ተረጋግቶ መደበኛ ሥራውን ማከናወን ካለመቻሉም በላይ በኅብረተሰቡ መካከል አለመተማመንና ጥርጣሬ ተፈጥሮ እንደነበር ነው ነዋሪው የገለጹት። ከዚህ የተነሳ ኅብረተሰቡ ከቤት ውጭ ሆኖ ራሱን ሲጠብቅ እንደነበር ጠቁመው ፤ በዘላቂነት ግን መንግሥት ኅብረተሰቡን የመፍትሄ አካል በማድረግ የሰከነ ሁኔታ እንዲፈጠር መስራት አለበት ብለዋል።
ሰሞኑን በከተማዋ የተፈጠረውን የፀጥታ ስጋት በተመለከተ በትናንትናው ዕለት መግለጫ የሰጠው የሃዋሳ ከተማ ፖሊስ መምሪያም የድርጊቱን ፈፃሚዎች  በቁጥጥር ስር እንደሚያውል ገልፆ፤ ጉዳዩን የከተማዋን ህዝብ በአንድነት የመኖር ዕሴት ለማፍረስ ሆን ተብሎ የተደረገ ነው ብሎታል።
ጉዳዩን በተመለከተ ያነጋገርናቸዉ በወልቂጤ ዩንቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር የሆኑት አቶ ዳንኤል መኮነን በአዲሱና በነባሩ መካከል ባለ ተቃርኖ ሳቢያ በለውጥ ማግስት እንዲህ አይነት ነገሮች መፈጠራቸው በተለያዩ አገሮች የታየና የተለመደ መሆኑን ገልፀዋል።
እንደ አቶ ዳንኤል የዚህ መሰሉ ድርጊት አላማ የነበረዉን ስርዓት ማስቀጠል፤ ለውጡን ደግሞ በጅምር ማስቀረት ነው። በተለይ ደግሞ በኢትዮጵያ እንደታየው ለውጡን የሚደግፈው ማኅበረሰብ በርካታ ከሆነ  አለመተማመንና ጥርጣሬ የሚፈጥሩ ነገሮች በሌላኛው ወገን መመደረጉ አይቀሬ ነው። ለዚህም ሰሞኑን በተለያዩ አካባቢዎች የተደረገዉ ቀለም የመቀባትና ምልክት የማድረግ ጉዳይ በማሳያነት ያቀርቡታል።

«ለምሳሌ ድሬደዋ ላይ ተመልክተናል።ሀዋሳ ላይ ተመልክተናል።ጅግጅጋም ላይ ነበር።እነዚህ ነገሮች ምንድናቸዉ በየቤቱ ምልክት የማድረግ ነዉ።ይህ ነገር በህዝቡ ላይ «ቴረር»ይፈጥራል።ካሉ በኋላ ፤ ህዝቡ ምንም እንኳን በለዉጡ ደስተኛና ተስፋ ያለዉ ቢሆንም፤ይህ ጉዳይ ጥርጣሬ ያሳድራል ነዉ ያሉት።

መንግሥት በአጥፊዎቹ ላይ አስፈላጊና ትክክለኛ እርምጃ መውሰድ፤ ማኅበረሰቡ የነበረውን ተሳስቦና ተከባባሮ የመኖር ባህል ማጎልበትና ወጣቱ የአካባቢውንና የማኅበረሰቡን ሰላም ነቅቶ መጠበቅ ፤ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ እየታዬ ላለው ችግር መፍትሄ መሆኑን የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ አቶ ዳንኤል መኮነን መክረዋል።

ሙሉ ዘገባዉን የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን ያድምጡ።

ፀሐይ ጫኔ

ሸዋዬ ለገሠ