1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያን ወዳጁ የጥቁር ህዝብ መብት ተሟጋች

ሐሙስ፣ ሐምሌ 16 2012

«በአንደኛ ደረጃ ሰላማዊ ትግል የእዉነት ምን እንደሆነ በጆን ሉዊስ ህይወት እና ማንነት ዉስጥ መማር ይቻላል። እኛ ኢትዮጵያዉያን አሁን ለሚደርስብን ችግር ሁሉ በሰላማዊ ትግል መፍትሄን መፈለግና ይሄን አሁን ያለንበትን የወሊድ ምጥ ሁላችንም ተባብረን አዲሲትዋ ኢትዮጵያ እንድትወለድ መርዳት አለብን።»

https://p.dw.com/p/3fphM
USA Konföderiertenstatue - Black Lives Matter Protest
ምስል picture-alliance/AP Photo/S. Helber

ጆን ልዊስ በሰላማዊ ትግል የሚያምኑ ለጥቁር ሕዝብ መብት የታገሉ ናቸዉ

 

«በወጣትነት ዘመናቸዉ በሰብዓዊ መብት ትግል ላይ ሳሉ ብዙ ስቃይ አሳልፈዋል። ታስረዋል። ተደብድበዋል። ያንን ሁሉ አልፈዉ ግን ያደርጉት የነበረዉ ትግል ቂመኛ አልነበረም። ይልቁንም በአሜሪካ የሚታየዉ የመብት ጥሰት ከድንቁርና የተነሳ ነዉ። ስለዚህ ማስተማር ነዉ ያለብን ይሉ ነበር።  እኛ እንደተረዳነዉ ሌላዉ ሰዉ ላይረዳዉ ይችላል፤ የሚል አቋም ነበራቸዉ። ነገሩን እኛ በምናየዉ መልክ እንዲረዱ እናድርግ ይሉ ነበር። በጥላቻ የሚሆን አይደለም ይሉ ነበር። ሰላማዊ በሆነ ትግል የሚያምኑ ሰዉ ነበሩ።»     

176c John Lewis WhatAmerica
ምስል DW

ጥቁር አሜሪካዊው የመብት ተሟጋች ጆን ሮበርት ልዊስን በተመለከተ አስተያየት የሰጡን በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢዋ በኅብረተሰብ አገልግሎት ላይ የሚሰሩት የኢትዮጵያዉያን ማኅበረሰብ ምክር ቤት መስራችና ፕሬዚዳንት  ዶ/ር ፀሐዬ ተፈራ ናቸዉ ። ሐምሌ 11፤ 2012 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸዉ የተሰማዉ ጥቁር አሜሪካዊዉ ጆን ልዊስን በተመለከተ አስተያየት የሰጡን ሌላዉ ኢትዮጵያዊ መዲና ዋሽንግተን ዲሲ ላይ ነዋሪ የሆኑት የፀሐይ አሳታሚ ድርጅት መስራችና ባለቤት አቶ ኤልያስ ወንድሙ ናቸዉ።

«በአንደኛ ደረጃ ሰላማዊ ትግል የእዉነት ምን እንደሆነ በጆን ሉዊስ ህይወት እና ማንነት ዉስጥ መማር ይቻላል። የጆን ሉዊስ ስራዎችን ወደ አማርኛ ተተርጉሞ ተዘጋጅተዋል። እነዚህ ስራዎች ማንበብ እና ማየት ይጠቅማል። እኛ ኢትዮጵያዉያን አሁን ለሚደርስብን ችግሮች ሁሉ  ሰላማዊ መፍትሄዎችን መፈለግ እና ይሄንን አሁን ያለንበትን የወሊድ ምጥ ሁላችንም ተባብረን አዲሲትዋ ኢትዮጵያ እንድትወለድ መርዳት አለብን።»   

ሐምሌ 11 ቀን  2012 ዓ.ም ቅዳሜ እለት ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸዉ የተሰማዉ ስመ ጥሩዉ ጥቁር አሜሪካዊው የመብት ተሟጋች ጆን ልዊስ ካንሰር ታመው ሕክምና በመከታተል ላይ ነበሩ።  የ 80 ዓመቱ ጥቁር አሜሪካዊ ለጥቁር ሕዝቦች ነጻነት እኩልነት እና ለሰብዓዊ መብቶች ሙሉ ሕይወታቸዉን ታግለዋል። በዚሁ ትግል በተለይ እንደ ጎርጎረሳዉያኑ አቆጣጠር በ 1960ዎቹ ለሕይወታቸዉ በአስጊ አደጋ  ላይ ሁሉ ደርሰዉም ነበር። ጆን ሉዊስ ባለፈዉ ዓመት መታመማቸዉን በይፋ ሲያሳዉቁ ካንሰርንም እንዲሁን እንደሚታገሉት ተናግረዉ ነበር። በቅርቡ በነጭ ፖሊሶች በግፍ የተገደለው ጆርጅ ፍሎይድ፤ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ሆኖ ፤ ፖሊስ አንገቱ ላይ በጉልበቱ ቆሞ የሚታይበትን የ 46 ሰከንድ ፊልም አይተዉ ማልቀሳቸዉን ተናግረዋል። እንድያም ሆኖ የፖሊስን የግፍ አያያዝ እና አገዳደል በመቃወም ብላክ ላይቭስ ማተር በተሰኘ የጥቁር ሕይወትም ዋጋ አለዉ በሚል  በአሜሪካ ምድር ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ የተነሳዉን ንቅናቄ አይተዉ «በአዲሱ  ትዉልድ እኮራለሁ» ሲሉ ተናግረዋል።

Elias Wondimu und John Lewis
ምስል Elias Wondimu

ከጥቁር አሜሪካዊው የመብት ተሟጋች ከጆን ልዊስ ጋር በተዘዋዋሪ በስራ ግንኙነት እንደነበራቸዉ የነገሩን በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢዋ በኅብረተሰብ አገልግሎት ላይ የሚሰሩት የኢትዮጵያዉያን ማኅበረሰብ ምክር ቤት መስራችና ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፀሐዬ ተፈራ፤ ስለ ጆን ሉዊስ ይህን ተናግረዋል።   

«ጆን ሉዊስ በአሜሪካን ሃገር ጥቁሮች ያደርጉት በነበረዉ የሰብዓዊ መብት ትግል ላይ ብዙ ሚና የነበራቸዉ ታጋይ ነበሩ። በተለይ በአሜሪካ ምክር ቤት ኮንግረስ አባል ሆነዉ ትግላቸዉን በማጠናከር በተለይ የጥቁሮችን መብት ስደተኞችን በሚመለከት ትልቅ ሚና የተጫወቱ ናቸዉ። የአፍሪቃ ስደተኞች በአሜሪካን ሃገር መብታቸዉ እንዲከበር፤ ከአፍሪቃም ወደዚህ እንደማንኛዉም ስደተኛ መልሶ በማቋቋም አሜሪካን ሃገር እንዲገቡ ብዙ ታግለዋል። በአሜሪካ በጊዜዉ ወደ ፖለቲካዉ መድረክ ከሚመጡ አስተዳዳሪዎች ላይ ጫና በማሳረፍ ትልቅ ሚና የነበራቸዉ ሰዉ ናቸዉ። ብዙ ስቃይም አሳልፈዋል።  ታስረዋል። ተደብድበዋል። ያንን ሁሉ አልፈዉ ግን ያደርጉት የነበረዉ ትግል ቂመኛ ሳይሆን በአሜሪካን ሃገር ያለዉ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ከድንቁራ የተነሳ ነዉ ሲሉ ነበር የሚያምኑት። ስለዚህም ማስተማር ነዉ ያለብን፤ እኛ እንደምናየዉ ልናሳያቸዉ ልንገልፅላቸዉ ይገባል ሲሉ ይናገሩ ነበር። ብዙዎቻችን እዚህ ሃገር ብዙ ነገር ከተስተካከለ በኋላ ነዉ የመጣነዉ። አሁን የፈለግንበት አካባቢ የመኖር መብት አለን። አቅሙ እስካለን ድረስ የፈለግለዉን ቤት መከራየት እንችላለን። መግዛት እንችላለን። ለጥቁሮች ይሄ አይነቱ ሁኔታ ከ 40 እና 60 ዓመት በፊት የማይታሰብ ነበር። »

በአሜሪካ የሕዝብ መጓጓዣዎች ጥቁሮች እንዳይጓዙ የሚደረገዉን መድሎ ለመታገል ጆን ሉዊስ የ21 ዓመት ወጣት ሳሉ ፍሪደም ራይደርስ የተባለ ማኅበር ከመሰረቱት ስድስት ወጣት የንቅናቄ አባላት አንዱ ነበሩ።  ከዝያ ነዉ በጥቁር አሜሪካውያን የፍትህ እና የእኩልነት ትግል ውስጥ ላቅ ያለ ሚና እያሳደሩ መምጣት የጀመሩት።  የፀሐይ አሳታሚ ድርጅት መስራችና ባለቤት አቶ ኤልያስ ወንድሙ ጥቁሩን የነፃነት ታጋይ ያቋቸዋል። የሕይወት ታሪካቸዉንም ወደ አማርኛ ተርጉመዉ ለአድማጭ አንባብያን እያሰራጩ ነዉ።    

« የቀድሞዉ ፕሬዚዳንት ቢል ክሊንተን ጆን ሉዊስን « የሃገሪትዋ ህሊና ናቸዉ ብለዋቸዋል።  እኔ እንደ አጋጣሚ ሆኖ በአሜሪካ የሰብዓዊ መብት እንቅስቃሴ በነበረበት ጊዜ የጆን ሉዊስ አስተማሪ የነበሩ ጂም ሎሰንን ለመተዋወቅ እድሉ ነበረኝ። ከዝያ በኋላ ኢትዮጵያ ዉስጥ የ1997 ምርጫ ከተካሄደና ሰዎች ከአለቁ በኋላ «ኢትዮጵያ የሰላም ጥናትና የነዉጥ አልባ ትምህርት» የተሰኘዉን ተቋም በምናቋቁምበት ጊዜ አብረዋቸዉ የነበሩ ብሪነት ላፋይት የተባሉ ሰዉ ከታላቁ ባለቅኔ ከሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን ጋር የቦርድ አባል ሆነዉ እኔ ባቋቋምኩት ተቋም ዉስጥ አብረን መስራት ጀምረን ነበር። በዝያም ምክንያት እነዚህ ሰዎች በግለሰብ ደረጃ ማወቅ ችያለሁ።»        

USA Protest Abgeordnete der Demokraten für Verschärfung des Waffenrechts
ምስል picture-alliance/dpa/J. lo Scalzo

ጆን ሉዊስ ከኢትዮጵያዉያን ጋር በጣም የቅርብ ግንኙነት እንዳላቸዉ ይነገራል። ብዙዎችም ይወድዋቸዋል ይባላል ይህ ምን ያህል እዉነት ነዉ? ለሚለዉ ጥያቄ አቶ ኤልያስ ወንድሙ፤

 « አዎ አትላንታም ሆነ በዋሽንግተን ከሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን ጋር ብዙ ግንኙነት ነበራቸዉ። በአሜሪካን ሃገር በሰብዓዊ መብት ትግል ላይ የተሳተፉት ሰዎች ከኢትዮጵያና ከኢትዮጵያዉያን ጋር የመንፈስ ቁርኝት ነበራቸዉ። ከማርቲን ሉተር ኪንግ ጋር በትግል ላይ የነበሩ አንድ ሰዉ ተዋዉቄ ፤ «ስሞት ኢትዮጵያ  ነዉ መቀበር የምፈልገዉ » ሲሉ እንደነገሩኝ አስታዉሳለሁ። እነዚህ  ከትግል ጋር የነበሩ ሰዎች ነፃነታቸዉንም ከኢትዮጵያ ጋር አብረዉ አዋቅረዉ የሚይዙ ግለሰቦች ነበሩ። የሚያሳዝነዉ ኢትዮጵያን በእንዲህ በትልቅነት መንፈስ ያዉቁ የነበሩ የዝያን ጊዜዎቹ የነፃነት ታጋዮች በእድሜ በጤና እያለቁ ነዉ። አሁን ያለዉ ትዉልድ ኢትዮጵያን የሚያዉቋት በጦርነት በረሃብ ፤ በስደት ነዉ። ያ ያሳዝነኛል። »

ማርቲን ሉተር ኪንግ ሕልም አለኝ የሚል ታዋቂ ንግግራቸውን ያደረጉበት እና በጎርጎሮሳዊው 1963 ዓ.ም  በዋሽንግተን ዲሲ የተካሔደ ሰልፍ ካስተባበሩ ስድስት መሪዎች መካከል ጆን ልዊስ ነበሩ።

Tsehaye Teferra, Ethiopian Community Development Council (ECDC)
ምስል privat

« ጆንሉዊስ የኮንግረስ አባል ከሆኑ ከጎርጎረሳዉያኑ  1986 ዓ.ም ጀምሮ እስከአሁን ድረስ ለ 17 ጊዜ በማሸነፍ በኮንግረስ ጆርጅያ የሚባለዉን ጠቅላይ ግዛት ሲወክሉ ነዉ የቆዩት። ለጥቁር መብት ሲታገሉ ሙሉዉን ጊዜያቸዉን ያሳለፉ ነበር። በሆቴል ገብቶ እንደ ነጩ ሁሉ እኩል ለመስተናገድ የሚያስችል መብትን ለማግኘት፤ ጆን ሉዊስ ፤ ሲደበደቡ፤ ሲረገጡ ፤ ፀጉራቸዉ ላይ ሲጋራ ሲለኮስባቸዉ፤ ከነበሩ ሰዎች መካከል አንዱ ናቸዉ። ኢትዮጵያዉያን እዚህ መጥተን ፤ ትዳር መስርተን፤ አልያም ትምህርት ተምረን ስራ ለመያዝ የሚያስችል መብት ያገኛነዉ በእንደነዚህ አይነት ሰዎች ትግል እና በከፈሉት መስዋትነት ነዉ። በጎርጎረሳዉያኑ 1960 ዓ.ም  አካባቢ በአሜሪካ የነፃነት ትግል በሚደረግበት ጊዜ ጆን ሉዊስ ወደ 40 ጊዜ ታስረዋል። የአሜሪካ የሕግ ማስፈፀምያ ክፍል ዉስጥ ትልቅ ስልጣን እያላቸዉ እንኳ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ መቃወም አላቆመዉም ነበር። የኮንግረስ አባል ከሆኑ በኋላ እንኳ አምስት ጊዜ ታስረዋል። በአሁኑ ጊዜ በየትምህርት ቤቱ የሚከሰተዉን የተኩስ እና ግድያ በጣም ተቃዋሚ ነበሩ። »  

ዶ/ር ፀሐዬ ተፈራ በበኩላቸዉ የአሜሪካን ፖለቲከኞች የሃገሪቱን ነዋሪ ምቾት ለማስጠበቅ ሲሉ በመድረክ ላይ በልዩነት ዱላ ቀረሽ ክርክር ያደርጋሉ፤ ሲሉ የአሜሪካን የፖለቲካ መድረክ ባህል በምሳሌ ያስረዳሉ። 

አቶ ኤልያስ ወንድሙ በበኩላቸዉ እኛ ኢትዮጵያዉያን የጆን ሉዊስን ታሪክ የፖለቲካ ስልት ልናዉቀዉ ልናጤነዉ ይገባል ሲሉ ደጋግመዉ ተናግረዋል። ምክንያቱም ይላሉ ጆን ሉዊስ ሰላማዊ ትግል አድርገዉ ለጥቁር ሕዝብ ነጻነትን በማስገኘታቸዉ ነዉ።

USA I Demokrat John Robert Lewis gestorben
ምስል Reuters/J. Young

የካቲት 21 ቀን 1940 ዓ.ም በዩናይትድ ስቴትስ አላባማ ትሮይ በተባለ ቦታ ከጥቁር አሜሪካዉያን ወላጆች የተወለዱት ጆን ልዊስ በአሜሪካ ለጥቁሮች መብት ትግል ከፍተኛ ሚናን በመጫወታቸዉ  ከፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ እጅ በጎርጎሮሳዊው 2011 ዓ.ም የሃገሪቱን ከፍተኛ የነፃነት ሜዳይ ተቀብለዋል። ጆን ሮበርት ሉዊስ ከሁለት ወሩ ጀምሮ ከባለቤታቸዉ ጋር እንደ ልጅ ያሳደጉት የ 44 ዓመት ጎልማሳ ልጅ አላቸዉ። ባለቤታቸዉ ሊሊያን ሚልስ በጎርጎረሳዉያን 2012 ዓ.ም ከረጅም ጊዜ ሕመም በኋላ ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸዉ የታሪክ መዝገባቸዉ ያሳያል።

በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢዋ የኢትዮጵያዉያን ማኅበረሰብ ምክር ቤት መስራችና ፕሬዚዳንት  ዶ/ር ፀሐዬ ተፈራ እና የፀሐይ አሳታሚ ድርጅት መስራችና ባለቤት አቶ ኤልያስ ወንድሙ ለሰጡን ቃለ- ምልልስ እያመሰገንን ፤ ሙሉ ቅንብሩን የድምጽ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን!

 

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ