1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያን በድሮን ምርት የማሳወቅ ህልም ያለው ወጣት

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 23 2014

ኢብራሂም አሊ ይባላል።በሃያዎቹ መጀመሪያ ዕድሜ ላይ የሚገኝ ወጣት ነው። በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የኬሚካል ምህንድስና የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ሲሆን አምስት ሰው ዓልቫ አውሮፕላኖችን ጨምሮ ከ20 በላይ የፈጠራ ስራዎች አሉት። ከነዚህም ውስጥ 14ቱ ስራዎቹ «ሴብ አይዲያስ» በተሰኘው ዓለም አቀፍ ድርጅት ተመዝግበው ይገኛሉ።

https://p.dw.com/p/4Ejvk
Ibrahim Ali, junger Unternehmer in Äthiopien
ምስል privat

ወጣቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ድሮን የማምረት ዕቅድ አለው


በዓለማችን በሳይንስና ቴክኖሎጅ ዘርፍ  ለተከሰቱ አስደናቂ ለውጦች የግለሰቦች የፈጠራ ክህሎት አስተዋፅኦው ከፍተኛ  ነው።ይህንን በመገንዘብ ይመስላል በኢትዮጵያም በርካታ ወጣቶች አስደናቂ ፈጠራዎችን ሲሰሩ ይታያል።የዛሬው የሳይንስና ቴክኖሎጅ ዝግጅትም ኢትዮጵያን በድሮን ምርት የማሳወቅ ህልም ያለው አንድ ወጣት የፈጠራ ባለሙያን ያስተዋውቃል።
ኢብራሂም አሊ ይባላል።በሃያዎቹ መጀመሪያ ዕድሜ ላይ  የሚገኝ ወጣት ነው።ኢብራሂም ትውልድ እና ዕድገቱ አዲስ አበባ ከተማ  ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የኬሚካል ምህንድስና የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ነው።ከትምህርቱ ጎን ለጎን በዩንቨርሲቲው ግቢ የመስሪያ ቦታ ተዘጋጅቶለት  የፈጠራ ስራዎችን በመስራት ላይም ይገኛል።የኢብራሂም የፈጠራ ስራ  አሁን የተጀመረ አይደለም።አብሮት ያደገ የልጅነት ህልሙ  ሲሆን፤ የጀመረውም  ገና  በልጅነቱ የአራተኛ ክፍል ተማሪ እያለ ነው።

Ibrahim Ali, junger Unternehmer in Äthiopien
ምስል privat

«አጀማመሬ ገና ትንሽ ያለሁ ነበር። የአራተኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ ነበር የመጀመሪያውን በካርቶን  የምታኮበኩብ ሂሊኮፍተር የሰራሁት። ከዛም በኋላ በደንብ የሚንቀሳቀሱ ነገሮች ላይ፣ ሮቦቶች ላይ፣ቴክኖሎጂ ነክ ነገሮች ላይ በደንብ መስራት የጀመርኩት 4ኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ  ጀምሮ ነው ።»
በዚህ ሁኔታ የተጀመረው የኢብራሂም የፈጠራ መንገድ በአካባቢው እና በማህበረሰቡ ውስጥ የሚያየውን ችግር ለመፍታት ያግዛሉ  ብሎ የሚያስባቸውን የፈጠራ ስራዎች ከአካባቢው በሚያገኛቸው ነገሮች መስራቱን ቀጠለ። 

«ስምንተኛ ክፍል እያለሁ የሰራሁትት የፈጠራ ስራ ነበር። እስከ ወረዳ ድረስ የሄደ የፈጠራ ስራ ነበረኝ። እሱም «ደብል ሴኪሪቲ» የሆነ ነገር ነው። በራችንን  በቁልፍ ምፓስወርድ እና በካርድ መክፈትና መዝጋት የምንችልበት። እሱን የ8ኛ ክፍል ተማሪ ሆኜ ሰርቻለሁ።» ካለ በኋላ ችግር ፈች የሆነ ዘመናዊ ምንጣፍ መጥረጊያ ማሽን የ11ኛ ክፍል ተማሪ እያለ መስራቱን ገልጿል።
 ከዚህ በተጨማሪ «ከዛም በኋላ ሌሎቹ ፈጠራ ስራዎች አሉ ለምሳሌ የመኪናችን ሞተር ማስነሳትና ማንኛውም ከቤት ውስጥ ያሉት ቁሳቁሶችን  ስልካችንን ጨምሮ ያለ ኢንተርኔት ማብራትና ማጥፋት የሚችል የሚችል ቴክኖሎጂ ሰርቻለሁ።»ሲል አብራርቷል። 
 እንዲህ እንዲህ እያለ የቀጠለው  የወጣቱ የፈጠራ ስራ በአሁኑ ወቅት 28 የፈጠራ ስራዎችን የሰራ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 14ቱ ስራዎቹ «ሴብ አይዲያስ» በተሰኘው ዓለም አቀፍ ድርጅት ተመዝግበው ይገኛሉ።አንዱ የፈጠራ ስራው ማለትም ከዕጅ ንክኪ  ነፃ የሆነ የዕጅ መታጠቢያ ማሽን ደግሞ የአእምሮአዊ ንብረት ባለቤትነት መብት አግኝቷል።ያም ሆኖ ከቀለም ትምህርት ይልቅ ወደ ፈጠራ ስራ ማዘንበሉን የተመለከቱት ወላጆቹ በወቅቱ ደስተኞች አልነበሩም እና እነሱን ለማሳመን አንድም የሚጠቅም ነገር ሰርቶ ማሳየት በሌላ በኩል ደግሞ በትምህርቱ ጎበዝ መሆን ነበረበት።

«ያው ቤተሰቦች የተማሩ ሰዎች አልነበሩም። እነሱ ያሳለፉትንህይወት  ነገር እኔ እንዳልደግመው ስለሚፈልጉ ትምህርት ላይ ብቻ «ፎከስ» አርጌ በዚያ ብቻ ለውጥ እንዳመጣ ነብር የሚፈልጉት። ስምንተኛእና  ዘጠነኛ ክፍል እያለሁ አይደግፉኝም ነበር። ብቻየን ነበር የምስራው ። እንደዛም ሆኖ ግን  የኔን ስሜት ለመጠበቅ ገንዘብ  ይሰጡኝ ነበር።  ከዚያ  በኋላ የፈጠራ ሰራ የሰሩ ሰዎች መለወጥ እንደሚችሉ ስንግግራቸው  ቀስበቀስ እያመኑ መጡ።  በኋላ ዘጠነኛ ክፍል ላይ ሙሉ በሙሉ የፈጠራ ስራ አቆምኩ እና ወደ ትምህርቴ ተመለስኩ 12ተኛ ክፍል ድረስ የደረጃ ተማሪ ሆንኩኝ። በፊት ለማለፍ ያህል ነበር የምማረው።ሰነፍ ተማሪ ነበርኩ። ከዛ በኋላ በትምህርቴ ጎበዝ ሆኘ  እንደምችል  አሳየኋቸው።እነሱም አመኑበት። አሁን በጣም ትልቁን ድጋፍ የማገኘው ከቤተሰቦቼ ነው።»
በፈጠራ ስራዎቹ የአካባቢን ችግር መፍታት ቀዳሚ አላማው መሆኑን የሚናገረው ኢብራሂም፤ የኮሮና ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅት ከሰራው ንክኪ አልቫ  የዕጅ መታጠቢያ ማሽን በተጨማሪ በርቀት የሰዎችን ሙቀት መለካት እና ናሙና መሰብሰብ የሚችል  ሰው አልቫ አውሮፕላን ወይም ድሮን ለመስራት አቀደ።ምንም እንኳ በወቅቱ ሰው አልቫ አውሮፕላኑን ሰርቶ ላቀደው ዓላማ ማዋል ባይችልም በዚህ ስራው ጥሩ ሙከራ ማድረጉን ገልጿል።ከዚህ ሙከራው በመማርም ሁለተኛውን እና ለተለያዩ ግልጋሎቶች የሚውለውን ሰው አልቫ አውሮፕላን  በተሳካ ሁኔታ መስራት ችሏል።
በዚህ ሁኔታ ፊቱን  ወደ ሰው አልቫ አውሮፕላን ስራ ያዞረው ኢብራሂም እስካሁን አራት ድሮኖችን የሰራ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ደግሞ በአይነቱ ለየት ያለ አምስተኛ ድሮን ሰርቶ ማጠናቀቁን ገልጿል።ኢብራሂም እንደሚለው ይህ ሰው አልቫ አውሮፕላን ሁለት ባትሪ ያለው ፣በሶላር የሚሰራ፣ አየር ላይ ሆኖ ባትሪ መቀየር የሚችል እና ረዘም ያለ ስዓት አየር ላይ መቆየት የሚችል ነው።
ወጣቱ በዚህ  ስራው  የፈጠራ መብት ለማግኘት እና በአፍሪካ ድንቃድንቅ ላይ ለማስመዝገብ እንዲሁም ምርቱ በኢትዮጵያ ብቻ የሚመረት ብቸኛ ቴክኖሎጂ እንዲሆን እየሰራ መሆኑን አመልክቷል። ለዚህም የሚማርበት የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ  እና አንዳንድ አካላት ድጋፍ እንደሚያደርጉለት ቃል መግባታቸውንም ተናግሯል።የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ  የምርምር ስራውን እንዲያከናውን የመስሪያ ቦታ  በማመቻቸት አቅሙን አውጥቶ እንዲሰራ እያበረታታው በመሆኑ ለተቋሙ ከፍተኛ ምስጋና አለው።
ያም ሆኖ የመረጃ እጥረት ለፈጠራ ስራ ግብዓት የሚሆኑ ዕቃዎች አቅርቦት ችግር እና የገንዘብ እጥረት በዘርፉ የሚታዩ ተግዳሮቶች በመሆናቸው የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡ ጠይቋል።
 በሌላ በኩል የድሮን ቴክኖሎጅ በአግባቡ እና በሃላፊነት ስሜት ካልተያዘ ለጥፋት ሊውል ይችላል እና  በመመሪያ እና በህግ ማዕቀፍ ውስጥ መስራትን ይጠይቃል።ስለሆነም በዘርፉ  መስራት መብት ብቻ ሳይሆን ግዴታዎች ያሉት  እና ሀላፊነትን የሚጠይቅ ጉዳይ ጭምር ነው።ይህንን በመገንዘብም  ኢብራሂም ስራዎቹን ከሚመለከታቸው የኢትዮጵያ ሚንስቴር መስሪያቤቶች ጋር አብሮ እየሰራ መሆኑንም ገልጿል። እንደ ኢብራሂም የድሮን ቴክኖሎጅ ለተለያዩ ተግባራት የሚውል ቢሆንም፤ እሱ ግን የህብረተሰቡን የዕለት ተዕለት ህይወት ለማሻሻል በሚጠቅም መልኩ እንደሚሰራ ተናግሯል።

Ibrahim Ali, junger Unternehmer in Äthiopien
ምስል privat
Ibrahim Ali, junger Unternehmer in Äthiopien
ምስል privat

«ያው ድሮን ለብዙ አገልግሎት ይውላል። በጣም በጅግ ዘመናዊ የሆነ ቴክኖሎጂ ነው።ለጦርነት ከተጠቀምነው  በትክክል ለጦርነት ማገልገል  የሚችለው ነው።ለልማት ችግሮችን ለመቅረፍ ከተጠቀምን ደግሞ የማህበረሰቡን ችግር ለማቃለል ይውላል።ለምሳሌ ለህክምና አቅርቦት አስፈላጊውን  «ማቴሪያል» በድሮን ማጓጓዝ ብንችል ህይወት ለማዳን ብንጠቀምበት፤ ከተማ ውስጥም በድሮን ዕቃ ብናጓጉዝ የትራፊክ አደጋን መቀነስ እንችላለን። በጣም ትልቁ የሰው ልጅ ህይወትን መታደግ የምንችልበትም ነው። እና ለታዳጊ ሀገር ድሮን ማበልፀግ ያለብን ችግሮችን መቅረፍ የሚችሉ ድሮች ነው።» 

ወጣቱ በልጅነቱ የሰነቀውን ህልም ዕውን ለማድረግ በትምህርትና በልምድ እያጎለበተ፣እንዲሁም  ከስህተቱ እየተማረ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ ደርሷል።ይህንን የዘወትር ጥረቱን በመቀጠልም ለወደፊቱ ማሳካት የሚፈልገው ሁለት ዕቅዶች አሉት።አንደኛው ድሮኖችን ከማሳያነት ባሻገር ወደ ምርት እና አገልግሎት በመቀየር ኢትዮጵያን በዚህ የቴክኖሎጅ ምርት ስሟን ማስጠራት ሲሆን፤ ሁለተኛው ዕቅዱ ደግሞ የፈጠራ ባለሙያዎችን ችግር የሚቀርፍ ትልቅ ድርጅት መመስረት ነው።

«ወደ ፊት በጣም ብዙ ዓላማዎች አሉኝ።  ከነዚያ ውስጥ አንዱ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ የተመረተ ድሮን መስራት እፈልጋለሁ።ሁሉንም  ችፍሮች ለመፍታት የሚችል። ብዙ ችግሮችንና ክፍተቶችን መሸፈን የሚችል ድሮን መስራት ፈልጋለሁ። ድሮን የሚያመርት የራሴ የድርጅት ኢንኖረኝ እፈልጋለሁ። ሁለተኛው ዓላማዬ ደግሞ  የፈጠራ ስራ  ባለሙያዎችን ችግር መቅረፍ የሚችል የአሁኑንም  የቀጣዩንም ትውልድ በፈጠራ ላይ ያሉ ችግሮችን መቅረፍ የሚችል አንድ ትልቅ ድርጅት መመስረት ፈልጋለሁ። እነዚህን እነዚህ ሁለቱም ባሳካ  ወደፊት ልቅ ለውጥ አመጣለሁ ብዬ እየሰራሁ ነው።» በማለት ገልጿል።

 

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።


ፀሀይ ጫኔ
ሽዋዬ ለገሰ