1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዳይስፖራው ሚና

ሐሙስ፣ ሐምሌ 9 2012

ፍርንክፈርት የሃጫሉን ግድያ በመቃወም የተካሄደው ሰልፍ ታዳሚዎች የዶቼቬለን ዘጋቢ«የኢትዮጵያ መንግሥት ሰላይ»በማለት ለመተናኮል ሞክረው ነበር።ይህ ዓይነቱ ሙከራ ከ1ዓመት በፊት አቶ ጀዋር መሐመድ ኑርበርግ ጀርመን በመጡበት ወቅት የአቶ ጀዋርን ጉብኝት እንቃወማለን ባሉ ሰልፈኞች፣ለመዘገብ በስፍራዉ በነበረ በሌላ የዶቼቬለ ዘጋቢ ላይም ተቃጥቶ ነበር

https://p.dw.com/p/3fIEs
Deutschland Protest gegen Mord an Hachalu Hundessa in Frakfurt
ምስል DW/E. Fekade

የዳይስፖራው ሚና

በሌላ በኩል ከድምጻዊው ግድያ በኋላ በርካታ ንጹሀን ያለ አበሳቸው መገደላቸውን፣ባለሃብቶችና ግለሰቦች ጥረው ግረው ያፈሩት ሃብትና ንብረት ሃይ የሚል ጠፍቶ ዶግ አመድ መሆኑም በዳያስፖራው ክፉኛ ተወግዟል።በደቦ በተፈጸሙ ጥቃቶች የተፈፀመዉ ወንጀል እንዲጣራ፣  ተጠያቂዎችም በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ  እየጠየቁ ነው።ከዚሁ ጋር በሥልጣኔ በመጠቁ ፣ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በተዘረጋባቸውና የሕግ የበላይነት በሚከበርባቸው ምዕራባውያን ሃገራት የሚኖሩ ከርቀት ጥላቻን ይዘራሉ፣ ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶችን እና የአመጽ ጥሪዎችን ያስተላልፋሉ የተባሉትን ለፍርድ ለማቅረብ በዝግጅት ላይ እንደሆኑም የተናገሩ አሉ። 
ጀርመን ከ30 ዓመት በላይ የኖሩት ዶክተር ፀጋዬ ደግነህ የምጣኔ ሃብት ባለሞያና የመኪና አምራቹ የመርሰዲስ ቤንዝ ኩባንያ ባልደረባ ናቸው። ዶክተር ጸጋዬ  ከድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ የተከተለው ጥፋት በኢትዮጵያ ይሆናል ብለው ያሰቡት አልነበረም።ጥፋቱን በአንዳንድ የአፍሪቃ ሃገራት የደረሱ እልቂቶችን ወደ ኢትዮጵያም ለማምጣት የተደረገ ሙከራ ሲሉ አውግዘውታል።
ብራሰልስ ቤልጂግ ውስጥ ለምትኖረው ለኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሞያዋ ለወጣት ኅሊና ሙላቱ ጥፋቱ ሊከሰት እንደሚችል ከዚህ በፊት ጠቋሚ ምልክቶች ነበሩ።በኅሊና አስተያየት በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ ችግሩ አሁን የሚገኝበት ደረጃ ላይ ሊደርስ የቻለው በአንዲት ጀምበር አይደለም።ይልቁንም ተዳፍኖ የቆየ፣ለዓመታት ሲሰራበት የቆየ ጉዳይ መሆኑን ነው የምታስረዳው። ለዚህ አብቅቶናል የምትላቸውን ምክንያቶችም እንዲህ ዘርዝራለች።ለዘመናት ተከማችቶ ዘልቋል የተባለው ጥላቻ እንዲወገድ  በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ የበኩላቸውን ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባው ኅሊናም ዶክተር ጸጋዬም ይስማማሉ።ዶክተር ጸጋዬ ዳይስፖራው በተለይ ሃገሪቱን የሚያረጋጋና ሰላም ሊያወርድላት፣ አንድም ሊያደርጋት የሚችል ተግባር ላይ ሊያተኩር ይገባል ነው የሚሉት።ይህም እንደ ዶክተር ጸጋዬ በድህነት የሚማቅቁ በርካታ ዜጎች ላሏት ለኢትዮጵያ ችግሮች ማቃለያ መሠረታዊ ጉዳይ ነው። 
የሃጫሉን ግድያ በመቃወም በአውሮጳ እና በአሜሪካን በተካሄዱ ሰልፎች የተሰሙ የተሳከሩ መፈክሮች ሲያነጋግሩ ሰንብተዋል።በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተሰቀለ ባንዲራ አወረዱ የተባሉ ወጣቶች እዚያው ለንደን የሚገኝ መናፈሻ የቆመ የአፄ ኤይለ ሥላሴ ኃውልትን ማፍረሳቸዉም አጠያይቋል።ኅሊና ይህን ያስከተለው የጥላቻ ንግግር ነው ትላለች።በየሰልፎቹ የሆነውም በየሚኖሩበት ሃገር በሕግ የሚያስጠይቅ ድርጊት መሆኑንም አስገንዝባለች።

ከሳምንት በፊት ፍርንክፈርት ጀርመን የሃጫሉ ግድያ በመቃወም የተካሄደው ሰልፍ ታዳሚዎች፣የዶቼቬለን ዘጋቢ የኢትዮጵያ መንግሥት ሰላይ በማለት ለመተናኮል ሞክረው ነበር።ይህ ዓይነቱ ሙከራ ከአንድ ዓመት በፊት አቶ ጀዋር መሐመድ ኑርበርግ ጀርመን በመጡበት ወቅት የአቶ ጀዋርን ጉብኝት እንቃወማለን ባሉ ሰልፈኞች፣ ጉብኝትና ሰልፉን ለመዘገብ በስፍራዉ በነበረ በሌላ የዶቼቬለ ዘጋቢ ላይም ተቃጥቶ ነበር።በሁለቱም አጋጣሚዎች  ፖሊስ ነበር ባልደረቦቻችንን ከጥቃት ያዳናቸው።ዶክተር ፀጋዬ እንኳን  በጋዜጠኞች ላይ የሚደረግ የጥቃት ሙከራ ሌሎች ቀላል ሊመስሉ የሚችሉ የሕግ መተላለፎች ሳይቀሩ በጀርመን የሚያስጠይቁ መሆናቸውን በምሳሌ ያስረዳሉ።  
በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በውጭም መልኩን ቀይሮ የቀጠለው ተቃውሞ ጥላቻና ሌሎችም ሁኔታዎችን የሚያባባብሱ ድርጊቶች ሃገሪቱን የባሰ ግጭት ውስጥ እንዳይከቷት ሊከላከሉ የሚችሉ ከወዲሁ ሊወሰዱ የሚገባቸው እርምጃዎችን ዶክተር ጸጋዬም ኅሊናም ጠቁመዋል።

Äthiopien Militär Pick-up Truck in Addis Abeba
ምስል Reuters/T. Negen
USA Protest gegen Ermordung eines äthiopischen Sängers
ምስል picture-alliance/AP/E. Frost

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ