ኢትዮጵያ፦ ግጭቱ በአማራ ክልል ትቶት ያለፈው ጠባሳ
በአማራ ክልል ስልታዊ ከተሞች ውስጥ የትግራይ ተዋጊዎች፤ የኢትዮጵያ መንግሥት እና የአማራ ክልል ኃይላት አካባቢውን ለመቆጣጠር ባደረጉት ፍልሚያ መጠነ ሰፊ ውድመት፤ መፈናቀል እና ስቃይ ተከስቷል።
በኮረብታዎቹ ላይ ፍልሚያ
የትግራይ ተዋጊዎች በኅዳር ወር መገባደጃ በመዘዞ ዙሪያ ባሉ ኮረብታዎች ላይ ብርቱ ሽንፈት ደርሶባቸዋል ተብሎ ይታመናል። ተዋጊዎቹ ወደ መዲና አዲስ አበባ እያቀኑ ነበር። እንደ ዐይን እማኞች ከኾነ ውጊያው በአምስት ቀን ነው የተጠናቀቀው። የመድፍ ፍንዳታ በተሰማበት ብርቱ ውጊያ ወቅት በፍራቻ ዉስጥ የነበሩ ነዋሪዎች ከቤታቸው አልወጡም ነበር። በመንገዱ ጠርዝ እና መስኮች ላይ የሰዎች አስክሬኖችም ይታዩ ነበር።
ውድመት መዘዞ ውስጥ
አዩ ብርሃን በኅዳር ወር የትግራይ ተዋጊዎች ከአዲስ አበባ 200 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው መዘዞ መንደርን ሲይዙ ለዘጠኝ ቀናት ጫካ ውስጥ ተሸሽገው ነበር። የ55 ዓመቷ የመዘዞ ነዋሪ ወደ ቀዬያቸው ሲመለሱ ቤታቸው በመድፍ አረር ወድሞ ነው ያገኙት። «[ጫካ ውስጥ] ተርበን እና ተጠምተን ነበር። ሕጻናትም አብረውን ነበሩ። ሁሉንም ነገር ነው ያጣነው፤ ጭራሽ ወደ ቤታችን ስንመለስ ደግሞ የመኖሪያ ስፍራችንን አጥተናል» ሲሉ ለዶይቸቬለ ተናግረዋል።
ሕይወት ቀስ በቀስ ወደቀድሞው እየተመለሰ ነው
ሕወሓት ከማፈግፈጉ በፊት ስልታዊዋ የኮምቦልቻ ከተማን እና ደሴን ለበርካታ ሳምንታት ተቆጣጥሮ ነበር። በከተሞቹ አሁን ሕይወት ቀስ በቀስ ወደ ቀድሞው እየተመለሰ ነው። ሆኖም ግን የምግብ፤ የነዳጅ እና ሌሎች መሠረታዊ ቁሳቁሶች እጥረት አለ። የኤሌክትሪክ ቧንቧ ውኃ አገልግሎት ገና አልጀመረም።
የደሴ ሆስፒታል
ሐኪም ቤቱ ለስምንት ሚሊዮን ሰዎች ሕክምና መስጪያ ነበር። በኢትዮጵያ መከላከያ እና ሌላ ጊዜ በትግራይ ተዋጊዎች የወታደራዊ ሐኪም ቤት ኾኖ አገልግሏል። የአካባቢው ነዋሪዎች የትግራይ ተዋጊዎች ከመሸሻቸው በፊት ሐኪም ቤቱን መዝብረዋል። «መውሰድ ያልቻሏቸውን መድኃኒቶች ከጥቅም ውጪ አድርገዋቸዋል» ሲሉ አሁን የወደመው ሐኪም ቤቱ የኦክስጂን ማዕከል ተጠሪ አቶ መላኩ ሰጤ ተናግረዋል። ክልሉ የኦክስጂን እጥረት ገጥሞታል።
ወሎ ዩኒቨርሲቲ እጅግ ተጎድቷል
የዩኒቨርሲቲ ተቋሙ በመድፍ አረሮች በብርቱ ተጎድቷል፤ ተመዝብሯልም። «በእውነቱ የከፋ ጥፋት ነው» ይላሉ የካምፓሱ ዳይሬክተር አቶ መንገሻ አየለ። ለውድመቱ የትግራይ ተዋጊዎችን ተጠያቂ ያደርጋሉ። «ይኼን አልጠበቅሁም። ይህ ለመጀመሪያ እና ድኅረ-ምረቃ ዲግሪ ልጆቻቸው የሚማሩበት ዩኒቨርሲቲ ነው።» የዐይን እማኞች የዩኒቨርሲቲ ካምፓሱን የግጭቱ ተሳታፊ የሁለቱም ወገን ወታደሮች በተለያየ ጊዜ ተጠቅመውበታል ይላሉ።
የርዳታ መጋዘኖች ተመዝብረዋል
ኮምቦልቻ ከተማ ውስጥ በዐሥራዎቹ የሚቆጠሩ ለዓለም አቀፍ እና የሀገር ውስጥ ሰብአዊ ርዳታ አድራሾች በማከማቻነነት ሲያገለግሉ የነበሩ መጋዘኖች በከፍተኛ ኹኔታ ተዘርፈዋል። የአካባቢው ኃላፊዎች ለዘረፋው የትግራይ ተዋጊዎችን ተጠያቂ ያደርጋሉ። ሆኖም የሰብአዊ ርዳታ ለጋሽ ምንጮች ማኅበረሰቡ ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሶችን በመውሰድ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል ይላሉ። ሌሎች ታጣቂ ቡድኖችም ኋላ ላይ በዘረፋው ተሳትፈዋል ተብሎ ይታመናል።
የጅምላ መቃብር ተራፍ ውስጥ
ተራፍ በተባለችው መንደር 21 ያልታጠቁ ሰላማዊ ሰዎች እና አራት ተዋጊዎች በዚህ ጅምላ መቃብር ውስጥ ተቀብረዋል። ተራፍ በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ውስጥ የምትገኝ ቀበሌ ናት። የኦሮሞ እና ትግራይ አማጺያን በአካባቢው አናሳ የሆኑ የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎችን ለይተው ማጥቃታቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል። የስምንት ዓመት እና የ12 ዓመት ልጆች ከሰለባዎቹ መካከል ናቸው።
በወታደሮች መተኮስ
የ17 ዓመቷ ታዳጊ ወጣት አራቢ ሐሰን አንድ ተዋጊ ቤታቸው ገብቶ ሲተኩስባት ከእናቷ እና ከእህት ወንድሞቿ ጋር ነበረች። «እንደዚህ ቆስሎ ከመኖር መሞት ይሻላል። ምክንያቱም ቁስሉ እጅግ ነው የሚያሰቃየኝ» ስትል አራቢ ለዶይቸ ቬለ ተናግራለች። በስልኩ ላይ የሚታየው የአጎቷ ልጅ በዛኑ ቀን ጎረቤት በሚገኘው ቤት ውስጥ ተገድሏል። የአራቢ እናት ወ/ሮ ፋጡማ በተኩሱ የተነሳ ልጆቿ አሁንም ድረስ ከሰቆቃው አልተላቀቁም።
ተፈናቃዮች በደብረ ብርሃን
ከአዲስ አበባ የሦስት ሰዓት መንገድ ላይ በምትገኘው የደብረ ብርሃን ከተማ ውስጥ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውጊያውን ሸሽተው የተጠለሉ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ይገኛሉ። «አንዳች የሚቀመስ ነገር የለም። እዚህ ህጻናት አብረውን አሉ…ሰው ቤቱን ጥሎ የሸሸውም አንዳችም ነገር ሳይዝ ነው» ይላሉ ከአጣዬ ከተማ የመጡት ወ/ሮ ማሚቱ በላቸው። «አሁን እዚያ ሰላም ነው እያሉን ነው፤ ወደዚያ ብንኼድ ግን ምንም ነገር የለም። የመኖርያ ቤቶቹ በቃጠሎ ወድመዋል።»
ሚሊሺያዎች በጥበቃ ሥራ ላይ
የአካባቢው በጎ ፈቃድ ሚሊሺያዎች አሁንም ድረስ የትግራይ ተዋጊዎችን እያሰሱ ነው። ሚሊሺያዎቹ አነስተኛ ወታደራዊ ሥልጠና ያገኙ ገበሬዎች አለያም ሲቪል ሠራተኞች ናቸው። «ይህን ጉብታ የሕወሓት ርዝራዦችን ለማሰስ እንጠቀምበታለን። ስናገኛቸው በቁጥጥር ስር እናውላቸዋለን» ይላሉ የሸዋ ሮቢትን ሚሊሺያ ቡድን የተቀላቀሉት አቶ ባሕረ ከፈለ። «አካባቢያችን ለቀዋል ብለን ልንዘናጋ አንችልም። መጠንቀቅ ያስፈልገናል።»
የተናጋዉ ኤኮኖሚ
ሸዋ ሮቢት በደሴ አዲስ አበባ ዋናው መንገድ ላይ 50,000 ነዋሪዎች የሚገኙባት አነስተኛ ከተማ ናት። ከተማዋ በትግራይ ተዋጊዎች ለበርካታ ቀናት ተይዛ ነበር። ተዋጊዎቹ በርካታ ባንኮችን እና ሆቴሎችን አውድመው የኤኮኖሚ ድቀት አስከትለዋል። የአካባቢው ባለሥልጣናት ከተማዋ እና ክልሉ ከደረሰው ውድመት እስኪያገግሙ ዓመታት ሊፈጅ እንደሚችል ተናግረዋል።