1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

ኢትዮጵያ በ“ድሮን” መድኃኒቶች ማጓጓዝ ልትጀምር ነው

ረቡዕ፣ ነሐሴ 9 2010

የምስራቅ አፍሪቃዊቷ ሩዋንዳ አነስተኛ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን (ድሮን) በመጠቀም በቀላሉ መድረስ ለማይቻልባቸው የሀገሪቱ ክፍሎች መድኃኒቶች እና ደም ማከፋፈል ከጀመረች ሁለት ዓመት አስቆጠረች። የሩዋንዳን ፈለግ የተከተለችው ኢትዮጵያም ተመሳሳዩን አገልግሎት በሚቀጥለው ዓመት ለመጀመር በዝግጅት ላይ ነች።

https://p.dw.com/p/33DnB
Rwanda Drone Pictures
ምስል DW/G. Kowene

የ“ድሮን” ሙከራ በሳምንታት ውስጥ ይጀመራል ተብሏል

ሩዋንዳውያን የሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) አንቀሳቃሾች በቀን ለበርካታ ጊዜያት አነስተኛ አውሮፕላኖችን ወደ አየር ያስወነጭፋሉ። አንቀሳቀሳቃሾቹ በቀላሉ ከቦታ ቦታ የሚዘዋውሯቸውን እነዚህን ሰው አልባ አውሮፕላኖች የተመለከተ የልጆች መጫወቻ ቢመስሉት አይፈረድበትም።እስከ 80 ኪሎ ሜትር ርቀት መጓዝ የሚችሉት አነስተኛዎቹ አውሮፕላኖች ግን ህይወት የማትረፍ ተልዕኮ ይዘው የሩዋንዳን ተራራማ መልከዓ ምድር በአየር የሚያቆራርጡ ናቸው።

አውሮፕላኖቹ በሆዳቸው ከደም እስከ መድኃኒት ቁሳቁስ ሸክፈው “የሺህ ኮረብቶች ሀገር” የምትባለውን ሩዋንዳ በቀን እስከ 500 ጊዜ ያህል ሲያዳርሱ ይውላሉ። ከሁለት ዓመት በፊት የተጀመረው ይህ የደም እደላ ዛሬ ከመዲናይቱ ኪጋሊ ውጭ ያለውን የደም አቅርቦት 20 በመቶ ለመሸፈን ችሏል። ቴክኖሎጂን የመጠቀም ከፍተኛ ተነሳሽነት አለው በሚል የሚወሰደው የሩዋንዳ መንግስት ይህን አገልግሎት የጀመረው ተቀማጭነቱን አሜሪካ ካደረገው ዚፕላይን ከተሰኘ የቴክኖሎጂ ድርጅት ጋር በመተባበር ነው። የኢትዮጵያ መንግስት ዘግይቶም ቢሆን ተመሳሳይ አገልግሎት ለመጀመር እንቅስቃሴ ጀምሯል። 

Rwanda Drone Pictures
ምስል DW/G. Kowene

በኢትዮጵያ በኩል የሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ቴክኖሎጂን የመጠቀም ተነሳሽነቱን የወሰደው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ነው። በቅርቡ የሚኒስትርነት ቦታውን የተረከቡት ዶ/ር አሚር አማን ጉዳዩ ከዕቅድ ወደ ሙከራ ለመሻገር የሳምንታት ዕድሜ እንደቀሩት ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል። የዕቅዱን መነሻ በማስረዳት ይንደረደራሉ። 

“የድሮን ቴክኖሎጂ ለመጠቀም ያሰብነው እንደሚጠቀመው ድሮን ትልቅ ግብዓቶችን ማድረስ አይችልም። በኪሎ ግራም በጣም  የተወሰኑ ግብዓቶችን ነው ማድረስ የሚችለው። ስለዚህ ኢትዮጵያ ካላት ኢትዮጵያ የመልክዓ ምድር አቀማመጥም ጋር ተያይዞ በጣም ለመድረስ አስቸጋሪ የሆኑ ቦታዎችን ታሳቢ ያደረገ ነው። ሁለተኛ ደግሞ ድንገተኛ ነገሮች ሲከሰቱ ነው። በክብደት ትንሽም ቢሆን ዋጋውም ደግሞ ምናልባት ከመደበኛ አካሄድ የተወደደ ቢሆንም እርሱን ሁለተኛ ከግንዛቤ በማስገባት ነው። ሶስተኛ ከአዋጪነት ጥናት (cost benefit analysis) አንጻር በድሮን ብናደርስ ከሌሎቹ ነገሮች ከምናደርሰው ምን የተሻለ ነገር ያመጣል የሚል ትንታኔ በመስራት ዋና ዋና የሚባሉ ግብዓቶችን ለማድረስ ነው። መጀመሪያ ክትባትን፣ ሁለተኛ ደምን እና ሶስተኛ ደግሞ የቤተሰብ ዕቅድ ላይ ሊያገልግሉ የሚችሉ አቅርቦቶችን ታሳቢ ያደረገ ምክረ ሀሳብ አዘጋጅተን ነው የጀመርነው” ይላሉ ሚኒስትሩ። 

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በእነዚህ መመዘኛዎች ላይ በመመስረት የድሮን ቴክኖሎጂው በሙከራ ደረጃ ስንት ጤና ኬላዎች፣ ጤና ጣቢያዎች እና ሆስፒታሎች መድረስ እንዳለበት መለየቱን ዶ/ር አሚር ተናግረዋል። በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 17 ሺህ የጤና ኬላዎች፣ 3,700 ጤና ጣቢያዎች እና 411 ሆስፒታሎች አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መረጃ ያመለክታል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የሙከራ አገልግሎቱን በሁለት ሳምንት ውስጥ መስጠት እንደሚጀምር ዶ/ር አሚር ገልጸዋል። ለዚህም ይረዳ ዘንድ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አማካኝነት በቻይና ሀገር የተገጣጠመ ድሮን በሚቀጥለው ሳምንት ወደ ኢትዮጵያ ይገባል ብለዋል። እስከ ሚቀጥለው ዓመት አጋማሽ ድረስ የሚቀጥለው የሙከራ አገልግሎት ምንን ታሳቢ አድርጎ እንደሚካሄድ ሚኒስትሩ ያብራራሉ። 

Rwanda Drone Pictures
ምስል DW/G. Kowene

“በመላው ሀገሪቱ በ150 ኪሎ ሜትር ራዲየስ ስድስት ቦታ በሂደት ጣቢያዎች ይቋቋማሉ። እያንዳንዱ ጣቢያ ላይ አራት ድሮን፤ በአጠቃላይ ደግሞ 24 ድሮን በመላው ሀገሪቱ ላይ ይኖሩናል። [ድሮኖቹ] 150 ኪሎ ሜትር ነው የሚጓዙት። አጠቃላይ ደርሶ መልሱ ወደ ሁለት ሰዓት አካባቢ ነው የሚፈጀው። የሚሸከመው አምስት ኪሎ ግራም ዕቃዎች ይሆናል ማለት ነው። የክትባት አቅርቦቶች ወይም ደም ሊሆን ይችላል። እርሱን ታሳቢ ያደረገ አድርገን ነው ሙከራውን የምንሰራው” ይላሉ ዶ/ር አሚር።  

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በፍጥነት ወደ ሙከራ የገባው ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ቢሆንም ከኢትዮጵያ ስፋት እና ፍላጎቱ አኳያ የግል ኩባንያዎችንም ወደፊት እንደሚያሳትፍ ዶ/ር አሚር ተናግረዋል። የቴክኖሎጂ አገልግሎቱን ለማቅረብ ሶስት የሀገር በቀል ኩባንያዎች ከሚኒስቴሩ ጋር መነጋገራቸውን ገልጸዋል። በሩዋንዳ ስኬት ያስመዘገበው ዚፕላይን ኩባንያ በኢትዮጵያም ለመሰማራት ምክረ ሀሳቡን ማቅረቡን እና የኩባንያ ኃላፊዎችም ወደ አዲስ አበባ መጥተው ውይይት ማድረጋቸውን ሚኒስትሩ አስረድተዋል። መስሪያ ቤታቸው ሩዋንዳን ጨምሮ የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ መመልከቱን የሚገልጹት ዶ/ር አሚር በጎ ጎናቸውን እና ተግዳሮቶቻቸውን እየፈተሸ እንዳለ ጠቁመዋል።  

“ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ዋናው ሀሳቡ እነዚህን የድሮን ቴክኖሎጂን ያላቸውን በመንግስትም፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂም ወይም የግል ሴክተሩን አበረታቶ ወደ ስራ ማስገባት ነው። እኛ የራሳችን ድሮን፣ የራሳችን mechansim ውስጥ አንገባም። አንደኛ ከዓላማችን ጋር አይሄድም፤ ሁለተኛ ደግሞ ውጤታማ አያደርግንም። የራሳችን ብዙ ስራ አለ። ስለዚህ በደንብ ድጋፍ ሰጥተናቸው ወደ መስመር ከገቡ በኋላ እኛ አገልግሎቱን ብቻ ነው የምንገዛው። እስካሁን ድረስ የተለያየ ዕቅድ ተሰጥቶናል። በአንድ ጉዞ ከ800 ብር እስከ 1,200 ብር ነው የቀረበልን። ገና ወደ ድርድር አልገባንም። 

አጠቃላይ በዓመቱ የምናዝዘውን ትዕዛዝ፣ የትኞቹን የጤና ተቋማት እንመርጣለን? ፣ ምን ያህል ክብደት ነው የምናመላልሰው? ምን ያህል ምልልስ ነው የምናዝዘው በሚለው መሰረት ዋጋውም መቀነሱ አይቀርም። እርሱን ውይይት ጎን ለጎን እያደረግን ነው። እዚህ ሙከራ ላይ ስራውን እየሞከርን፣ ዋጋውንም እየተደራደርን፣ የጤና ተቋሞችንም በደንብ እያጠበቡ የሚደርሱበትንም ሁኔታ እየሰራን እንገኛለን። በአጠቃላይ የመጀመሪያው ስድስት ወር፣ ከዚያም ሊበልጥ ይችላል አገልግሎት እየተሰጠ፣ በደንብ ሞክረንበት ልክ የሙከራው ጊዜ ሲያልቅ ሙሉ ለሙሉ የምገባበት ይሆናል ማለት ነው” ሲሉ በመስሪያ ቤታቸው እየተደረገ ያለውን ክንውን አስረድተዋል። 

Symbolbild Kinder Impfung Afrika Archiv 2014 Bangui
ምስል AFP/Getty Images/M. Medina

በሩዋንዳ የድሮን ቴክኖሎጂ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣው በደም ስርጭት ላይ ነው። ደምን ጨምሮ ሶስት የህክምና ግብዓቶችን በድሮን ለማጓጓዝ ባቀደችው በኢትዮጵያ ግን ቴክኖሎጂው በሚገባ ይቀይረዋል ተብሎ የሚታሰበው የክትባት ስርጭትን ነው። ዶ/ር አሚር የድሮን ቴክኖሎጂ በደም ስርጭት ላይ የሚያመጣውን ለውጥ አስቀድመው ወደ ክትባት ይሻገራሉ።  

“በአደጋ ጊዜ በተለይም ደግሞ ሆስፒታል ላይ ሆኖ ለምሳሌ ኦ ኔጌቴቭ ብዙም አይገኝም። አንድ ቀብሪ ደሃር ሆስፒታል ላይ ያለ ሰው፣ ወይም ደግሞ መተማ አሊያም በጣም ርቆ አፍዴራ ያለ ሰው በዚያ ሰዓት ኦ ኔጌቴቭ ቢያስፈልገው በአንድ ሰዓት ውስጥ ማድረሱ መቻሉ እርሱም ትልቅ ነገር ነው።  ግን በእኛ ግምገማ ትልቅ ለውጥ አምጪ (game changer) የሚሆነው የክትባቱ ነው የሚሆነው። ምክንያቱም እንደሚታወቀው ክትባት የቀዝቃዛ ሰንሰለቱን (cold chain) ጠብቆ መሄድ አለበት።

ክትባት ማድረስ ብቻ አይደለም። መድረሱ ሊደርስ ይችላል። በትክክል የቀዝቃዛ ሰንሰለቱን ጠብቆ ካልሄደ ግን ውጤታማነቱን እና ብቃቱን (efficiency and potency) አጥቶ ቢወጋ ትርጉም የሌለው ሆኖ ሊደርስ ይችላል።  ለእርሱ በጤና ኬላ ደረጃ፣ በሀገሪቱ ገንዘብ ከዩኔሴፍ ጋር በመሆን የሶላር ፍሪጆችን ለመላ የጤና ኬላዎች ወደ 52 ሚሊዮን ዶላር አውጥተን እያሰራጨን ነው። ስለዚህ ጤና ኬላ ላይ ከደረሰ በኋላ የቀዝቃዛ ሰንሰለቱ መጠበቁን ሶላር ፍሪጅ ስላሰራጨን አስተማማኝ አድርገናል። እስከ ጤና ኬላው እስኪደርስ ግን በትክክል የቀዝቃዛ ሰንሰለቱን ጠብቆ ስላልሄደ ብቃቱን ስለሚያጣ አሁን እነዚህ ድሮኖች ውስጣቸው ፍሪጅ የተገጠመላቸው ናቸው። ሁለተኛ ከአንድ ሰዓት እስከ ሁለት ሰዓት ባለው ውስጥ ነው የሚደርሱት። ስለዚህ የቀዝቃዛ ሰንሰለቱን እና ጥራቱን የጠበቀ የክትባት አገልግሎት ላይ ትልቅ ለውጥ አምጪ ይሆናል” ይላሉ ሚኒስትሩ። 

በደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ ሆስፒታል መምህር የሆኑት ዶ/ር ኤርሚያስ አበባው የመድኃኒት አቅርቦትን ተደራሽ ማድረግ የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ለአንድ የጤና ስርዓት ወሳኝ ከሚላቸው ምስሶዎች መካከል አንዱ ነው ይላሉ። “WHO የራሱ የሆኑ ለጤና ስርዓት በጣም ወሳኝ የሆኑ ማገሮች ብሎ ያስቀመጣቸው የማዕዘን ድንጋዮች አሉ። አንድ የጤና ስርዓት የዘመነ እንዲሆን ከሚያስቀምጣቸው መስፈርቶች መካከል አንደኛው work force ይላል። የጤና ባለሙያ ማለት ነው። ሁለተኛ ደግሞ የጤና አገልግሎት አቅርቦት (health care delivery) ነው። ሶስተኛው ደግሞ አስፈላጊ የሆኑ የመድኃኒት እና የጤና  ግብዓት አቅርቦት እንደ አንድ ወሳኝ የማዕዘን ድንጋይ የሚያስቀምጠው ነው። ከዚያ ባለፈ ደግሞ የጤና መረጃ ስርዓቱን (health information system) እና ሌላውና የመጨረሻው የጤና አመራሩ (leadership and governance) ነው” ይላሉ መምህሩ። 

በኢትዮጵያ ተራ የጤና አገልግሎትን እንኳ በቅጡ ማዳረስ ባልተቻለበት የድሮን መሰል ቴክኖሎጂዎችን ተግባራዊ ማድረግ ቅንጦት አድርገው የሚወስዱ ወገኖች አሉ። የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ግን እንደ ድሮን አይነት የቴክኖሎጂ ውጤቶች ከአደጉት ሀገራት ይልቅ ይበልጥ የሚያስፈልጉት እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ላሉቱ ነው ሲሉ ይከራከራሉ። ቴክኖሎጂው ለጤና ብቻ ሳይሆን ለግብርና ጭምር እንደሚውል የሚጠቅሱት ዶ/ር አሚር ለብዙ አገልግሎቶች መዋል የሚችል ቴክኖሎጂ “በፍጹም ቅንጦት ሊሆን አይችልም” ባይ ናቸው። ከወጪ አንጻርም ቢሆን አዋጪ መሆኑን በምሳሌ አስደግፈው ያስረዳሉ።

Somaliland Reportage Verbindungstraße zwischen Äthiopien und Somaliland
ምስል DW/J. Jeffrey

“እኛ በቀላሉ ለማነጻጸር ለአንድ ወር የሚሆን ክትባት፣ አሁን በተሰጠው ምክረ ሀሳብ መሰረት ወደ ቅናሽ ሳንገባ በ800 ብር በአንድ ሰዓት ውስጥ ወይም ከአንድ ሰዓት እስከ አንድ ሰዓት ተኩል ባለው ማድረስ የሚቻለውን በተለመደው በመኪና ጭነን እንሂድ ብንል የትራንስፖርት ወጪው፣ የሹፌር አበል፣ የነዳጅ የምን የምን ተብሎ በፍጹም አይገናኝም። በብዙ እጥፍ ነው የሚበልጠው። አንዳንድ ጥያቄ ለሚያነሱ ሰዎች ማስተማመኛ ለመስጠት ለምሳሌ ከዚህ አዳማ እዚህም እዚያም ትራንስፖርት ጥሩ በሆነበት ሁኔታ ላይ ድሮን ቴክኖሎጂን በሶስቱ መስፈርቶች መሰረት የአዋጪነት ጥናት (cost benefit analysis) ሳይሰራ አንጠቀመም። 

ነገር ግን ኢትዮጵያ በጣም ሰፊ ናት። በጣም አስቸጋሪ ቦታዎች አሉ። በመኪና የማይደረስበት፣ አንዳንዴ በአህያ፣ በፈረስም፣ አንዳንዴ በግመልም እየተጫነ ሰፊ፣ ረጅም መንገድ የሚኬድባቸው የጤና ተቋማት አሉ። በእነዚህ የጤና ተቋማት በፍጥነት ደርሰን ህይወትን ማዳን መቻላችን ከሁሉ በላይ ትልቅ ምላሽ የሚሆን እና በምንም ገንዘብ የማይገዛ ነው። ለእኔ የሰው ህይወትን ከአንድ ከቁሳቁስ፣ ከግዑዝ ነገር ከዋጋ ጋር እያነጻጸሩ ተገቢ ነው አይደለም የሚለው ውይይት ውስጥ መግባቱ ተገቢ አይመስለኝም። እርሱ ውይይት ውስጥ ከተገባ ደግሞ በደንብ በማስረጃ የተደገፈ በአዋጪነት ጥናት የተሻለ ስራ ሊሰራ የሚችል ቴክኖሎጂ መሆኑን ሳንረጋገጥ እንደማንገባ ማረጋገጫ መስጠት እፈልጋለሁ” ሲሉ ጠያቂዎች ስጋት እንዳይገባቸው ያሳስባሉ። 

ረዳት ፕሮፌሰር ኤርሚያስም እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ድሀ ሀገራት የድሮን ቴክኖሎጂ “ዘመን አመጣሽ በረከት እንጂ ቅንጦት አይደለም” ሲሉ የሚኒስትሩን መከራከሪያ ይደግፋሉ። “አሁን ብዙ ቦታዎች ስታይ የመድኃኒት እና ክትባት አቅርቦት እንደገና ደግሞ ሰው በአደጋም ወይም አንዲት እናት ስትወልድ በወሊድ ምክንያት ብዙ ደም ቢፈሳት የደም አቅርቦት ያስፈልጋል። እና እነዚህን ወሳኝ የሆኑ የህክምና ግብዓቶችን ለማቅረብ ለምሳሌ እስካሁን በምንጠቀምበት የመንገድ ትራንስፖርት ብንሄድ አንደኛ ብዙ ቦታዎች ላይ መንገዶች ተደራሾች አይደሉም። መንገድ ራሱ ያሉባቸው ቦታዎች በሚያስፈልገው ሰዓት፣ የሚያስፈልገው ግብዓት ለማቅረብ ጊዜ ይፈጃል። ህክምና ደግሞ  በጣም በቅጽበት፤ በሰከንዶች ውስጥ የሚስፈልገው ህክምና ካልተደረገ ህይወትን ሊንጠቅ የሚችል፣ ሞትን የሚያስከትል ሙያ ነው ያለውና ከዚህ አንጻር ስናየው እነዚህን አስፈላጊ የመድኃኒት እና ለአንድ ሰው ለህክምና የሚፈልጉ ግብዓቶችን ለማቅረብ ፈጣን የሆነ የዘመኑን ቴክኖሎጂን መጠቀም ግድ ይላል። እና የድሮን ቴክኖሎጂ በጣም አስፈላጊነቱ የሚመጣው እዚህ ላይ ነው።”

ተስፋለም ወልደየስ

ኂሩት መለሰ