1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ ሰላም እየናፈቃት ሰላም የሚጠላባት ምድር

ሰኞ፣ ጥቅምት 29 2014

በተለይ የኢትዮጵያ መንግስት ደጋፊዎች ትብብሩ የተመሰረተዉ ወትሮም ሕወሓትን «ይደግፋል» በሚሉት በአሜሪካ መንግሥት ይሁንታና ድጋፍ ነዉ በማለት ይከሳሉ።አቶ ጌታቸዉ ግን ዩናይትድ ስቴትስ ሕወሓትን ትደግፋለች መባሉን አጣጥለዉ ነዉ የነቀፉት።ይጠይቃሉም «በምን መንገድ» እያሉ።

https://p.dw.com/p/42k1H
Äthiopien | Proteste Regierungsanhänger in Addis Abeba
ምስል Seyoum Getu/DW

ኢትዮጵያ የጦርነቱ ምስቅልቅልና የሰላም ጥያቄ

ዉጊያ፣ የፕሮፓጋንዳ ጦርነቱ ቀጥሏል።ፍተሻ -ቁጥጥሩ፣ የሚገደል፣የሚሰቃይ፣ የሚፈናቀል የሚራብ፣የሚታሰረዉ ሰዉ ቁጥርም አይሏል።የዉጊያ ዘመቻ፣ ዝግጅት፣ ፉከራ ቀረርቶዉም ከአዲስ አበባ አደባባይ እስከ ፌስ ቡክ ገፆች ተጋግሟል።ኢትዮጵያ።ሠላም የለም።አልፎ አልፎ ብልጭ የሚሉ የሠላም፣ የድርድር-ዉይይት ጥያቄ ጥሪዎችም ሰሚ አላገኙም።እንዲያዉም ስለ ተኩስ አቁም፣ሥለ ድርድር-ዉይይት አስፈላጊነት ሐሳብ ያቀረቡ ወገኖች መኖራቸዉን የዘገቡ መገናኛ ዘዴዎችም ባንዱ ወይ በሌላዉ ወገን እንደጠላት እየተወዘገዙ፣ እየተዛተ እየተፎከረባቸዉ ነዉ።ለሐገርና ሕዝብ ይጠቅም ይሆን? በምስቅልቅል ትርምሱ መሐል የሸምጋዮች ጥረት መቀጠሉን የሚጠቁሙ ዘገቦች ብልጭ እያሉ ነዉ።የሩቅ ተስፋ አለዉ ይሆን? የተስፋ ቀቢፀ ተስፋዉ እንዴትነት ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ አብራችሁን ቆዩ።

 የጠመንጃ አፈሙዙ ዉጊያ ሰሜን ሸዋ ደርሷል።በየዉጊያ ቀጠናዉ በሚኖረዉ ሕዝብ ላይ የሚደርሰዉ ግፍ በደል እየከፋ መምጣቱ እየተነገረ ነዉ።የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ኮሚሺኖች ባለፈዉ ሳምንት ሮብ ያወጡት የጥናት ዘገባ ትግራይ ዉስጥ የደረሰዉን የሰብአዊ መብት ጥሰት የሚመለከት ነበር።

ይሁንና የሁለቱ ተቋማት ባለሙያዎች ጥናቱን በሚያደርጉበት ወቅት ወደ አማራና አፋር ክልሎች በተስፋፋዉ ጦርነት ቁጥራቸዉ በዉል ያልተነገረ ሰላማዊ ሰዎች መገደል፣መሰቃየት፣ መበደላቸዉን የሚጠቁሙ ዘገቦች እንደደረሷቸዉ አልሸሸጉም።በአፍሪቃ ሕብረት የምስራቅ አፍሪቃ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ድርጅት ተወካይ ያሬድ ኃይለማርያምም ዉጊያ በሚደረግባቸዉ አካባቢዎች በሚኖረዉ ሕዝብ ላይ የሚደርሰዉን ግፍ በገለልተኛ ወገን ማጣራት አይቻልም።አቶ ያሬድ «ታማኝ» ያሏቸዉ ምንጮች እንደሚናገሩት የሕወሓት ታጣቂዎች በሚቆጣጠሯቸዉ አካባቢዎች ወጣቶችን እየገደሉ፣ሴቶችን እየደፈሩ፣የሰላማዊ ሰዎችን ሐብት ንብረት እየዘረፉና እያጠፉ ነዉ።የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና ቃል አቀባይ ጌታቸዉ ረዳ ግን  በትግራይ ሕዝብ ላይ «ተፈፅሟል» ያሉት ግፍ በሌላ ሕዝብ ላይ እንዲደርስ ፓርቲያቸዉ አይፈልግም።ጥርጣሬዉ በገለልተኛ ወገን እንዲጣራም ፈቃደኛ ነዉ።

Äthiopien | Addis Abeba Olusegun Obasanjo

የዚያኑ ያክል የኢትዮጵያ የፈደራል መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ የአዲስ አበባ መስተዳድር ደግሞ የክተት ጥሪ ካወጁ ካለፈዉ ሳምንት ወዲሕ የርዕሰ ከተማይቱ ፖሊስ   ጠንካራ ፍተሻ፣ ቁጥጥርና የጦር መሳሪያ ምዝገባ እየተደረገ ነዉ።

በፍተሻ-ቁጥጥሩ ፖሊስ  የትግራይ ተወላጆችን በጅምላ ያስራል፣ቤት፣የንግድ ተቋሞቻቸዉን ይመዘብራል የሚል ወቀሳ እየተሰነዘረ ነዉ።የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ፋሲካ ፈንታ ግን ወቀሳዉን ነቅፈዉታል።

ኮምናደር ፋሲካ አክለዉ እንዳሉት ፖሊስ የሰለጠኑና የታጠቁ «የአሸባሪ ቡድን አባላት» ያላቸዉን ሰዎች፣ በርካታ የጦር መሳሪዎች፣የፖሊስና የጦር ሠራዊት የደንብ ልብሶች ይዟል።በፍተሻ፣ ቁጥጥር፣ ሥጋትና የዘመቻ ዝግጅት፣ ዲፖሎማቶችን በማስተናገድና የዉጪ ዜጎችን በመሸኘት ስትጣደፍ ሳምንቱን ያገባደደችዉ አዲስ አበባ የአደባባይ ሰልፍ አስተናግዳም ነበር።ትናንት።

ለኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትና መንግስት ድጋፍ ለመስጠት በተጠራዉ ሰልፍ ላይ የተጋበዘዉ ድምፃዊ ታሪኩ ጋንኪሲ ያስተላለፈዉ የሠላም ጥሪ፣ የመብት ተሟጋቹ ያሬድ ኃይለማርያም እንዳሉት ለሰላም ወዳዶች ተገቢና ወቅታዊ ነበር።

Äthiopien Getachew Reda in Addis Abeba
ምስል DW/Y. Geberegeziabeher

ይሁንና እንደወታደር የጦርነትን አስከፊነት በማየቱ እንደ ድምፃዊ ስለሰላም፣ፍቅር፣ መከባበርና አንድነት የሚያዜማዉ ታሪኩ ትናንት የሰላምን አስፈላጊነት በመናገሩ እስከ ግድያ ዛቻ የደረሰ ዉግዘትና ርግማን እየተፈራረቀበት እንደሆነ ተናግሯል።አጃኢብ እንበለዉ ይሆን?

አልነዉም አላልነዉ ከወራት በፊት ስለ ዉይይት፣ድርድር ሠላም አስፈላጊነት የሚናገሩ ወገኖችን ጥሪ በመዘገባችን በዶቸ ቬለ ጋዜጠኞች ላይ ይወርድ የነበረዉ ርግማን፣ ዉግዘት፣የግድያ ዛቻ ዛሬ ለድምፃዊ መትረፉንም አስተዋልን።

በአፍሪቃ ቀንድ የአፍሪቃ ሕብረት ልዩ መልዕክተኛ ኦሌሴጎን ኦባሳንጆ ትናንት ትግራይ የገቡት አዲስ አበባ ላይ ያስወገዘ፣ ለግድያ ያስዛተዉን የሰላም መልዕክት ይዘዉ ነበር።ኦባሳንጆ ከሕወሓት ሊቀመንበር ከደብረ ፂዮን ገብረ-ሚካኤል ጋር ያደረጉትን ንግግር አቶ ጌታቸዉ ረዳ «ፍሬያማ» ብለዉታል።

ኦባሳንጆ ትግራይ ከመግባታቸዉ ከጥቂት ቀናት በፊት በአፍሪቃ ቀንድ የዩናይትድ ስቴትስ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሬይ ፌልትማን አዲስ አበባ ነበሩ።አሜሪካዊዉ ዲፕሎማት ካለፈዉ ሐሙስ ጀምሮ ከአፍሪቃ ሕብረትና ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር መነጋገራቸዉ ተዘግቧል።

የንግግሩ ዉጤት ግን እስከዛሬ ቀትር ድርስ በዝርዝር አልነገረም።ይሁንና ኦባሳንጆ ወደ ትግራይ የተጓዙት የአሜሪካዉ መልዕክተኛ ከአፍሪቃ ሕብረት ባለስልጣናት ጋር ከተነጋገሩ በኋላ በመሆኑ የሁለቱ መልዕክተኞች ጥረት የተቀናጀ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አሳድሯል።

ዩናይትድ ስቴትስ ልዩ መልዕክተኛዋን ወደ አዲስ አበባ ስትልክ፣ሕወሓትን ጨምሮ የኢትዮጵያ መንግሥትን ለማስወገድ የሚፈልጉ ኃይላት ዋሽግተን ዉስጥ የጋራ ትብብር መመስረታቸዉ ግን ብዙ እያነጋገረ ነዉ።በተለይ የኢትዮጵያ መንግስት ደጋፊዎች ትብብሩ የተመሰረተዉ ወትሮም ሕወሓትን «ይደግፋል» በሚሉት በአሜሪካ መንግሥት ይሁንታና ድጋፍ ነዉ በማለት ይከሳሉ።አቶ ጌታቸዉ ግን ዩናይትድ ስቴትስ ሕወሓትን ትደግፋለች መባሉን አጣጥለዉ ነዉ የነቀፉት።ይጠይቃሉም «በምን መንገድ» እያሉ።

Jeffrey Feltman UN-Untergeneralsekretär
ምስል Getty Images/AFP/R. Arboleda

ለኢትዮጵያ ጉደኛ ሳምንት ነበር።ጦርነት፣ የአስኳይ ጊዜ አዋጅ፣ የአዲስ አበባ ባለስልጣናት ዘመቻ፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት ዘገባ፣ የአደባባይ ሰልፎች፣ የዉጪ ዜጎች ከኢትዮጵያ መዉጣት፣ የአሜሪካና የአፍሪቃ ሕብረት የሰላም ጥረት፣ ስለሰላም የተናገረ የተወገዘ-የተደገፈበት፣አሰሳ፣ ፍተሻ የጠነከረበት፣ መንግስትን ለመጣል የሚሹ ቡድናት ሕብረት የመሠረቱበት--ከሁሉም በላይ የሕዝብ ስቃይ፣ ጭንቀትና ሥጋት ያየለበት----ምንቀረ? ብቻ ሌላ ሳምንት ጀመርን።

ነጋሽ መሐመድ 

አዜብ ታደሰ