1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለዉጥና ቅልበሳ

ነጋሽ መሐመድ
ማክሰኞ፣ ሰኔ 19 2010

«ትናንት ዛሬ አይደለም» እንዲል ድምፃዊዉ 1969 2010 አይደለም።የዚያኑ ያክል «ታሪክ እራሱን ይደግማል» ይላል የታሪክ ሰዉ።አዲስ አበባም ብዙ ፖለቲከኞች እና የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚያምኑት በአርባ አንድ ዓመትዋ ዘንድሮ በመሪዋ ላይ የተቃጣ ሌላ የግድያ ሙከራ አስተናግዳለች።ቅዳሜ።

https://p.dw.com/p/30GL0
Äthiopien Demonstration Untersützung für Premierminister Abiy Ahmed in Addis Ababa
ምስል picture-alliance/Anadolu Agency/M. Wondimu Hailu

ኢትዮጵያ፤ ሠላም እና ግጭት፤ ፍቅርና ጥላቻ

ከኢትዮጵያ ሶማሌ-ኦሮሚያ ድንበር እስከ ሐዋሳ፤ ከወላይታ ሶዶ-ወልቂጤ እስከ ቤኒሻንጉል-ኦሮሚያ ድንበር የጎሳ ግጭት፤ ግድያ ጥፋት፦ የአብሮ መኖር፤ መተባበር (በጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ አገላለፅ ከመደመር) ጋር እየተናነቁ ነዉ።ከኢትዮጵያም በላይ የአፍሪቃ አንድነት፤ ትብብር፤ ሠላም እና ብልፅግና  በሚቀመር፤ በሚሰበክ፤ በሚመከርባት አዲስ አበባ፦ የቦምብ፤ ፍንዳታ፤ ግድያ እና ሽብር የሚሊዮኖችን የፍቅር፤ የአንድነት፤ የይቅርታ፤ የሠላማዊ ለዉጥ አቋም፤ድጋፍ ፅናትን ባያጨናግፍ ብዙዎች እንደተስማሙበት ብዙዎችን አሸብሯል።ሚሊዮኖች የቆሙለት የሰወስት ወር ለዉጥ «ዳዴ» ፤27 ዓመት ከደደረዉ የምጣኔ ሐብት ሻጥር  እና ሴራ ጋር እየተናነቀ ነዉ።ኢትዮጵያ።ለምን? እና ወዴት? ላፍታ አብረን እንጠይቅ።

መስከረም 1969 በያኔዉ የጊዚያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ምክትል ሊቀመንበር በኮሎኔል መንግሥቱ ኃያለማርያም ላይ የተቃጣዉ የግድያ ሙኩራ እስከያኔ  በቋፍ የነበረዉን የለዉጥ በጎ ተስፋ ባፍጢሙ ደፍቶ መገዳደል፤ መበቃቀል፤ መጠፋፋት ሽብርን አንግሷል።

የግድያ ሙከራዉ ወትሮም መስመር አብጅተዉ የሚፋተጉትን የለዉጥ ኃይላት ሽብርን እንደ ፖለቲካ አላማ ማስፈፀሚያ እንዲከተሉ ከማድረጉ አልፎ፤ አንጋፋዉ የመላዉ ኢትዮጵያ ሶሻሊስታዊ ንቅናቄ (መኢሶን) አመራር አባል አበራ የማነአብ እንደሚያስታዉሱት «በቃል ኪዳን ተሳሰርን» ይሉ የነበሩትን የደርግ አባላትንም እሁለት ገምሶ «ለምሳ ያሰቡንን ቁርስ አደረግናቸዉ»ን እያስፎከረ ያጫርስ ገባ።

Äthiopien Kundgebung Premierminister Abiy Ahmed in Addis Ababa | Explosion
ምስል Oromo Media Network

                                 

አርባ አንድ አመቱ።«ትናት  ዛሬ አይደለም» እንዲል ድምፃዊዉ 1969 2010 አይደለም።የዚያኑ ያክል «ታሪክ እራሱን ይደግማል» ይላል የታሪክ ሰዉ።አዲስ አበባም ብዙ ፖለቲከኞች እና የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚያምኑት በአርባ አንድ ዓመትዋ ዘንድሮ በመሪዋ ላይ የተቃጣ ሌላ የግድያ ሙከራ አስተናግዳለች።ቅዳሜ።ሙከራዉ በርግጥ አልተሳካም።ሠላማዊ ሰዉ ግን ተገድሏል።ቆስሏል።ተሸብሯልም።ሙከራዉ ካደረሰዉ  በላይ ጉዳት ቢያደርስ ኖሮ ግን መዘዙ ጋዜጠኛ መስፍን ነጋሽ እንደሚለዉ ታሪክ እራሱን ደገመ ከማሰኘትም በላይ በሆነ ነበር።

                                    

የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ (OMN) ሥራ አስኪያጅ እና የፖለቲካ አቀንቃኝ ጀዋር መሐመድ ደግሞ «ኢትዮጵያ ታበፅሕ እደዊሐ ሐብ እግዚብሔር» የተባለዉ ለምን ሆኖ ይላል።

                                          

ጠቅላይ ሚንስትሩ ከሞት-ቁስለት፤ ሐገር፤ ሕዝብ፤ ዳዴ ባዩ ለዉጥም ከጥፋት ተርፈዋል።የጥፋት ሙከራዉ ግን አዲስ አበባ ብቻ ዓይደለም።በጠቅላይ ሚንስትሩ እና በተከታዮቻቸዉ ላይ ብቻም አይደለም።ከኢትዮጵያ-ሶማሌ -ኦሮሚያ ድንበር እስከ ሐዋሳ፤ ከወላይታ ሶዶ-ወልቂጤ እስከ ቤኒሻንጉል የታዩና የሚታዩ ግጭት፤ ግድያዎች የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ለዉጡን ለማደናቀፍ የሚደረጉ የጥፋት ሙከራ አካል ናቸዉ።

የአጥፊ፤አደናቃፊዎቹ ማንነት በግልፅ አያታወቅም።የግጭቱን ጠንሳሾች ስራ-እና ሴራ፤ የቦምብ ፍንዳታዉን ዉጥን፤ከሁሉም በላይ ከዚሕ ቀደም የነበረዉን ሐቅ ገጣጥመዉ የሚያነቡ ተንታኞች ግን ጣታቸዉን የሚቀስሩት ወደተመሳሳይ አቅጣጫ ነዉ።ለዉጡ ያስፈራቸዉ የቀድሞ ወይም አሁንም ያሉ ባለሥልጣናት።ፕሮፌሰር መሐመድ አባጀበል ጣሒሮ አንዱ ናቸዉ።

                               

የጋዜጠኛ መስፍን ነጋሽም አስተያየትም ተመሳሳይ ነዉ።

                       

Äthiopien Addis Abeba - Rally für Premierminister Abiy Ahmed
ምስል DW/G. T. Hailegiorgis

ጀዋር መሐመድ ከግጭት-ግድያ ፍንዳታዉ ዉጤት በፊት ምክንያት ነበር ባይ ነዉ።የአራት ዓመት ትግል እና ድል።

                  

መስፍን ነጋሽ ያክልበታል።አደጋ፤ግጭቱን ያደረሱት ወይም የጠነሰሱት ወገኖች እኒያ የሥርዓታቸዉ ፍፃሜ ያሰጋቸዉ ሆኑም አልሆኑ ሱማሌን-ከኦሮሞ፤ሲዳማን-ከወላይታ፤ ሥልጤን ከጉራጌ ከማጋጨት ማጫረስ፤ ሠልፈኛን ከመግደል-ማሸበር የሚያገኙት ጥቅም ምንነት፤ ከፖለቲካዉ ሴራ ለራቀዉ ኢትዮጵያዊ በርግጥ ግራ ነዉ።ፕሮፈሰር መሐመድ አባጀበር ጣሒሮ ግን የምክንያቱን ምክንያት ይናገራሉ።

                                      

ጀዋር መሐመድ እንደሚለዉ ደግሞ ግጭት፤ሁከት፤ ፍንዳታዉ በምጣኔ ሐብት ሻጥር የታጀበ ነዉ።የፀጥታ ችግርን ከምጣኔ ሐብት ቀዉስ  ጋር ደብለዉ ሕዝብ በፍርሐት እና ሥጋት ሲርድ ሥልጣንን መልሶ መቆጣጠር ነዉ-ግባቸዉ እንደጀዋር።

                                  

አንጋፋዉ ፖለቲከኛ አበራ የማነአብ ግን ግጭት፤ጥቃት፤ ግድያ የምጣኔ ሐብቱ ሴራየተጀመረዉን ለዉጥ ያፋጥነዉ እንደሁ እንጂ አይቀለብሰዉም።

                                      

ፕሮፈሰር መሐመድ አባጀበል ጣሒሮም ለዉጡ አይቀለብስም ባይ ናቸዉ።ዋስትናዉ ግን ለዉጡን ለማደናቀፍ የሚሞክሩ ወገኖች  ላሁኑ ዳባም ሆነ፤ በፊት ለሰሩት ወንጀል መጠየቅ አለባቸዉ።-እንደ ፕሮፌሰር እምነት።

                                  

ዘመኑ ግን ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ እንደሚሉት የይቅርታ ነዉ።ሰዎች ተጠያቂ ካልሆኑ ይቅርታዉ ምንድነዉ ባዮች አሉ።ጋዜጠኛ መስፍን ነጋሽ ወንጀለኛ ተጠያቂ መደረጉን አይቃወምም።ጊዜዉ እና የኢትዮጵያ አቅም ግን ገና ነዉ ባይ ነዉ።

                               

Äthiopien Vorbereitungen zur Kundgebung im Unterstützung zum Premierminister Abiy
ምስል DW/Y. Gebregziabeher

ጠቅላይ ሚንስትሩ እስካሁን የሕዝብ ድጋፍ ሞልቶ ተርፏቸዋል።ባለፉት አራት ዓመታት የመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች ዘመድ-ወዳጁን የገደሉበት ሕዝብ፤ የታሰረ፤የተገረፈ፤ የተፈናቀለ የተዘረፈዉ ሕዝብ ቢያንስ እስካሁን ካሳ አልጠየቀም።ገዳይ፤ገራፊ፤ ዘራፊ ወንጀለኞች ለፍርድ እንዲቀርቡ አልጠየቀምም።ምክንያቱ ተስፋ ሊሆን ይችላል። ለዉጡ እንዳይደናቀፍ ማሰብ፤ ያገኘዉ አንፃራዉ ነፃነት እንዲሰርፅ ወይም ፖለቲከኞች እንደሚሉት ኢትዮጵያዊ «ጨዋ» እና «ታጋሽ» ስለሆነ ሊሆን ይችላል።ግን አልጠየቀም።

መጠየቅ የሚገባቸዉ ወገኖች ሰሞኑን ያየን-የሰማዉነዉን ዓይነት ግጭት፤ግድያ፤ሽብር ካደረሱ፤ ወይም ከቀቀሰቀሱ ወይም የምጣኔ ሐብት ሻጥር ከፈፀሙ ወይም ጥፋት ሻጥሩን ለመከላከል ካልጣሩ ያለመጠያቃቸዉ ምክንያት በርግጥ ያጠያይቃል።ጀዋር መሐመድ ሕዝባዊ አመፅ የ27 ዘመኑን ሥርዓት ባፍረከረከበት ወቅት በገዢዉ ፓርቲ አባል መሪዎች መካከል ስምምነት ነበር ይላል።ፕሮፌሰር መሐመድ አባጀበል ጣሒሮ እንደሚሉት ግን ስምምነቱም፤ ትዕግስቱም፤ ይቅርታዉም አስጊዉን ግጭት፤ ግድያ፤ ጥፋት እና ሴራ አላስቆመም።መጠየቅ ያለበት ሊጠየቅ ይገባል።

                                

ጀዋር መሐመድ እንደሚለዉ ለሐገር አንድነት እና ለሰላም ሲባል ሕዝብ የዘረጋዉ የሰላም እጅ ለዝንተ-ዓለም እንደተዘረጋ አይቀጥልም።መስፍን ነጋሽ የለዉጥ አራማጆቹ እርምጃ፤ የተቆጣዉ ሕዝብ ንቅናቄም ሆነ የቀልባሾቹ ሴራ እና ሻጥር  ከጎሳ ጋር እንዳይያያዝ ይመክራል።ኦሮሚያ እና ኢትዮዮጵያ ሶማሌ ድንበር፤ ደቡብ እና ምዕራብ ኢትዮጵያ ሰዉ የሚያጋድል፤ የሚያፈናቅለዉ ግጭት የጎሳ መልክ እና ባሕሪ የተላበሰ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም።ኢትዮጵያ  ከአርባ ዓመት በፊት የነበረ ታሪኳ መደገሙ ላሁኑ አጠራጣሪ ነዉ።በየስፍራዉ ብልጭ-ድርግም የሚለዉ ግጭት፤ ግድያ፤ ሥርዓተ አልበኝነት ግን ለዉጥ አራማጁን እና ደጋፊዉን ሕዝብ ተስፋ አስቆርጦ የከፋ እንዳያስከትል  ማስጋቱም ሐቅ ነዉ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ