1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ 6ኛውን ምርጫ ነጻ፣ ፍትሐዊ እና ተዓማኒ ማድረግ ይሳካላታል?

እሑድ፣ መስከረም 17 2013

ኢትዮጵያ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሐዊ እና ተዓማኒ ማድረግ ይቻላታል? ምርጫውን ለማራዘም ምክንያት የሆነው የኮሮና ወረርሽኝ ይኸ ውይይት እስከተካሔደበት ዕለት በከፍተኛ ሁኔታ ከተስፋፋባቸው 50 አገራት ኢትዮጵያ አንዷ ናት። በምርጫው ሒደት ወረርሽኙ ቢበረታስ? ይኸ የውይይት መሰናዶ እነዚህን ጉዳዮች ያጠይቃል

https://p.dw.com/p/3j16C
Logo National Election Board of Ethiopia

ውይይት፦ የስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ውስብስብ ፈተናዎች

የጤና ሚኒስቴር እና የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባቀረቡት ምክረ-ሐሳብ መሰረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዚህ አመት 6ኛው አገራዊ ምርጫ እንዲካሔድ ውሳኔ አሳልፏል። ሮይተርስ ያሰባሰበው መረጃ እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ ምርጫውን ለማራዘም ምክንያት የሆነው የኮሮና ወረርሽኝ በከፍተኛ ብዛት ከተስፋፋባቸው 50 አገራት አንዷ ናት። በኢትዮጵያ ይኸ ውይይት እስከተካሔደበት አርብ መስከረም 15 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ በአጠቃላይ 72 ሺሕ 173 ሰዎች በወረርሽኙ ሲያዙ 1 ሺሕ 155 ሰዎች ኮሮና ባስከተለው ሕመም ሳቢያ ሕይወታቸውን አጥተዋል።  

በምርጫው መራዘም የኢትዮጵያን መንግሥት በብርቱ የተቹ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ከድምፃዊ ሐጫሉ ሑንዴሳ ግድያ በኋላ ታስረው ጉዳያቸውን በፍርድ ቤት እየተከታተሉ ይገኛሉ። የኦሮሞ ፌድራሊስት ኮንግረስ አመራሮች የሆኑት አቶ ጃዋር መሐመድ፣ አቶ በቀለ ገርባ እና አቶ ደጀኔ ጣፋ ከታሰሩ መካከል ይገኙበታል። የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ሊቀ-መንበር አቶ እስክንድር ነጋ እና አቶ ስንታየሁ ቸኮል በእስር ላይ ናቸው። የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ብሔራዊ ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ልደቱ አያሌው ታስረው በፍርድ ቤት ዋስትና ቢፈቀድላቸውም ይኸ ውይይት እስከተካሔደበት ዕለት ድረስ አልተፈቱም።

በዚህ ሁኔታ ውስጥ የሚካሔድ ምርጫ ምን ያክል ነፃ፣ ፍትሐዊ እና ተዓማኒ ይሆናል? ምርጫ በተለይ ቅድመ-ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች በርከት ካሉ ደጋፊዎቻቸው እንዲገናኙ ያደርጋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመላ አገሪቱ መራጮች እና ተወዳዳሪዎች መመዝገብ ይጠበቅበታል። በዚህ ሒደት የኮሮና ወረርሽኝ እንዳይስፋፋ ምን ሊደረግ ይገባል?

በዛሬው የውይይት መሰናዶ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የማሕበረሰብ ጤና ትምህርት ቤት ኃላፊ አቶ ትዝአለኝ ተስፋዬ ፣ የፖለቲካ ተንታኝ እና አክቲቪስት የሆኑት አቶ መስፍን አማን እንዲሁም ሌላው አክቲቪስት አቶ አብዶ ቃዲ አባጀበል ተሳትፈዋል።

ውይይቱን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ፦