1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮ ቴሌኮም ስለሰሜን ኢትዮጵያ ሠራተኞቹ

ሐሙስ፣ ጥር 4 2015

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሲካሄድ በነበረበት አካባቢ በተለይ ትግራይ ይሠሩ ከነበሩ የኢትዮ ቴሌኮም 700 ሠራተኞቹ መካከል 200 ያህሉ ወደ ሥራ ገበታቸው ለመመለስ አለማመልከታቸው ተገለጠ። ኢትዮ ቴሌኮም ሥራ ለመጀመር እስካሁን ያመለከቱት 500 ሠራተኞች ብቻ ናቸው ብሏል።

https://p.dw.com/p/4M5Sc
Frehiwot Tamru, CEO Ethio Telecom, in Addis Abeba, Ethiopia at Ethio Telecom
ምስል Hanna Demisie/DW

8.1 ቢሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን ዐሳውቋል

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሲካሄድ በነበረበት አካባቢ በተለይ ትግራይ ይሠሩ ከነበሩ የኢትዮ ቴሌኮም 700 ሠራተኞቹ መካከል 200 ያህሉ ወደ ሥራ ገበታቸው ለመመለስ አለማመልከታቸው ተገለጠ። ኢትዮ ቴሌኮም ሥራ ለመጀመር እስካሁን ያመለከቱት 500 ሠራተኞች ብቻ ናቸው ብሏል። ኢትዮ ቴሌኮም ሐሙስ ጥር 4 ቀን፣ 2015 ዓ.ም በሰጠው መግለጫ በ2015 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት 8.1 ቢሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱንም ዐሳውቋል። የአዲስ አበባ ወኪላችን ሐና ደምሴ ዝርዝር ዘገባ ልካልናለች።  
 
የኢትዮ ቴሌኮም በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ተቋርጦ የነበረውን የደንበኞች አገልግሎት መልሶ ማስጀመር በተቻለባቸው አካባዎች በተለይ በትግራይ ክልል ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ከነበሩት 700 ሠራተኞቹ መካከል ወደሥራ ገበታቸው ለመመለስ እስካሁን 500 ያህል ሠራተኞች ብቻ ሪፓርት ማድረጋቸውን የኢትዮጵያ ቴሌኮም ሥራ አስኪያጅ ፍሪሕይወት ታምሩ ተናግረዋል። 

ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ ጦርነት ሲካሄድባቸው በነበሩ አካባቢዎች ተቋርጦ የነበረውን አገልግሎት በአፋጣኝ ለማስጀመር ቅድሚያ በመስጠት አገልግሎቶች መጀመራቸውን ገልጸዋል። ጦርነት ሲካሄድባቸው በቆዩ አካባቢዎች በነበሩት የቴሌኮም አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ላይ የደረሰው ጉዳት ምን ያህል እንደሆነ የዳሰሳ ጥናት እየተደረገ መሆኑን ጥናቱ ሲጠቃለል በአሐዝ እንደሚያሳውቁ ተናግረው በግማሽ የበጀት ዓመት በተለይ በሰሜን እንዲሁም በምዕራብ የሀገሪቱ ክፍል የሚገኙ አእካባቢዎች በግጭት እምሮ በተከሰተ ችግር፤ ወደ 2,716 የሞባይል ኔትዎርክ ሳይቶቹ እንዲሁም 145 የመደበኛ ሳይቶቹ ሥራ ያቋረጡ መሆኑን ገልጿል። 

Äthiopien Telecom 5G Internet Service
የኢትዮ ቴሌኮም 5G ኢንተርኔት አገልግሎት ማብራሪያ ሠሌዳምስል Solomon Muchiee/DW

ተቋሙ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወር 33.8 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ ማግኘቱን ያስታወቀ ሲሆን፤ የግማሽ ዓመቱ ገቢ ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ5.62 ቢሊዮን ብር ዕድገት ማሳየቱን እንደዚሁም የውጭ ምንዛሪ ከሚያስገኙ አገልገሎቶች 64.8 ሚሊዮን ዶላር አግኝቷል ተብሏል።  የአገልግሎት ጥራት ማሻሻያዎች እና አዳዲስ አገልግሎቶችን ወደ ሥራ ማስገባቱ ለገቢው መሻሻል ምክንያት መሆኑ የኢትዮ ቴሌኮም ሥራ አሰፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ተናግረዋል።

የኢትዮ ቴሌኮም አዲስ የግንኙነት ማዕከል

በሰው ሠራሽ ችግር ምክንያት ለሁለት ዓመታት ሲታመሱ በነበሩ አካባቢዎች ተቋርጦ የነበረውን የደንበኞች አገልግሎት ለማስጀመር እንደዚሁም የቴሌኮም መሰረተ ልማት እና አገልግሎት ለማስቀጠል ሠራተኞቸው ከፍተኛ መስዋእትነት እየከፈሉ መሥራታቸው ተገልጧል። በዚህም ድርጅቱ በግማሽ ዓመቱ አሳካዋለሁ ካለው እቅዱ 96 ከመቶ ማሳካቱን   ሥራ አስፈፃሚዋ ተናግረዋል። በተለይ በቅርቡ ተፎካካሪ በመሆን በሀገሪቱ አገልግሎት ለመስጠት ወደ ሥራ ከገባው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ጋር በተያያዘ ሰሞኑን በሰመራ ለሰአታት ስለደረሰው የኔት ወርክ መቆዋረጥ ችግርም ገለጣ አድርገዋል። ጉዳዩ በኮምንኬሽን ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት የተያዘ መሆኑን ተናግረው በኢትዩ ቴሌኮም ላይ የደረሰውን የጉዳት ካሳ ለመጠየቅ ጉዳዩ በሕግ ተይዟል ብለዋል።

የደንበኞቼ ቁጥር ከባለፈው ጋር ሲነጻጻር የ9.2 ሚሊዮን ዕድገት አለው ያለው ኢትዮ ቴሌኮም በአሁኑ ወቅት 70 ሚሊዮን ደምበኞቼ ጋር በመድረስ አገልግሎት እየሰጠሁ ነው ብሏል።

ሐና ደምሴ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ