1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢቦላ ዳግም በከጎንጎ?

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 10 2012

ኮንጎ ከኢቦላ ነጻ ኾናለች ብሎ ለማወጅ የዓለም ጤና ድርጅት ቀነ ቀጠሮ ይዞ የነበረው ባለፈው ማክሰኞ ነበር። በመላ ኮንጎ ለ42 ቀናት በኢቦላ ተሐዋሲ የተያዘ አንድም ሰው አለመኖሩ ነበር በኮንጎ ኢቦላ ጠፍቷል የሚል እምነት ያሳደረው። ኾኖም  ባለፈው ሳምንት ዐርብ ብዙዎችን ያስደመመ ነገር ተከሰተ።

https://p.dw.com/p/3b5Wf
Symbolbild Masernkrise
ምስል picture-alliance/AP Photo/J. Delay

ነዋሪዎች ኢቦላ የገቢ ምንጭ ኾኗል ሲሉ ያማርራሉ

ኮንጎ ከኢቦላ ነጻ ኾናለች ብሎ ለማወጅ የዓለም ጤና ድርጅት ቀነ ቀጠሮ ይዞ የነበረው ባለፈው ማክሰኞ ነበር። በመላ ኮንጎ ለ42 ቀናት በኢቦላ ተሐዋሲ የተያዘ አንድም ሰው አለመኖሩ ነበር በኮንጎ ኢቦላ ጠፍቷል የሚል እምነት ያሳደረው። ኾኖም  ባለፈው ሳምንት ዐርብ ብዙዎችን ያስደመመ ነገር ተከሰተ። አንድ የ26 ዓመት ወጣት የኮንጎ ዜጋ በተሐዋሲው ተጠቅቶ መሞቱን የሀገሪቱ መንግስት ይፋ ማድረጉ ተስፋው ላይ ውኃ ቸልሶበታል። የጤና ባለሞያዎች ከወጣቱ ጋር ንክኪ ሊኖራቸው ይችላሉ ብለው የሚገምቷቸውን ሰዎች በማፈላለግ ላይ ናቸው። 

በኮንጎ የኢቦላ ተሐዋሲ ድል ተመትቷል ሲል የዓለም ጤና ድርጅት ሊያውጅ በተቃረበባቸው ቀናት የ26 ዓመቱን ወጣት ጨምሮ ሦስት ሰዎች በተሐዋሲው መጠቃታቸውን የኮንጎ መንግሥት ዐስታውቋል። ሦስቱም ሰዎች ነዋሪነታቸው በሰሜን ምሥራቃዊ ኮንጎ ቤኒ ውስጥ ነው። የኢቦላ ተሐዋሲ በብርቱ ባጠቃት የሰሜን ኪቩ አውራጃ ውስጥ በምትገኘው የቤኒ ከተማ የ26 ዓመቱ ወጣት ለኹለት ሳምንታት ታሞ እንደሞተ እና አንድ የአካባቢ የባሕል መድኃኒት ዐዋቂ ዘንድም ኼዶ ነበር ተብሏል። የቤተ ሙከራ ምርመራ ውጤት ወጣቱ በኢቦላ ተሐዋሲ መሞቱን ቢያረጋግጥም የቤኒ ከተማ ነዋሪዎች ግን ያን የሚቀበሉ አይመስልም። ኬሲቶ ቢናንጊ የበርካታ ሲቪል ማኅበረሰብ ቡድኖች ተወካይ ናቸው።

England | Coronavirus | Strensall, North Yorkshire
ምስል picture-alliance/dpa/empics/PA Wire/O. Humphreys

«በርካታ የቤኒ ነዋሪዎች እና የሕክምና ባለሞያዎች እኛ ጋር መጥተው አመልክተዋል።

በመላው ኮንጎ በኢቦላ የተጠቃ የመጨረሻው ሰው ከተመዘገበበት 52 ቀናት በኋላ  በድንገት አንድ ሰው ላይ ተሐዋሲው ሊገኝ ቻለ መባሉን እንደሚጠራጠሩ ገልጠዋል።»  

በርካታ ሰዎች አንድ ሰው ላይ ተሐዋሲው ተገኘ መባሉ የፈጠራ ነው ባይ ናቸው። ለዚያ ደግሞ ምክንያታቸው ከውጭ ሃገራት ኢቦላን ለመዋጋት በሚል የመጡ ሰዎች ጠቀም ያለ ገንዘብ የሚያገኙበት ስለኾነ ነው የሚል ነው።

ይኽ አለመተማመንም ኢቦላን ከአካባቢው ለማጥፋት በሚደረገው ዘመቻ ላይ በአጠቃላይ የነበረ ነው። በአካባቢው በብርቱነቱ በኹለተኛ ደረጃ የሚጠቀሰው የኢቦላ ወረርሽኝ ከ20 ወራት በፊት ከተቀሰቀሰ በኋላ 2300 ሰዎች በኢቦላ ተሐዋሲ ሞተዋል። ኮንጎ ውስጥ ባለፉት 44 ዓመታት የኢቦላ ወረርሽኝ ሲቀሰቀስ የዛሬ ኹለት ዓመቱ ዐሥረኛው ነበር።  

ፓስካል ማፔንዚ ሙሂንዶ ከተማዪቱ ቤኒ ውስጥ የሚገኝ «ራዲዮ ሞቶ» የተባለ የግል ጣቢያ ኃላፊ ናቸው። ባለፉት ወራት ማኅበረሰቡ ራሱን ከኢቦላ ተሐዋሲ እንዴት እንደሚጠብቅ ለማስተማር የቦዘኑበት ጊዜ የለም።

«ርዳታው ሲጨምር ከተለያየ ዓለማት በርካታ ነጮች መጉረፋቸውን ዐየን። ሰዉ ግራ በመጋባት የሚጠይቀው፦ ኹሉም በድንገት እንዴት ይመጣሉ? ዓመታት ስንሰቃይ ዞር ብሎ ያላየን ኹሉ ዛሬ በድንገት ሊረዳን መጉረፍ ጀመረ። ከዚህ ታሪክ ጀርባ ግን ምንድን ነው ያለው

በምስራቅ ኮንጎ የእርስ በእርስ ግጭቱ ለዐሥርተ ዓመታት እንደቀጠለ ነው። ነዋሪዎች ከቀዬያቸው ይባረራሉ፤ በዐስር ሺህዎች ዛሬም ድረስ ስደት ላይ ናቸው፤ በዚሁ በኢቦላ ተሐዋሲ የተነሳ። ይራባሉ ይጠማሉ። ከኢቦላ በባሰ እንደ ፈንጣጣ፣ ወባ እና ኮሌራ ያሉ በሽታዎች በርካታ ሰዎችን ቢፈጁም ዓለም ብዙም ትኩረት አልሰጣቸውም።

Symbolbild Coronavirus und Ebola

ከምንም በላይ ታዲያ የሀገሬው ሰው ከውጭ ለርዳታ ብለው የሚመጡ ሰዎችን በጎሪጥ ነው የሚመለከታቸው፤ የኮንጎ መንግስትንም እንደዛው። ያም በመኾኑ የቤኒ ነዋሪዎች መንግስት የምርመራ ውጤቱን በተለያዩ ቤተ ሙከራዎች ደጋግሞ ሊያጣራ ይገባል ባይ ናቸው። የቤኒ ከንቲባም የነዋሪውን ሐሳብ ይደግፋሉ።   

«አኹን ባለው ኹኔታ ቢያንስ ሟቹን የሚያውቊት ሰዎች ኢቦላን ከሚዋጋው ቡድን ጋር መነጋገር አለባቸው። ያ ሲኾን ብቻ ነው ኹኔታው ከቊጥጥር ውጪ እንዳይወጣ መከላከል የምንችለው።»  

ያ በእርግጥም ወሳኝ ነገር ነው። ምክንያቱም በምሥራቅ ኮንጎ አኹን ኢቦላ ብቻ አይደለም ችግር የኾነው። የኮሮና ተሐዋሲም የነዋሪው ስጋት ኾኗልና።  እስከ ትናንት አመሻሹ ድረስ ብቻ 287 ሰዎች ኮንጎ ኪንሻሳ ውስጥ በኮቪድ 19 ተሐዋሲ ተጠቅተው ከ20 በላይ ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል።

ቤቲና ሩይኅል/ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ