1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢሳያስ እና አብይ የአንድ ለአንድ ውይይት ጀምረዋል

እሑድ፣ ሐምሌ 1 2010

የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና የኢትዮጵያው ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ የአንድ ለአንድ ውይይታቸውን ጀምሩ። በጠ/ሚ አብይ የሚመራዉ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ከአስመራ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እስከ ኤርትራ ቤተ-መንግሥት በነበረው ጉዞ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል።

https://p.dw.com/p/312yf
Äthiopien Präsident  Isaias Afwerki und Premierminister Abiy Ahmed in Asmera
ምስል Yemane G. Meskel/Minister of Information

የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና የኢትዮጵያው ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ የአንድ ለአንድ ውይይታቸውን ጀምሩ። የኤርትራው የማስታወቂያ ምኒስትር አቶ የማነ ገብረ መስቀል ውይይቱ "መከባበር፣ ሉዓላዊነት፣የግዛት አንድነት፣ እኩልነት፣ እና የሁለቱን አገሮች የጋራ ጥቅም መሰረት ያደረገ ፈጣን እና አዎንታዊ ለውጥ" ለማምጣት የሚያስፈልገውን አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል ሲሉ በትዊተር ገፃቸው ፅፈዋል። 
ጠቅላይ ምኒስትር አብይ ዛሬ አስመራ ሲደርሱ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ሞቅ ያለ አቀባበል አድርገውላቸዋል። በአስመራ ጎዳናዎች የኤርትራ እና የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማዎችን የሚያውለበልቡ፣ የሁለቱ መሪዎች ምስሎች የታተሙባቸው ቲ-ሸርቶች የለበሱ ኤርትራውያን የአቀባበል መርኃ-ግብሩን አድምቀውት ታይቷል። 
አብረዋቸው የተጓዙት የጠቅላይ ምኒስትር ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍጹም አረጋ ከአስመራ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እስከ ኤርትራ ቤተ-መንግሥት በነበረው ጉዞ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ደማቅ አቀባበል እንደተደረገለት ገልጸዋል። ሰላም እንዲወርድ ያለው ፍላጎት በግልጽ የሚታይ ነው ያሉት አቶ ፍጹም ለሕዝቦቻችን ጥቅም ስንል በእርግጠኝነት ወደ ፊት እንራመዳለን ብለዋል። ጉብኝቱ በሁለቱ አገሮች መካከል ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት እንደሚያጠናክርም ገልጸዋል። 
የኤርትራው ማስታወቂያ ምኒስትር አቶ የማነ ገብረ መስቀል በግል የትዊተር ገፃቸው "እውነተኛ ታሪካዊ ጊዜ"ብለውታል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአስመራ ሲደርስ ከ20 አመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን የማስታወቂያ ምኒስትሩ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን አስመራ ከመድረሱ ቀደም ብሎ አቶ የማነ ጉብኝቱ "የሰላም እና የትብብር አዲስ ዘመንን ያበስራል" ብለው ነበር። 
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌድሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤዎች ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል እና ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሒም፣  ውጭ ጉዳይ ምኒስትሩ ወርቅነህ ገበየሁ እና የመንግሥትየኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ አሕመድ ሽዴ ከልዑካን ቡድኑ መካከል ይገኙበታል። 
ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ አቦ ሸኔ ተብሎ የሚጠራው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር አንድ አንጃ ሊቀ-መንበር አቶ ዳውድ ኢብሳን ወደ ኢትዮጵያ ይዞ ለመመለስ ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውም ተሰምቷል። የኦሕዴድ የድርጅትና የገጠር አደረጃጀት ጉዳዮች ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ቂጢሳ በግል የፌስቡክ ገፃቸው ባሰፈሩት አጠር ያለ ፅሁፍ ጠቅላይ ምኒስትሩ አቶ ዳውድን ለመመለስ ጥረት እያደረጉ መሆኑን ከመጠቆም ባለፈ ያሉት ነገር የለም።
 

Äthiopischer Ministerpräsident Abiy Ahmed beim Staatsbesuch in Eritrea
ምስል Twitter/@fitsumaregaa

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ