1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኡስማን ዳን ፎዲዮ የህይወት ታሪክ ምን ይመስላል?

Muhammad Al Amin
ዓርብ፣ የካቲት 27 2012

ኡስማን ዳን ፎዲዮ በሀውሳ ግዛት ውስጥ እስከ 15ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ወደ ኃላ የሚዘልቅ ታሪክ ያለው የቀድሞ የፉላኒ ሰፋሪዎች ተወላጅ ናቸው። ታዋቂ የእስልምና አስተማሪ እና ሰባኪም ነበሩ።

https://p.dw.com/p/3YRWf
DW African Roots | Sheikh Usman dan Fodio

የኡስማን ዳን ፎዲዮ የህይወት ታሪክ ምን ይመስላል?
ኡስማን ዳን ፎዲዮ እ.ኤ.አ. ታህሳስ 15 ቀን 1754 ዓ ም ማራታ መንደር ውስጥ ተወለዱ። ይህ መንደር የሀውሳ ቋንቋ በሚነገርበት የጎቢር ግዛት እና የዛሬዋ ሰሜን ናይጄሪያ ውስጥ ይገኛል። እሳቸውም ኒጀር ውስጥ በምትገኘው የአጋዴዝ ከተማ የህግ ፣ ሥነ-መለኮትን እና ፍልስፍና ተማሪ ነበሩ። መምህራቸው ደግሞ እስላማዊው ምሁር ጂብሪል ኢብን ዑመር ነበሩ። ኡስማን በነበራቸው ሃይማኖታዊ እውቀት እና ክብር ምክንያትም ሼህ ኡስማን እየተባሉ ይጠሩ ጀመር።  

ኡስማን ዳን ፎዲዮ የገዥውን ስርዓት እንዴት ተቃወሙ?
ኡስማን ትምህርታቸውን ከጨረሱ በኋላ ወደ ጎቢር በመመለስ እስልምናን ከአረማውያን ጋር ለሚደባልቀው ህዝብ እስልምናን ያስተምሩ ጀመር። ኡስማን ጎቢር ውስጥ ዝናቸውም እየጨመረ ሄደ። ይህ ደግሞ ለዚያን ዘመን የጎቢር ንጉሥ ሪምፋ ስጋት ነበር። ስለሆነም ንጉሡ ኡስማን ዳን ፎዲዮን ሊያስፈራሩ እና ሊገሏቸው ሞከሩ። በዚህም የተነሳ ኡስማን  ወደ ገጠራማ መንደር በመሸሽ የአካባቢውን ማህበረሰብ ይሰብኩ ፣ ያስተምሩ እና ይፅፉ ጀመር ፡፡
እ.ኤ.አ. በ 1803 ሼህ ኡስማን እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ተከታዮቻቸው እስልምናን ለማስፋፋት ወደ ጉዱ ተሰደዱ፡፡ ኡስማን ዳን ፎዲዮ ጉዱ በነበሩበት ወቅትም በጎቢር ንጉስ ዩንፋ (የሪምፋ ልጅ እና አልጋወራሽ) ላይ ቅዱስ ጦርነት ወይም ጂሃድ አወጁ። ጦርነቱ በህዝባቸው ላይም ጭምር ነበር። ምክንያቱም የህዝቡ አኗኗር እስልምና ከሚያስተምረው ጋር ይጣጣማል ብለው ስለማያምኑ።
ኡስማን ዳን ፎዲዮ እንዴት የሶኮቶ ካሊፋትን አቋቋሙ?
የቅዱስ ጦርነቱ አዋጅ በመላው ሀውሳ ተሰራጭቶ ብዙ ሰዎች ወደ ሠራዊቱ ለመቀላቀል ፈቃደኞች ሆኑ፡፡ እ.ኤ.አ. በ 1804 ዓ ም በመላ ሀውሳ በይፋ ጦርነቱን አወጁ ፡፡ በ1808 ኡስማን እና ተከታዮቻቸው ጎቢር ፣ ካኖ እና ሌሎች የሀውሳ ግዛቶችን ከተሞች በቁጥጥራቸው ስር አደረጉ። እሳቸውም እ.ኤ.አ. በ 1811 ዓ ም ከጦርነት ተመልሰው   ማስተማራቸውን እና መፃፋቸውን ቀጠሉ። ጦራቸው ግን እስከ 1815 ድረስ ትግሉን ቀጠለ። 
ይህ የሃይማኖት አብዮት በእስላማዊ ሕግ መሠረት የሀውሳ ግዛቶችን አንድ እያደረገ እና እያቀራረበ ሄደ። ኃላም እ.ኤ.አ. በ 1812  የአሚር አስተዳደሮችን ያቀፈ «ሶኮቶ ካሊፋት» የተባለ መንግሥት እንዲመሠረት አደረገ ። የብዙዎቹም ቤተ መንግሥት በየነበሩበት የሀውሳ ግዛት ነበር የተገነባው። የሶኮቶ ካሊፋት በ 19 ኛው ምዕተ ዓመት በአካባቢው ጠንካራ ኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ስርዓት እንዲዘረጋ እንዲሁም ለሰሜን ናይጄሪያ እስልምና እንዲስፋፋ አስተዋጽኦ አበርክቷል ፡፡ 
በኡስማን ዳን ፎዲዮ የተመሰረተው ካሊፋት ምን ያህል አስፈላጊ ነበር?
የእስልምና ሃይማኖታዊ ግዛታቸው የአሁኑን አብዛኛውን የሰሜን ናይጄሪያ ክፍል እንዲሁም የኒጀር እና ሰሜናዊ ካሜሮን የተወሰኑ ክፍሎችን ያጠቃልላል ፡፡ የቅዱስ ጦርነቱ በዚያን ጊዜ በምዕራብ አፍሪቃ የተለያዩ አካባቢዎች ተመሳሳይ ጦርነቶች እንዲካሄዱ ያነሳሳ ሲሆን በምዕራብ አፍሪቃውያን ዘንድ የእስልምና ሐይማኖት ቀዳሚውን ስፍራ እንዲይዝም አድርጓል። 
እ.ኤ.አ. በ 1837 የሶኮቶ ካሊፋት ምዕራብ አፍሪቃ ውስጥ ከ 20 ሚሊዮን በላይ የሚገመት ህዝብ ያለው እጅግ ግዙፉ ግዛት ነበር።
ሼህ ኡስማን ዳን ፎዲዮ እ.ኤ.አ. ሚያዚያ 20 ቀን 1817 ሶኮቶ ውስጥ አረፉ፡፡

DW African Roots | Sheikh Usman dan Fodio

ኡስማን ዳን ፎዲዮ

ኡስማን ዳን ፎዲዮ

ይህ ዘገባ አፍሪካዊ ሥረ-መሠረት በሚል ከጌርዳ ሔንክል ተቋም ጋር በመተባበር የሚቀርብ ዝግጅት ነው። የዘገባው ሳይንሳዊ ምክር የተገኘው ከፕሮፌሰር ጉዳዬ ኮናቴ፣ ሊሊ ማፌላ Ph.D እና ፕሩፌሰር ክሪስቶፈር ኦግቦግቦ ነው።