1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍሪካውያንን ለዓለም ጤና ድርጅት ጥብቅና ያቆመው የቴድሮስ ጉዳይ

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 3 2012

ከአፍሪካ ኅብረት ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ እስከ ኮሚሽኑ ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪ ማኅማት፤ ከኢትዮጵያዋ ርዕሰ-ብሔር ሣህለ ወርቅ ዘውዴ እስከ የርዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ በሳምንቱ ለዓለም ጤና ድርጅትና ኃላፊው ድጋፋቸውን ገልጸዋል። ኮሮና ዓለምን በሚያምስበት በዚህ ወቅት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ከተቋሙና ኃላፊው የገቡት እሰጥ አገባ መነሾ ነው

https://p.dw.com/p/3amqu
Schweiz WHO Tedros Adhanom Ghebreyesus
ምስል AFP/F. Coffrini

የአፍሪካ መሪዎች ድጋፋቸውን ለድርጅቱ ገልጸዋል

የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር እና ደጋፊዎቹ ለኮሮና ወረርሽኝ የዓለም ጤና ድርጅትን በከፊል ተጠያቂ አድርገዋል። ፕሬዝዳንቱ ድርጅቱ እጅግ ለቻይና ያደላ ነው የሚል ወቀሳ አላቸው። ሪፐብሊካን የአሜሪካ ምክር ቤት አባላት የድርጅቱ ዳይሬክተር ቴድሮስ አድኃኖም ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ እስከ መጠየቅ ደርሰዋል። 

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት አገራቸው ለዓለም ጤና ድርጅት የምትሰጠውን ገንዘብ እስከ መከልከል የደረሰ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጅት ላይ መሆናቸውን ጥቆማ ሰጥተዋል። «በሚቀጥለው ሳምንት ስለ የዓለም የጤና ድርጅት በቅጡ እንነጋገራለን» ያሉት ትራምፕ «ለበርካታ አመታት ከ300 እስከ 500 ሚሊዮን ዶላር አንዳንዴም ከዚያ በላይ ስንከፍላቸው ቆይተናል። ቻይና ባለፉት አመታት ስትከፍላቸው የቆየችው ከ40 ሚሊዮን ዶላር በታች ነው። እኛ የምንከፍለው ከቻይና አስር እጥፍ የሚበልጥ ቢሆንም ከዚህ ቀደም እንደምለው እጅግ ለቻይና ያደሉ ናቸው። ይኸን አልወደውም። ለአሜሪካውያን ፍትኃዊ ነው ብዬ አላስብም። ይኸን ለፕሬዝዳንት ዢ እና ለዶክተር ቴድሮስ ነግሪያቸዋለሁ» ብለዋል።

USA Präsident Donald Trump Coronavirus Pressekonferenz
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕምስል Reuters/J. Roberts

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከዓለም ጤና ድርጅት እሰጥ አገባ ከገጠሙ ሶስት ሳምንታት ገደማ አለፋቸው። በኮሮና ጉዳይ ከአገራቸው ባለሥልጣናት ጋር ሆነው በሰጧቸው ተደጋጋሚ መግለጫዎች ድርጅቱን ሲኮንኑ ተደምጠዋል። በትራምፕ እምነት የዓለም የጤና ድርጅት የኮሮናን አስከፊነት በቅጡ መረዳት ሳይችል ቀርቷል። የትራምፕ ወቀሳ እና ክስ ድርጅቱን በሚመሩት ዶክተር ቴድሮስ አድኃኖም ዘንድ ተቀባይነት የለውም። ዶክተር ቴድሮስ ባለፈው ሳምንት እንደ ወትሮው ከሚያተኩሩበት የኮሮና ወረርሽኝ ኹኔታ ባሻገር ጠንከር ያለ አስተያየት ተሰጥተዋል።

«በአገር ደረጃ ከፖለቲካ፣ ሐይማኖት፣ ርዕዮተ ዓለም እና ሌሎች ልዩነቶቻችን  ተሻግረን መስራት መቻል አለብን። በአገር ደረጃ በፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሐይማኖቶች ወይም ሌሎች ቡድኖች መካከል ተሕዋሲው አንድ ስንጥቅ ሲያገኝ በዚያ ገብቶ ሊያሸንፈን ይችላል። ስለዚህ ቀዳሚው ነገር አገራዊ አንድነት ነው-የፓርቲ ልዩነት ተሻግሮ መስራት» ያሉት ዶክተር ቴድሮስ ጉዳዩ በጥንቃቄ እንዲያዝ መክረዋል።

ዶክተር ቴድሮስ «እኔም ፖለቲከኛ ነበርኩ። ይኸ እንዴት ፈታኝ ሊሆን እንደሚችል አውቀዋለሁ። አስቸጋሪ ነገር ቢሆንም እንኳ ሊደረግ የሚገባው ነው። የሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ዋንኛ ትኩረት ዜጎቻቸውን ማዳን መሆን አለበት። እባካችሁ ይኸን ተሕዋሲ ፖለቲካዊ ጉዳይ አታደርጉት» ሲሉ ተማፅነዋል።

ከጥቂት ቀናት በኋላ ደግሞ «ፖለቲካዊ ጉዳይ አታድርጉት ሲሉ ራሳቸው ፖለቲካ እያደረጉት ነው። ከቻይና ጋር ያላቸውን ግንኙነት ተመልከቱ» ሲሉ ትራምፕ መልስ ሰጡ።

ይኸ እሰጥ አገባ የአፍሪካ ኅብረትን ጨምሮ የአኅጉሪቱ ተቋማት እና መሪዎች እጃቸውን አጣጥፈው የሚመለከቱት አልሆነም። ከኢትዮጵያ ርዕሰ ብሔር ሣህለ ወርቅ ዘውዴ እስከ ናሚቢያው ፕሬዝዳንት ሐጌ ጌይንጎብ፤ ከአፍሪካ ኅብረት ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ እስከ ኅብረቱ ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማኅማት ለዓለም ጤና ድርጅት እና ኃላፊው ድጋፋቸውን እንዲገልጹ አድርጓቸዋል።

ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ «ውጤታማ አመራር አሳይተዋል» ያሏቸው የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር አንገብጋቢ በሆነው በዚህ ወቅት የተጣለባቸውን ኃላፊነት ተወጥተዋል የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል። የአሜሪካ መንግሥት በዓለም ጤና ድርጅት አመራር ላይ ጀምሮታል ያሉትን የውግዘት ዘመቻ የነቀፉት የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪ ማኅማት ናቸው።  ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪ ማኅማት በተጨማሪ የናሚቢያው ፕሬዝዳንት ሐጌ ጋይንጎብ ለዶክተር ቴድሮስ ድጋፋቸውን ገልጸዋል። ፕሬዝዳንቱ “የዓለም የጤና ድርጅት በዶክተር ቴድሮስ አመራር ትብብር በሚያስፈልግበት በዚህ ወቅት ትክክለኛ ዓለም አቀፍ ተቋምነቱን አሳይቷል” ብለዋል። የርዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ በበኩላቸው «ዶክተር ቴድሮስ አድኃኖም በዓለም ጤና ድርጅት መሪነታቸው አፍሪካ ትተማመንባቸዋለች፤ ትደግፋቸውማለች» የሚል መልዕክት በትዊተር አስተላልፈዋል።

የአፍሪካ ኅብረትን የሚመሩት የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት  ሲሪል ራማፎሳ በበኩላቸው ዶክተር ቴድሮስ በዓለም ጤና ድርጅት ወደር የሌለው አመራር አሳይተዋል ሲሉ አሞካሽተዋቸዋል።

የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (Africa CDC) ዳይሬክተር ዶክተር ጆን ንኬንጋሶንግ በበኩላቸው "ይኸ ዓለም አቀፍ ውጊያ ይመስለኛል። ዓለም አቀፍ ትብብር ዝግጅት ይፈልጋል። ማግለል እና መድሎ አያስፈልግም። ተላላፊ በሽታዎች በበረቱባቸው ታሪኮች አንድ ጊዜ መድሎ ከተጀመረ ተሕዋሲውን ለማሸነፍ የሚደረገውን ፍልሚያ አስቸጋሪ እናደርገዋለን። ጠላታችን ተሕዋሲው እንጂ ቻይና አይደለችም» ብለው ነበር።

ማርኮ ሩቢዮ የተባሉ የአሜሪካ ምክር ቤት አባልን ጨምሮ ቀኝ ዘመም የአገሪቱ ፖለቲከኞች እና ጋዜጠኞች የዓለም ጤና ድርጅት እና ኃላፊው ዶክተር ቴድሮስ አድኃኖም “ለቻይና ያደላሉ” የሚል ወቀሳ ሲያቀርቡ ሰንብተዋል። ባለፉት ሳምንታት ከአሜሪካ በኩል በዓለም የጤና ድርጅት ላይ የበረታው ወቀሳ በዶክተር ቴድሮስ አድኃኖም ጉዳይ ብቻ የተገደበ አይመስልም። ከዚህ ቀደም የንግድ ጦርነት ውስጥ ገብተው በነበሩት አሜሪካ እና በቻይና መካከል የሚቀሰቀሰዝ ዘርፈ ብዙ እሰጥ አገባ አንድ አካል እንጂ

የዓለም ጤና ድርጅት እና ቴድሮስ በምዕራባውያኑ በወረርሽኝ ሳቢያ ሲወቀሱ ይኸ የመጀመሪያቸው አይደለም። ከሁለት አመት ገደማ በፊት በሱዳን የተከሰተን ወረርሽኝ ደብቀዋል ተብለው በአምስት የአሜሪካ የሕክምና ዶክተሮች ተወንጅለዋል።

እሸቴ በቀለ