1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍሪቃውያን ከባይደን መመረጥ ምን ይጠብቃሉ?

ቅዳሜ፣ ጥር 15 2013

ጆ ባይደን ቃለ-መሐላ ከፈፀሙ በኋላ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቁልፍ ፖሊሲዎችን ለመከለስ ጀምረዋል።ከነዚህም ውስጥ የአየር ጠባይ ለውጥ፣የፍልሰት፣እንዲሁም በአንዳንድ የሙስሊም ሀገራት ላይ በትራምፕ አስተዳደር ተጥሎ የነበረውን እገዳ እንዲነሳም ወስነዋል።ይህንን የተመለከቱ አፍሪቃውያን በባይደን አስተዳደር ተስፋ ሰንቀዋል።

https://p.dw.com/p/3oKoc
USA Washington | Pressekonferenz Joe Biden zum Coronavirus
ምስል Jonathan Ernst/REUTERS

ትኩረት በአፍሪካ

«ዋና ዳኛ ሮበርትስ፣ምክትል ፕሬዚዳንት ሃሪስ፣አፈ ጉባኤ ፔሎሲ፣ከፍተኛ አመራር ሹመር፣ ከፍተኛ አመራር ማክኔል፣ምክትል ፕሬዚዳንት ፔንስ፣የተከበራችሁ እንግዶች ወገኖቼ አሜሪካውያን ይህ የአሜሪካ ቀን ነው።ይህ የዲሞክራሲ ቀን ነው።የታሪክና የተስፋ ቀን ነው።»
አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆባይደን ያለፈው ረቡዕ መንበረ ስልጣኑን ሲረከቡ ካደረጉት ንግግር የተቀነጨበ ነበር።የረጅም ጊዜ የሴኔት አባል በመሆንና በምክትል ፕሬዚዳንት ያገለገሉት የ78 ዓመቱ አንጋፋ ፖለቲከኛ ጆባይደን የቀድሞውን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን ተክተው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በመሆን በሳምንቱ አጋማሽ ቃለ መሀላ ፈፅመዋል።46ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ቃለ-መሐላ ከፈፀሙ በኋላ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቁልፍ ፖሊሲዎችን ለመከለስ ጀምረዋል ።ከነዚህም ውስጥ የአየር ጠባይ ለውጥ፣የፍልሰት፣ለኮሮና ወረርሽኝ በተሰጠው ምላሽና  እንዲሁም  በአንዳንድ የሙስሊም ሀገራት ላይ በትራምፕ አስተዳደር ተጥሎ የነበረውን እገዳ እንዲነሳም ወስነዋል።ይህንን የተመለከቱ አፍሪቃውያን ታዲያ በባይደን አስተዳደር ተስፋ ሰንቀዋል።
በዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በ2017 ተጥሎ የበነበረው ይህ ህግ፤  በ13 ሀገሮች ላይ የቪዛና የጉዞ እገዳ የሚጥል ሲሆን፤ ከአፍሪቃ ናይጄሪያ፣ሱዳንን፣ኤርትራ፣ ግብፅ፣ ሊቢያና ታንዛኒያ ይገኙበታል።
በመሆኑም ፤ጆባይደን በመጀመሪያ ቀን ስልጣናቸው እንዲነሳ ያደረጉት ይህ ህግ በርካቶችን አስደስቷል።ዶቼ ቬለ ያነጋገራት ሱዳናዊት  ወጣትም ርምጃው  ተስፋ ሰጪ ነው ትላለች።
«እንደማስበው በጣም ተስፋ ሰጪ ነው።በጣም አወንታዊ ነገር ነው። በማንኛውም መልኩ በሱዳን ላይ የተጣለን እገዳና ማዕቀብ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሲያነሳ ይህ የመጀመሪያ ነው።»
በኬንያ  የስደተኛ ካምፕ ውስጥ ለሚገኙ አንዲት ሶማሊያዊት ወይዘሮ ደግሞ የጆባይደን መመረጥ የተለዬ ትርጉም አለው።
«እኛ በኬንያ በስደተኝነት የምንገኝ ሶማሊያውያን ነን።ጆባይደን ፕሬዚዳንት እንዲሆን እንፈልጋለን።ምክንያቱም ያንን ሰው ስትመለከቱ የእኩልነት ሰው ነው።የሁሉንም መብት ያከብራል።ትራምፕ ያጣለውን  የሙስሊሞች እገዳ ለማንሳት ቃል ገብቷል።ይህ ጥሩ ዜና ነው።ወደ አሜሪካ ለመሄድ ለምንጠባበቅ ከሶማሊያ ለመጣን ሶማሊያውያንና ለኬንያ ሶማሊያውያን።»
ባይደን ብዙዎች ዘንድ ዲሞክራሲ ተምሳሌት ተደርገው እየታዩ ሲሆን፤ በአንፃሩ ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሽንፈታቸውን አለመቀበላቸውና  በተመራጩ ፕሬዚዳንት ጆባይደን በዓለ ሲመት ላይ አለመገኘት ለአምባገነኖች በተለይም  በምርጫ መሪን መቀየር  ፈተና ለሆነባት የአፍሪቃ አህጉር መሪዎች የልብልብ የሚሰጥና የተሳሳተ መልዕክት የሚያስተላልፍ ነው ይላሉ።የዚምባብዌው  ደራሲ ችንገታይ ጉታ።
«የጆባይደን መመረጥና የዶናልድ ትራምፕ መሸነፍ እውነተኛ የዶሞክራሲ ፈተና ማሳያ ነው። እንዲሁም በአሜሪካ ተቋማት ምን ያህል ሀይል እንዳላቸው የሚያሳይ ነው።ነገር ግን በሚያሳዝን ሁኔታው  ነገር  ሁኔታ በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ አፋኝ አምባገነኖች እንደ ሰበብ  ሊያገለግል  እንደሚችል ተገንዝቢያለሁ።»
ባይደን በተጨማሪም ዓለም አቀፍ የ«ጋግ» ሕግ በመባል የሚታወቀውን  የመንግስት ፖሊሲ ለመሰረዝ ቃል ገብተዋል። ይህ ህግ በፅንስ ማስወረድ ላይ መረጃን ለሚሰጡ የውጭ ዕርዳታ ድርጅቶች ወይም ከዚህ ጉዳይ ጋር የተያያዙ ህጎች እንዲለወጡ ለሚጠይቁ ድርጅቶች አሜሪካ ድጋፍ እንዳትሰጥ የሚከለክል ነው።ፖሊሲው በአፍሪካ ውስጥ በተለያዩ የሴቶች ጤና አገልግሎቶች ላይ የሚሰሩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ሲያደናቅፍ የቆየ መሆኑ ይነገራል። 
በደቡብ አፍሪካ የፕሪቶሪያ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር የሆኑት ሲቴምቢል ሜቢቴ በበኩላቸው «እነዚህ ፈጣን ለውጦች በአሜሪካ እና በአፍሪካ መካከል ያለውን  ገጽታ እና ግንኙነት ይለውጣሉ»የሚል ተስፋ አላቸው። 
ሚቤቴ አያይዘውም፤ አሜሪካ በትራምፕ አስተዳደር በአፍሪካ ያላትን ወሳኝ ቦታ ያጣችበት በመሆኑ  እንደ ቻይና ፣ ሩሲያና  ህንድ  የመሳሰሉ ሀገራት  ለአፍሪካ ሰፊ  የአጋርነት ቦታ መያዝ ችለዋል።በመሆኑም አፍሪቃ ወጣት የሰው ሀይልና በማደግ ላይ ያለ ገበያ ያላት አህጉር በመሆኗ፤ የባይደን አስተዳደር በአፍሪካ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
በናይጄሪያ አቡጃ የማኅበራዊ ጉዳዮች ተንታኝ የሆኑት አብድራህማን አቡ ሀሚሱ ግን፤  ከአዲሱ ተመራጭ ፕሬዚዳንት ጆባይደን የሚጠብቅትንና የቀድሞውን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን  የሚያዩበት መንገድ የተለዬ ነው።ሀሚሱ ትራምፕ እጃቸውን ከአፍሪቃ ላይ አንስተው መቆየታቸውን በበጎ  ያዩታል።
« እንደ አፍሪቃዊ በፕሬዚዳንት ትራምፕ ላይ  አስተያየት መስጠት እፈልጋለሁ።በእውነቱ  ትራምፕ ፤ወንድማችን ኦባማ እንዳደረገው በአፍሪካ የአገዛዝ መውደቅ ሊያስከትል የሚችል ጦርነት እንዲባባስ አላደረጉም፡፡እሳቸው የተኩት ፕሬዚዳንት በሊቢያ ጋዳፊ እንዲወድቅ አደርጓል።ያ ደግሞ በናይጄሪያ የፀጥታ ሁኔታ ላይ በእጅጉ ተፅዕኖ አሳድሯል።እኛ ተስፋ የምናደርገው ባይደን በዚህ መንገድ እንዲቀጥል ነው።ምክንያቱም ባይደን ፍትህን የሚደግፍ ሰው ስለሆነ በመላው ዓለም ፍትህና ሰላም እንዲሰፍን፤ እንዲሁም በዓለም ዙሪያ  የሰዎች መብት እንዲከበር መደገፉን ይቀጥላል።ያ ደግሞ ሰላምን እንጅ ጦርነትን አያባብስም።»
በአፍሪቃ በህዝብ ብዛቷ የምትታወቀው ናይጄሪያ በትራምፕ አስተዳደር እገዳ ከተጣለባቸው ሀገሮች አንዷ ነች።ለትምህርት ለንግድ ለህክምናናና ለተለያዩ ጉዳዮች ወደ አሜሪካ ያመሩ የነበሩ ግን የተከለከሉ ናይጄሪያውያን ታዲያ  በባይደን አስተዳደር ተስፋ ሰነቀዋል።
 ከናይጄሪያ አቡጃ የፖለቲካ ተንታኙ ፕሮፌሰር ኦስማን ሙሃ ግን የአፍሪቃዉያንና የአፍሪቃ መሪዎች ፕሬዚዳንት ጆባይደንን ተስፋ ከማድረግ ይልቅ መሪዎች በሀገራቸው መልካም አስተዳደርና ዲሞክራሲ ቢያሰፍኑ ለህዝባቸው የበለጠ ተስፋ ይሰጣል ባይ ናቸው።
 ኦስማን እንደሚሉት ባይደን የኦባማ ምክትል ፕሬዚዳንት በነበሩበት ወቅት ለአፍሪቃ ትኩረትና ብዙ እርዳታ ይሰጡ እንደነበር ገልፀው፤በአሁኑ ወቅት ግን አሜሪካ ብዙ ችግር ያለባትና በኢኮኖሚዋም ደካማ በመሆኗ የተለዬ ነገር አይጠበቅም ። ሆኖም ግን ይላሉ የፖለቲካ ተንታኙ በተወሰኑ መስኮች ሀገሪቱ ከአፍሪቃ ጋር በትብብር መስራቷ አይቀርም።
 «ሌሎች የተወሰኑ  ስትራቴጅካዊ የትብብር  ሁኔታዎች ሊኖሩ ይችላሉ።ለምሳሌ  ኤች አይቬ ኤድስን የተመለከተ  እርዳታ እንዲሁም ቻይናና ሩሲያ በአፍሪቃ ያላቸውን ቦታ የሚተካ  የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት።ሀገራቱ በቀላሉ አፍሪቃን የሚለቁ ባለመሆናቸውም ዘዴኛ መሆን አለባቸው። በተረፈ  ይህ የተከበረ ሰው ጆ ባይደን ችግራችንን እንዲፈታ መጠበቅ የለብንም።የአፍሪቃ መሪዎች መተባበር አለባቸው።ህዝብን ያማከለና ተስፋ ሰጪ  ስራም መስራት አለባቸው።ለምሳሌ መሰረተ ልማት፣በተጨማሪ ተቀባይነት ያለው ለህዝቡ ግልፅና ተጠያቂነት ያለው ዲሞክራሲያዊ የአስተዳደር ዘይቬችን መከተል አለባቸው።»  
በፊላደልፊያ የሊንከን ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ጋንካ ላጎኬ በበኩላቸው በጆባይደን አስተዳደር አሜሪካ በልማት፣በዕርዳታ፣በዲፕሎማሲ እና በውጭ ፖሊሲዎች በአፍሪቃ የበለጠ  መስተጋብር ይኖራታል ብለው ይገምታሉ። ያም ሆኖ አሜሪካ በአፍሪቃ የምታደርገውን ተሳትፎ በጥርጣሬ ያዩታል። እሳቸው እንደሚሉት በአፍሪካ  የአሜሪካ ተሳትፎ  ጥሩ ቢሆንም፤በ2011 በሊቢያ እንደነበረው ፍላጎትን ለማስፈፀም ወታደራዊ ጣልቃ ገብነትና ጦርነት ወደ አካሄደችው  ኢምፔሪያሊስት አሜሪካ የመመለስ አደጋ መኖሩንም ጠቁመዋል።
እንደ ፕሮፌሰሯ ገለፃ የሀያላን ሀገሮች ውድድር  በአፍሪካ ሀብቶች ላይ  ነው። እናም ጆባይደን የአሜሪካን ኩባንያዎችን መደገፍ አሜሪካ በቻይና ፣ በፈረንሣይ ወይም በጀርመን ላይ ተወዳዳሪ እንድትሆን ያደርጋት እንደሁ  እንጅ አፍሪቃን ይጠቅማል ብለው አያስቡም።
ፀሀይ ጫኔ
ሽዋዬ ለገሠ