1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍሪቃዉያን የዘንድሮው የሐጅ ጉዞ፤ መጭዉ የታንዛኒያ ምርጫ

ሰኞ፣ ሐምሌ 27 2012

በእስልምና ሀይማኖት ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የሐጅ ጉዞ ዘንድሮ  በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ እክል ገጥሞታል።የሀጅ ጎዞ  የእስልምና ሀይማኖት ተከታዮች  በህይወት ዘመናቸው አንዴ ሊያደርጉት የሚገባ የተቀደሰ ተግባር  ሲሆን ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከ ሁለት እስከ ሁለት ነጥብ አምስት  ሚሊዮን  የእምነቱ ተከታዮች ወደዚያ ያመሩ ነበር።

https://p.dw.com/p/3gMS5
Afrika Tansania Präsidentschaftswahlen 2020
ምስል DW/S. Khamis

ትኩረት በአፍሪካ ሐምሌ 25/2012 ዓ/ም

አፍሪቃዉያን የዘንድሮው የሐጅ ጉዞ፤ መጭዉ የታንዛኒያ ምርጫ

 በእስልምና ሀይማኖት ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የሐጅ ጉዞ ዘንድሮ  በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ እክል ገጥሞታል።የሀጅ ጎዞ  የእስልምና ሀይማኖት ተከታዮች  በህይወት ዘመናቸው አንዴ ሊያደርጉት የሚገባ የተቀደሰ ተግባር  ሲሆን፤በዚህ ሀይማኖታዊ ጉዞ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከ ሁለት እስከ ሁለት ነጥብ አምስት  ሚሊዮን  የእምነቱ ተከታዮች ወደዚያ ያመሩ ነበር።

በዚህ ዓመት ግን የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመቆጣጠር ከዓለም ዙሪያ ለሀይማኖታዊ ጉዞው ወደ መካ የሚገቡ ሰዎች ተከልክለዋል። ሳዑዲ ዓረቢያ በዘንድሮው የሀጅ ጉዞ  ከ 10 ,000  የማይበልጡ የሳውዲ ዜጎችና በሳውዲ ለሚኖሩ የሌላ ሀገር ዜጎች እንዲታደሙ ፈቅዳለች።

በሳውዲ  የሚኖሩት ናይጄሪያዊው ናስር የኑስ ሶልባራሞ የዘንድሮዉን የሀጅ ጎዞ ለማድረግ ዕድል ካገኙ ጥቂት  ሰዎች መካከል አንዱ ናቸው፡፡ ሶልባርሞ ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል እንደገለፁት  ከሀይማኖታዊ ተጓዦቹ መካከል አንዱ ለመሆን መታደላቸውን «ወርቃማ ዕድል» ሲሉ ነበር የገለፁት።አያይዘውም ለሀጅ ጎዞ ዕድል ማግኘት በህይወቴ ከተሰጠኝ እጅግ ውድ ነገር ሲሆን፤ የረጅም ጊዜ ምኞቴም ነበር ብለዋል።

ሴኔጋል በሚገኘው የቲምቡክቱ የጥናት ተቋም ዋና ስራ አስፈፃሚ  በክሪ ሳምቤም የመካ ጉዞ የህይወት ዘመን ጉዞ ነው ይላሉ።

Saudi-Arabien Mekka | Corona & Hadsch | Pilgerfahrt
ምስል Reuters/Saudi Press Agency

«እንደማስበው የአፍሪካ ሙስሊሞች በአሁኑ ጊዜ መንፈሳዊ ሥነ-ስርዓቱን የመናፈቅ ስሜት አላቸው። ለብዙ የአፍሪካ ሙስሊሞች ሐጅ የሕይወት ዘመን ጉዞ ነበር ። በእውነቱ ወደ መካ መጓዝ ተምሳሌታዊ የህይወት ዘመን ጉዞ ነበር ፡፡»

በሀይማኖታዊ ጉዞው ከሚሳተፉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ  ተጓዦች መካከል ወደ አስር በመቶ የሚሆኑት ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት የሚመጡ አፍሪቃውያን ሙስሊሞች ናቸው።በክሪ እንደሚሉት የሀጅ ጉዞ መሰረዝ በተለዬ ምክንያት መሆኑን ቢገነዘቡም ለብዙዎች አፍሪቃውያን  አሳዛኝ ነው።

«አንድ አፍሪካዊ ሙስሊም ህይወቱን ሙሉ የሚሰጥበት ብቸኛው ጉዞ የመካ ጉዞ ነው። እናም መገመት ትችላለህ ሰዎች በዚህ አመት ወደ መካ መሄድ ባለመቻላቸው ይፀፀታሉ።በእድሜ የገፉ ከሆነ ደግሞ ምናልባት ወደፊት በጭራሽ ላይሄዱ ይችላሉ፡፡»

ጀርመን የሚገኘው የዕስልምና ጥናት ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪ  አብዱላይ ሶናዬ እንደሚሉት የምዕራብ አፍሪቃውያን የሐጅ  ጉዞ ዋጋ ከ 3,600 እስከ 5,400 የአሜሪካን ዶላር (ከ 3,000 እስከ 4 500 ዩሮ) ነው። ትልቁ አማካኝ የደመወዝ  መጠን 1,580 ዶላር ለሆነበት  ቀጠና ይህ ዋጋ ከፍተኛ ነው ፡፡«ለሀጅ ጎዞ ርካሽ የሚባል ዋጋ አይታሰብም»የሚሉት ሶናዬ ።ያ በመሆኑ፤ወደ መካ የሚደረገውን የሐጅ ጉዞ ለመታደም የሚያወጡትን ገንዘብ አንዳንድ አፍሪቃውያን ሙስሊሞች ምናልባትም ዕድሜ ልካቸውን ቆጥበው  ያጠራቀሙት ሊሆን ይችላል ይላሉ።ጉዞው ከመሰረዙ ጋር ተያይዞም የጉዞ ትኬት ቆርጠው ይጠባበቁ የነበሩ ሙስሊም አፍሪቃዉያን ገንዘቡን ለማስመለስ በመጣር ላይ ይገኛሉ።ሶናዬ ግን ስጋት አላቸው።

«በብዙ አገሮች ውስጥ የሀይማኖታዊ ተጓዦዎችን ከጉዞ ወኪሎች ጋር የሚያገናኙ እና ጉዳያቸውን የሚከታተሉ ሠራተኞች አሉ። የእኔ የሚያሳስበኝ እነዚያ አገናኞች  የተጓዦቹን ገንዘብ ተመላሽ ለማድረግ ምንያህል የገንዘብ ፍሰትና ዝግጁነት አላቸው የሚለው ነው። »

ሳዑዲ አረቢያ በየአመቱ ወደ መካ የሚሄዱ የሙስሊም ተጓዦችን ቁጥር ለመመጠን  ለእያንዳንዱ ሀገር ጥብቅ የሃጅ ኮታ ስርዓት አላት ፡፡ ከሰሃራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት ናይጄሪያ በመደበኛነት እጅግ በጣም ትልቁን ቁጥር በመያዝ የ 95,000 ፣ ሱዳን  35,000 ፣ ኒጀር ደግሞ 13,000 ኮታ አላቸው ፡፡ በዚህ ኮታ መሰረት ባለፈው ዓመት ብቻ 187,814 አፍሪቃዊውያን ሙስሊሞች ሐጅ አድርገዋል፡፡ በ COVID-19 ወረርሽኝ ምክንያት ቁጥሩ ባይቀነስ ኖሮ በዚህ ዓመትም ተመሳሳይ ቁጥር ይጠበቅ ነበር።

BdTD Saudi Arabien | Hadsch-Pilgerfahrt inmitten der COVID-19-Pandemie
ምስል Reuters/Saudi Ministry of Media

የሀጅ ጎዞ በጎርጎሪያኑ  2012 እና 2013 ዓ/ም ሳውዲ አረቢያ የመካከለኛው ምስራቅ የመተንፈሻ አካላት ህመም ስጋት ባለባቸው አዛውንቶች እና አቅመ ደካሞች የሃጅ ጉዞ እንዳያደርጉ ማስጠንቀቂያ አውጥታ የነበረ ሲሆን፤በ 2014 ዓመተ ምህረትም በኢቦላ በሽታ ስጋት  ለጊኒ ፣ ሊቤሪያ እና ሴራሊዮን  ዜጎች ቪዛ መስጠቷን  ለጊዜው አቁማ ነበር። በ 2019 ዓመተ ምህረት ደግሞ ከኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ  የሀጅ ተጓዦች እንዳይመጡ ከልክላ ነበር ፡፡

በሳውዲ ያለፈው ረቡዕ በጎሮጎሮያኑ ሀምሌ 28 ቀን የተጀመረውና እስከ ነሀሴ 2 ቀን የሚዘልቀው የዘንድሮው የሀጅ ሀይማኖታዊ ስነ-ስርዓት ቀደም ብለው የተመረጡና ከሳምንት በፊት የኮሮና ምርመራ ያደረጉ ሰዎች ብቻ የታደሙበት ሲሆን፤አካላዊ ርቀትን መጠበቅም ግድ ነበር።

በሳዉዲ አረቢያ እስከትናንት ዕኩለ ቀን ድረስ በኮሮና ተዋህሲ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 274,219 /ሁለት መቶ ሰባ አራት ሺህ ሁለት መቶ አስራ ዘጠኝ/ ሲሆን  የሟቾች ቁጥር ደግሞ 2,842/ ሁለት ሺህ ስምንት መቶ አርባ ሁለት/ ደርሷል።

Saudi-Arabien Mekka | Corona & Hadsch | Pilgerfahrt
ምስል Reuters/Saudi Ministry of Media

ለውጥ የማይጠበቅበት የታንዛኒያ ምርጫ

በ1961 ከብሪታንያ ነጻነቷን ያገነችው ምስራቅ አፍሪቃዊቷ ሀገር ታንዛኒያ በመጭው ታህሳስ ፕሬዝዳንታዊ  ምርጫ ታካሂዳለች።ሀገሪቱ ከነፃነቷን ካገኘች በኋላ  አምስት ምርጫዎችን ያካሄደች ሲሆን፤ በስልጣን ላይ የሚገኙትን ዶክተር ጆን ማጌፉሌይ ጨምሮ  አምስቱም ፕሬዚዳንቶች የወጡት የአብዮቱ ፓርቲ  ወይም «ቻማ ቻ ማፒንዱዚ » ተብሎ ከሚጠራው ገዥ ፓርቲ ነው።በዚህ የተነሳ በ2015  መንበረ ስልጣኑን በምርጫ የተረከቡት የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ከሶስት ወራት በኋላ በሚደረገው ምርጫም በድጋሚ ለመመረጥ ይችላሉ የሚል ግምት አሳድሯል።በቅርቡ አንድ ታዋቂ ፖለቲከኛ  ወደ ሀገራቸው ታንዛኒያ ከተመለሱ ወዲህ ግን የፖለቲካው ገጽታ የተለወጠ ይመስላል።እኝህ ሰው ቱንዱ ሊሱ ይባላሉ።

ታዋቂው የፖለቲካ ሰው ያለፈው ሳምንት ዳሬሰላም አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ  የነጭና የቀይ አበባ ጉንጉን አንገታቸው ላይ አድርገውና በክፍት መኪና ሆነው ቀኝ እጃቸውን ወደ ህዝቡ ሲያውለበልቡ ለተመለከታቸው፤ አንድ የስፖርት ቡድን ወሳኝ ውድድር አሸንፎ ሲገባ የሚደረግለት አቀባበል ይመስል ነበር።«ወደ ሀገሬ ተመለስኩ» አሉ ሊሱ ። እሳቸውን ለመቀበል  ወደ ተሰበሰበው ህዝብ  ዞረው።ቀጥለውም።  

Afrika Tansania Präsidentschaftswahlen 2020
ምስል DW/S. Khamis

« ወደ ሀገሬ ተመልሻለሁ ፡፡ሀገሬን እንዴት ለቅቄ እንደወጣሁ እንኳ ከማላስታውስበት ቀን ጀምሮ ሶስት አመት ሊሆነው ነው።ሶስቱ አመታት በጣም አስቸጋሪ አመታት ነበሩ።ዛሬ ግን ቢያንስ መራመድና መደነስ እችላለሁ።ነገር ግን  ራሴን ችዬ መራመድ አይደለም በህይወት እንዳልኖር ነበር የተደረገው።»

ሊሱ ፤ቻዴማ የተባለው ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ሲሆኑ  በፕሬዚዳንቱ ላይ የሰላ ትችት በመሰንዘር ይታወቃሉ።የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ሊሱ፤ ከሶስት ዓመት በፊት በ2017 ዓ/ም ከሀገሪቱ ፓርላማ ፊትለፊት በጥይት ተመተው ክፉኛ በመቁሰላቸው ወደ ቤልጀም ሄደው ሲታከሙ ከቆዩ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሀገራቸው መመለሳቸው ነበር።

ሊሱ፤ ለደህንነታቸው ሲባል  በመጀመሪያ ኬንያ ውስጥ ሲታከሙ ቆይተው ወደ ኋላ ላይ ግን ለተሻለ ህክምና ወደ ቤልጀም እንዲሄዱ ተደርጓል።ተኩሶ ጥቃት ያደረሰባቸው አካል እስካሁን ያልታወቀ ሲሆን በቤልጄም 19 ጊዜ የቀዶ ጥገና አድርገዋል። በመጭው ታህሳስ በሚደረገው ምርጫ የፕሬዝዳንቱ ዋነኛ ተቀናቃኝ ለመሆን ይፈልጋሉ።የሊሱ ወደ ታንዛኒያ መመለስ አዲስ የፖለቲካ ገጽታ ይፈጥራል ይላል ታንዛኒያዊው ጋዜጠኛ ጀነራሊ ኡሊምቬንጉ።

«አሁን አንዳንዶች አዲስ የለውጥ ተስፋ አላቸው።ብዙዎች ፖለቲከኛው ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ  ከሶስት አመት በፊት እንደሆነው እንደገና ሊያጠቋቸው ይችላሉ። ወይም ፖሊሶች የሰውን መሰባሰብ ሊያስተጓጉሉ ይችላሉ። የሚል ፍርሀት ነበራቸው።ግን ያ አልተከሰተም።»

ታንዛኒያ ከሳምንት በፊት በጎርጎሪያኑ ከ1985 እስከ2005 የመሯትን የቀድሞ ፕሬዝዳንቷን ቤንጃሚን ማካፓን በሞት አጥታለች።በዚህ የተነሳ የተቃዋሚው ቻዴማ ፓርቲ ዕጩ ተወዳዳሪዎች ምርጫ ስብሰባውን ለአንድ ሳምንት አራዝሟል።ከዚያም ቱንዱ ሊሱ በይፋ ዕጩ ተወዳዳሪ ሆነው መመረጥ ይፈልጋሉ።በዳሬሰላም የኮንራድ አደንአወር ፋውንዴሽን ስራአስኪያጅ የሆኑት   ዳንኤል ኤል ኖሽካቲ ግን በመጭው ምርጫ የስልጣን ለውጥ ይመጣል ብለው አይጠብቁም ።

« ፕሬዚዳንታዊ ምርጫውን ያሸንፋል ወይ ብትሉኝ መልሴ አይሆንም ነው።እኔ እንደምገምተው ፕሬዚዳንቱ በአብላጫ ድምፅ በድጋሜ ይመረጣሉ።እንደተናገርኩት ያንን ነው የሚፈልጉት።ሊሱ ያለው ዕድል አሁንም ድረስ ተቃዋሚ መኖሩን ማረጋገጥ ነው።»

ሊሱ፤ ተስፋ ሰጪ ተፎካካሪ እንዲሆኑ የምርጫ ቅስቀሳው ከወዲሁ መጀመር አለበት ይላሉ።  ፕሬዝዳንት ማጌፉሌ በበኩላቸው ባልተመደ ሁኔታ «ሁሉም ፓርቲዎች እኩል ናቸው« ሲሉ ተደምጠዋል። 

«ትንሽ የሚባል ፓርቲ የለም።ሁላችንም እኩል ነን።እናም ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የሰለጠነ የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ እንችላለን ብዬ አምናለሁ።ለመንግስት ባለስልጣናትም አስፈላጊ ያልሆነ ሀይል እንዳይጠቀሙ ጥሪ አቀርባለሁ።»

ያም ሆኖ ተችዎች ለተቃዋሚዎችና ለሲቪሉ ማህበረሰብ የፖለቲካ ምህዳሩን  አጥብበዋል በሚል ፕሬዚዳንት ማጌፉሊን ይወቅሳሉ።በሌላ በኩል የመንግስት የመገናኛ ብዙሃን  ቁጥጥር  እንዲሁም በጋዜጠኞችና በተቃዋሚ ሀይሎች ላይ የሚደረግ ጥቃት እየጨመረ መሆኑም ይነገራል።በቅርቡም ስምንት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች የመሰብሰብ ዕገዳን ጥሰዋል በሚል በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ዘገባዎች ያሳያሉ።

Tansania Sansibar| Hussein Ali Mwinyi
ምስል DW/Said Khamis

ጋዜጠኛና ተንታኙ ኦሊምቬንጉ ግን ፤መራጮች  ጠንካራ ተፎካካሪ በምርጫዉ ይሻሉና በዚህ አስቸጋሪና የተገደበ ሁኔታም ቢሆን ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚቻላቸውን ሁሉ ማድረግ አለባቸው በማለት ያጠቃልላል።

ታንዛኒያ ከ1992 ዓ/ም ጀምሮ የመድበለ ፓርቲ የፖለቲካ ስርዓት የምታራምድ ሀገር ቢሆንም የአብዮቱ ፓርቲ  ወይም «ቻማ ቻ ማፒንዱዚ » ተብሎ የሚጠራው ገዥ ፓርቲ ትልቁ ፓርቲ ነው።ይህ ፓርቲ በ1977 የተመሰረተ ሲሆን ከደቡብ አፍሪቃ ብሄራዊ ፓርቲ ቀጥሎ በአፍሪቃ ሁለተኛው ረጅም ዕድሜ ያስቆጠረ  ፓርቲ ነው።እስካሁን አሸንፈው ታንዛኒያን  የመሯት አምስት ፕሬዚዳንቶችም የወጡት ከዚሁ ፓርቲ ነው።

 

ፀሐይ ጫኔ

እሸቴ በቀለ