1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍሪቃ ውስጥ የኮረና ክትባትን የማዘጋጀት ዕቅድ

ሐሙስ፣ ጥቅምት 18 2014

አፍሪቃ በቂ የኮሮና ክትባት ገና አላገኘችም። አፍሪቃ ከውጭ በሚገኘው የክትባት ርዳታ ጥገኛ በመሆኗ እስካሁን አምስት በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ብቻ ነው የኮሮና ክትባት የወሰደው። ከሰሞኑ ሁለት የመድኃኒት አምራች ኩባንያዎች ይኽን ለመለወጥ መዘጋጀታቸው ተሰምቷል። ሞደርና እና ባዮንቴክ አሁን አፍሪቃ ውስጥ ክትባቱን ለማምረት እንቅስቃሴ ጀምረዋል።

https://p.dw.com/p/42JCa
USA Zulassung des Corona-Impfstoffs von Biontech-Pfizer für fünf- bis elfjährige Kinder
ምስል PFIZER VIA REUTERS

የኮቪድ 19 ክትባት ለአፍሪቃ

የዩናይትድ ስቴትሱ የመድኃኒት አምራች ሞደርና ከሰሞኑ ይፋ እንዳደረገው አፍሪቃ ውስጥ መዋዕለ ንዋዩን አፍስሶ የኮሮና ክትባት ለማምመረት ተዘጋጅቷል። ዋና መሥሪያ ቤቱ በጀርመኗ ማይንዝ ከተማ የሚገኘው ባዮንቴክም በበኩሉ ከአሜሪካው ተባባሪው ፋይዘር ጋር በመሆን በመጪው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት አጋማሽ አፍሪቃ ውስጥ መድኃኒቱን ማምረት የሚያስችል ኩባንያ እንደሚገነባ በዚህ ሳምንት አስታውቋል። ለመጀመሪያ ጊዜም በዓመት 50 ሚሊየን የኮቪድ 19 ክትባት ለማምረት ነው የታቀደው። ለዚህም ከሩዋንዳ መንግሥት እና ከሴኔጋሉ ፓስተር ደ ዳካር ተቋም ጋር ስምምነት ተፈርሟል። የሞደርና ተባባሪ መሥራች ዶክተር ኑበር ኤፊያን አፍሪቃ ውስጥ የመድኃኒት ፋብሪካውን ለመገንባት የወሰኑት ወደፊትም ወረርሽኝ መከሰቱ ስለማይቀር አህጉሪቱ አስተማማኝ የክትባት አቅርቦት እንዲኖራት ለማስቻል እንደሆነ ተናግረዋል። ለዚህም 500 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ኩባንያቸው መድቧል።

«ለእኛ የጤና ሥርዓቱ ይዞታ ነው በጣም ወሳኙ ነገር። በተወሰኑ ሰዎች ላይ አስፈላጊውን የመድኃኒት ሙከራ ለማካሄድ የሰለጠኑ ሠራተኞች መኖርም ያስፈልጋል። ጥሩ የጤና ሥርዓት ያላቸው በዚህ ላይ ከእኛ ጋር ለመሥራት የሚፈልጉ በርካታ ሃገራት መኖራቸውን እናውቃለን። እናም ተጓዳኞችን ይዘን አስፈላጊውን ለመገንባት ወደ 500 ሚሊየን ዶላር ለዚህ ሥራ እናውላለን።»

ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ የመድኃኒት ምርምር የማካሄድ እና የማምረት አቅሙ አለ። ሴኔጋሉ ፓስተር ተቋም የቢጫ ወባ ክትባት አምርቷል፤ ሩዋንዳ ደግሞ መድኃኒት እና ክትባቶችን የማምረት ፍላቶግ እንዳላት አሳይታለች።  ባዮንቴክም በበኩሉ ዋናው ግቡ አፍሪቃ ውስጥ የሚመረቱ ክትባቶችን በመደገፍ በአህጉሪቱ የወባን ጨምሮ የክትባት አቅርቦት ዘላቂነት እንዲኖረው የማምረትን አቅም በማጠናከር የጤና ጥበቃውን ይዞታ ለማሻሻል መሆኑን የኩባንያው ተባባሪ መሥራች ዑር ሳሂን ገልጸዋል። ባለፈው ነሐሴ ወርም ባዮንቴክ ሩዋንዳ እና ሴኔጋል ውስጥ የወባ እና የቲቢ ክትባቶችን በአዲሱ የኮቪድ ክትባት ቴክኒዎሎጂ ስልት ማምረት የሚያስችሉ ተቋማትን እንደሚገነባ ይፋ አድርጓል።

Infografik Karte Covid-Impffortschritt in Afrika DE

የደቡብ አፍሪቃው ባዮባክ አፍሪቃ ውስጥ በቀድሞ አሠራር ክትባትን ከሚያመርቱ የመድኃኒት አምራቾች አንዱ ነው። አሁን በአዲሱ ቴክኒዎሎጂ ተጠቅሞ መድኃኒቶቹን ለማምረት አስፈላጊ የመሠረተ ልማት ለውጦችን እያደረገ እንደሚገኝ ኬፕታውን የሚገኘው ባዮባክ ዳይሬክተር ፓትሪክ ቲፖ ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል።

«መደረግ የሚገባቸውን የመሠረተ ልማት ለውጦች ለማከናወን በሂደት ላይ ነን፤ ይኽ ደግሞ ለቀጣይ ጥቂት ወራት ይቀጥላል። ከዚያም በፋይዘር አማካኝነት የቴክኒዎሎጂ ሽግግር ወደማድረጉ እንቅስቃሴ እንገባለን።»

በቀጣይም ለሽያጭ የሚቀርቡ ምርቶችን ለመጀመር የሚያስችል ፈቃድ ወደሰኔ እና ሐምሌ ገደማ ከሚመለከተው ባለሥልጣን በመጠየቅም በመጪው ዓመት በዚህ ወቅት ሁሉን እንደሚያጠናቅቁም አመልክተዋል። ከዚህም ሌላ ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ከደቡብ አፍሪቃው ሌላ የመድኃኒት አምራች አስፓን ጋር ክትባት ለማምረት እየሠራ ነው። ግብጽም በበኩሏ ካለፈው ነሐሴ ጀምሮ ከቻይናው የመድኃኒት አምራች ስኖቫክ ጋር በቅርበት መሥራት ጀምራለች። ጋናም እንዲሁ በሀገር ውስጥ ክትባቱን ለማዘጋጀት እንደምትፈልግ አስታውቃለች። ይኽ ሁሉ ክትባት የማምረት እንቅስቃሴ አፍሪቃ ውስጥ የሚፈለገውን ሁለት ቢሊየን ክትባት የማቅረብ አቅም ይኖረው ይሆን? በምን ያህል ፍጥነትስ ለገበያ ይቀርባል? ለብዙዎች ጥያቄ ሆኗል።

 ሸዋዬ ለገሠ/ማርቲና ሺቪኮቭስኪ 

እሸቴ በቀለ