1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍሪቃ እና ትልቆቹ ሀይቆቿ

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 19 2010

በዓለም ካሉት እንደ መለያ ድንበርም በማገልገል ላይ ካሊት ትልቆቹ እና ጥልቅ ሀይቆች መካከል የቪክቶርያ ሀይቅ፣ የማላዊ ሀይቅ ወይም የታንጋኒጋ ሀይቅን የመሳሰሉ አንዳንዶች በምሥራቅ አፍሪቃ ይገኛሉ።  እነዚሁ ሀይቆች በግዛት ይገባኛል ጥያቄ ወይም በተፈጥሮ ሀብት ቁጥጥር ለሚነሱ ውዝግቦች አዘውትረው ምክንያት ሲሆኑ ይታያል።

https://p.dw.com/p/33ia3
Afrika Viktoriasee in Kenia
ቪክቶሪያ ሀይቅምስል picture-alliance/dpa/S. Morrison

አፍሪቃ እና ትልቆቹ ሀይቆቿ


ዩጋንዳን እና ዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክን በሚያዋስነው ድንበር ላይ በሚገኘው የኤድዋርድ ሀይቅ የሚሰራ አንድ ዶይቸ ቬለ ያነጋገረው የኮንጎ አሳ አስጋሪ ታድያ ይህ ሁኔታ ምን ያህል አስቸጋሪ መሆኑን ለተናግሯል። 
«ድንበሩ መሬት ላይ ይታያል፣ ሀይቁ ላይ ግን አይታይም። ወታደሮች ታድያ ይህን ሁኔታ መነገጃ አድርገውታል። አሳ አስጋሪዎችን ከፍተኛ የገንዘብ ቅጣት ለማስከፈል እያሉ ድንበር ጥሰው እንዲያልፉ ያስገድዳሉ። »  
የዩጋንዳ ጦር ቃል አቀባይ ሪቻርድ ካሬሚሬ ግን ከጎረቤት ኮንጎ ጦር ጋር ጥሩ ግንኙነት መኖሩን እና ችግር አለመኖሩን  ነው የገለጹት። 
« እነዚህ የወንድም ሀገር ጦር ኃይላት ናቸው። እርግጥ ነው፣ በሕገ ወጥ አሳ አስጋሪዎች ተግባር አንዳንድ ችግሮች ታይተዋል። የውዝግቡ ምክንያቶች እነሱ ናቸው።»
የዩጋንዳ ወታደሮች በኤድዋርድ ሀይቅ ከኮንጎ ጦር ጋር በተጋጩ ጊዜ በኮንጎ አሳ አስጋሪዎች ላይ ተኩሰው 13 መግደላቸውን እና 92 ማሰራቸውን  ነው የኮንጎ ዜጎች የተናገሩት። ችግሩን ለመፍታት  በሁለቱ ሀገራት መካከል የተካሄደ ድርድር አንዳችም መፍትሔ ሳያስገኝ ቀርቷል። እነዚሁ ሁለት ሀገራት በሰሜኑም ሌላ የሚያዋስናቸው ሀይቅ ይጋራሉ፣ አልበርት ሀይቅ። ባለፈው ሀምሌ ወር አንድ የዩጋንዳ ፍርድ ቤት 35 የኮንጎ ዜጎችን የዩጋንዳ  በሆነው ሀይቅ ክልል በሕገ ወጥ መንገድ አሳ አስግረዋል በሚል ክስ በሶስት ዓመት እስራት እንዲቀጡ በይኗል። ይህ በዩጋንዳ እና በኮንጎ ድንበር ላይ የሚታየው ውዝግብ ትልቆቹ ሀይቆች በሚገኙበት በምሥራቅ አፍሪቃ በጠቅላላ የሚታይ ችግር መሆኑን የአፍሪቃ ተመራማሪ ፊል ክላርክ አስረድተዋል።
« ጊዜው በኤኮኖሚው ላይ ብርቱ ግፊት ያረፈበት ነው። የሁኔታውን አዳጋችነት የዩጋንዳ መንግሥትም እየተሰማው ነው። መንግሥት ከሁለቱ ሀይቆች ከሚካሄደው አሳ ማስገር ተግባር የሚገኘውን ግብር እንዳያጣ ሰግቷል። በመሆኑም የዩጋንዳ መንግሥት የኮንጎ አሳ አስጋሪዎችን በኤድዋርድ ሀይቅ፣ የኬንያውያኑን አሳ አስጋሪዎችን ደግሞ በቪክቶርያ ሀይቅ ባለው የዩጋንዳ ሀይቅ ክልል እየገቡ አሳ ያጠምዳሉ ሲል መውቀስ ይዟል። ይህ የዩጋንዳ መንግሥት የሚገኝበትን ኤኮኖሚያዊ ግፊት እና ሀይቆቹ የያዙት ትርጓሜ ምን ያህል ከፍተኛ መሆኑን የሚያሳይ ነው። »
የአልበርት ሀይቅን በተመለከተ ከጥቂት ጊዜ በፊት በተገኘው የነዳጅ ዘይት ንጣፍ ሰበብ የተነሳው ንትርክ ሌላ ችግር ደቅኗል።  ከዚህ በተጨማሪ በአስር ሺህ የሚቆጠሩ የኮንጎ ዜጎች ከሀይቆቹ በስተሰሜን ምሥራቅ ከሚገኘው ውጊያ ከቀጠለበት አካባቢ እየሸሹ ከለላ ፍለጋ ወደ ዩጋንዳ የሚገቡበት ሁኔታ ውጥረቱ እንዲካረር ሌላ ምክንያት ሆኗል።
ይህ ዘርፈ ብዙ ውዝግብ ታሪካዊ መንሥዔ እንዳለው በዩጋንዳ የሚገኙት የኮንጎ አምባሳደር ዦን ፒየር ማሳላ አስረድተዋል። 
« በትልቆቹ ሀይቆች፣ ብሎም፣ በአልበርት እና በኤድዋርድ ሀይቆች  አካባቢ ያለው ግዛት ድሮ አንድ ላይ ነበር። አውሮጳውያኑ ናቸው የከፋፈሉት። እና ችግር በሚፈጠርበት ጊዜ ያካባቢው መሪዎች በመልካም ጉርብትና መፍትሔ ሊያገኙለት ይገባል። »
ቅኝ ገዢዎች በመንግሥታት መካከል ያለውን ድንበር እንደፈለጉት አዘውትረውም  ሀይቆቹን ተከትሎ እንዲያልፍ አድርገው መከፋፈላቸውን ፊል ክላርክ አስረድተዋል። በዚህም የተነሳ ነው ዛሬም ለውዝግብ መነሻ ምክንያት የሆነው። አንዳንድ ሀገራት በግዛት ይገባኛል ጥያቄ ውዝግብ በሚነሳበት ጊዜ ይህንኑ የቅኝ አገዛዝ ዘመን ድንበርን አሰማመርን በመጥቀስ ይከrk,ራሉ። ለምሳሌ ማላዊ የ1890 ዓም የተደረሰ ስምምነትን በመጥቀስ ባለቤትነቱ የታንዛንያ የሆነውን የማላዊ ሀይቅ ሰሜናዊ ክልል የሷ እንደሆነ ትከራከራለች።  በዚያን ጊዜ ጀርመን ሀይቁን በጠቅላላ ያኔ የብሪታንያ ግዛት ለነበረችው የዛሬዋ ማላዊ ትሰጣለች። ግን ሁለቱን ሀገራት የሚለየው ድንበር በሀይቁ ውሀ ውስጥ ስለሚያልፍ ውዝግብ ተፈጠረ። እርግጥ፣ ማላዊ ጉዳዩን ለዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት እንደምታቀርብ ብትዝትም፣ ይህን ዛቻ እስከዛሬ እውን አላደረገችም። የውጭ ታዛቢዎች ንትርኩን ከፍርድ ቤት ውጭ እንዲጨርሱት  ነው የሚገፋፉት። ይሁንና፣ በሀይቁ ስር የተገኘው የነዳጅ ዘይት መገኘቱ ይህን ጥr።ት አዳጋች እንደሚያደርገው ይገመታል። መዲናዎቹ ከድነበሩ የራቁበት ድርጊትም ችግሩን አዳጋች የሚያደርግ ሌላ ምክያያትም መሆኑን ፊል ክላርክ ገልጸዋል።
« አንድ ዋነኛ ምክንያት ቅኝ ገዢዎች ዋና ከተሞቹን ከድንበሩ በጣም እንዲርቁ ያደረጉበት ጉዳይ ነው። በዚህም የተነሳ የሀገራት ማዕከላይ መንግሥታት ድንበሮቻቸውን መቆጣጠር መቻላቸውን በተመለከተ የሚነሳ ጥያቄ አለ። »
የድንበር መቆጣጠር  መቻል ባካባቢው ጥንካሬ በማሳየቱ  ሰበብ በሚነሳ ንትርክ ወቅት ጥንካሬን ለማረጋገጥ ይጠቅማል ፣ ለምሳሌ ዩጋንዳ እና ኬንያ ይገባናል የሚሉት በቪክቶርያ ሀይቅ የሚገኘው የማኒንጎ ደሴት ይጠቀሳል። የዩጋንዳ ጦር ባለፈው ሰኔ ወር ከዚሁ ደሴት አንድ የኬንያ ትምህርት ቤት ዘግተዋል።    
በግልጽ ድንበር ፈንታ እስካሁን ልል የሆነ የአጠቃቀም ደንብ ነበር  ሲሰራበት የቆየው። ይህ እንዲቀጥል በምግብ ለዓለም ድርጅት ውስጥ የዓለም አመጋገብ ፣ የግብርና ንግድ እና የባህር ጉዳዮች  ተጠሪ ፍራንሲስኮ ማሪ ተማጽነዋል።

Ugandans Kazinga Kanal Edward-See
ኤድዋርድ ሀይቅምስል picture-alliance/Anka Agency International
Karte Albertsee Uganda englisch

« አንድ አሳ አስጋሪ እስከተመዘገበ እና ለሁለት ቀናት የአሳ ማስገር ተግባር ግብር እስከከፈለ፣ እንዲሁም፣ አንድ ጀልባ እስካለው ድረስ ችግር አልነበረም። በ2018 ዓም መጀመሪያ ላይ ዩጋንዳ ውስጥ ውዝግብ ከተፈጠረ በኋላ ግን ሁኔታው ተቀይሯል። ።»
ይህንን ደንብ አንድ የአሳ አስጋሪዎች ያቋቋሟቸው የሀይቅ ዳርቻ ተቆጣጣሪ ቡድኖች ሲከታተሉ ነበር። እነዚህ ቡድኖች ራሳቸውን መቼ፣ ምን ያህል እና በምን ዓይነት ሁኔታ  አሳ ማስገር እንደሚችሉ በመከታተል  የራሳቸውን እና የልጆቻቸውን ጥቅም ሊያስከብሩ ይችላሉ። 
ያም ሆኖ በሀይቅ ዳርቻ ተቆጣጣሪ ቡድኖች  መደዳ ሕገ ወጥ ማስገር  እና ሙስና  ተስፋፍቷል በሚል ቅሬታ ከተሰማ በኋላ የዩጋንዳ ፕሬዚደንት ሙሴቬኒ ርምጃ ወስደው የተቆጣጣሪ ቡድኖችን  ከግዛታቸው አንስተዋል፣ የዩጋንዳ ጦር  በአባቢው፣ ማለትም በአልበርት እና በኤድዋርድ ሀይቆች  ጭምር የኃይል ርምጃ በታከለበት ጠንካራ ቁጥጥር በማድረግ ላይ ይገኛሉ። በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ  በመቶ የሚቆጠሩ ጀልባዎች ተቃጥለዋል፣ ብዙ የአሳ ማስገሪያ መረቦች ወድመዋል።   ይህንን የመንግሥቱን ርምጃ አንዳንድ አሳ አስጋሪዎች ጥሩ ሆኖ አግኝተውታል፣ ምክንያቱም ከመጠን ባለፈ ሁኔታ እና በሕገ ወጡ የአሳ ማስገር ተግባር የመመናመን ስጋት የተደቀነባቸው የአካባቢው ሀይቆች የአሳ ይዘት መጠን በዚህ ዓይነት ርምጃ ሊያገግም እንደሚችል ያምናሉ። ይሁን እንጂ፣ ብዙዎች አሳ አስጋሪዎች ራሳቸውን ይቆጣጠሩበት የነበረው የቀድሞው አሰራር እንዲመለስ መፈለጋቸውን አጉልተዋል። የዩጋንዳ ጦር የሚከተለው ጠንካራ ርምጃ ጎጂ ውጤት ሊያስከትል እንደሚችል ማሪ አስጠንቅቀዋል።
« በዚህ ድህነት በጎላበት ሁኔታ ለመኖር የሚያስችል የአሳ መጠን ማስገር መቻል አለበት። ይህ በቪክቶርያ እና በኤድዋርድ ሀይቆች ዳርቻ መረባቸውን ለሚጥሉ ሴቶች  ጠቃሚ ነው። ይህን ማድረግ ካልቻሉ ድህነት ይስፋፋል፣ ረሀብም ይከሰታል። »
በርዋንዳ እና በዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክ ድንበር መካከል የሚገኘው እና በተለይ ውዝግብ የበዛበት የኪቩ ሀይቅ ለዚህ ዓይነቱ ችግር መፍትሔ ማግኘቱን /// ፊል ክላርክ ገልጸዋል። በኪቩ ሀይቅ፣ በተለይ በርዋንዳ በኩል ባለው የሀይቁ ከፊል  ግዙፍ የሜታን ጋዝ ንጣፍ መኖሩ ከጥቂት ዓመታት በፊት ከታወቀ ወዲህ፣ ርዋንዳ ጋዙን እንድታወጣ፣ ከጋዙ ሽያጭ የሚገኘውን ትርፍ ግን ሁለቱ ሀገራት እንዲከፋፈል ስምምነት ደርሰዋል። 
« የተፈጥሮ ሀብት አስተዳደር ወጥነት ያለው እንዲሆን እና ውዝግቡም በድንበሩ አካባቢ እንዳይስፋፋ ለማረጋገጥ የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት በዚሁ ድንበር አካባቢ በመመላለስ ተከታታይ የሆነ ግንኙነት ሲያደርጉ ተመልክተናል። »
ፊል ክላርክ እንደታዘቡት፣ የብዙ ዓመታት የውዝግብ ታሪካቸውርዋንዳ እና ኮንጎ  ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡ ያደረጋቸው ይመስላል። 

ፊሊፕ ዛንድነር/አርያም ተክሌ

እሸቴ በቀለ