1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከህይወት ማጥፋት ሙከራ እስከ በራስ መተማመን

ዓርብ፣ የካቲት 25 2014

የዛሬው የወጣቶች ዓለም እንግዳችን ቁመቱ አጭር በመሆኑ የተነሳ ብዙ ውጣ ውረዶችን እና ሥነ ልቦናዊ ችግሮችን ያሳለፈ ወጣት ነው። ዛሬ ላይ በራስ መተማመኑን አጠንክሮ ለሌሎች  ሰዎች አርዓያ መሆን ጀምሯል። ምን ገጠመው እንዴትስ ተወጣው?

https://p.dw.com/p/47wWs
Äthiopien | Kleinwüchsigkeit
ምስል privat

ፈይሳል መሀመድ ራሱን ማሸነፍ ላይ ለመድረስ ብዙ አመታት ፈጅቶበታል። ብዙዎች የሚያውቁት በቅፅል ስሙ ዴራ መጋላ ገለምሶ በሚል መጠሪያው ነው። የገለምሶ ረዥሙ ልጅ። ሀቁ ግን የ 32 አመቱ ወጣት ቁመት አንድ ሜትር ገደማ ነው። ይህም አጭር ቁመት ወይም በህክምና አጠራር ድዋርፊዝም ካለባቸው ሰዎች ተርታ ያካትተዋል።  ከዓለም ሕዝብ ሶስት በመቶ ያህሉ ሰዎች ቁመታቸው ካደጉ በኋላ ከ 147 cm እንደማይበልጥ ይታመናል። ኢትዮጵያ ውስጥ ምን ያህል ሰዎች አጭር ቁመት እንዳላቸው በግልፅ የተቀመጠ መረጃ የለም። ለምሳሌ ያህል  በዚህ ከ 83 ሚሊዮን በላይ ነዋሪ ባላት ጀርመን 100 ሺ ገደማ የሚሆኑ አጭር ቁመት ያላቸው ሰዎች ይኖራሉ።  አጭር ቁመት ያላቸው ሰዎች በቁጥር አናሳ መሆናቸውም ለመገለል እና ለመጨቆን ምክንያት ሆኗቸዋል።  « ህፃን ሆኜ በጣም የተጎዳው ሰው ነኝ። ሰፈር ውስጥ የሰው አመለካከት በጣም አዕምሮ ይነካል። ቤተሰብም ይጨነቃል። እኔም በዛ ምክንያት ብዙ ጉዳት ደርሶብኛል»    ሲል ዴራ የገጠመውን ያብራራል።
ምዕራብ  ሀረርጌ ገለምሶ ከተማ ተወልዶ ያደገው ዴራ በዚህ ምክንያት ትምህርቱን እስከ ማቋረጥ ደርሶ ነበር። ኋላ ግን በቤተሰብ ግፊት ተመልሶ ለመቀጠል ቻለ። ተመረቀ። ስራም ያዘ። ትዳርም መሠረተ ። የቁመቱ አጭር መሆን ግን ይበልጥ መነጋገሪያ ሆኖ ቀጠለ። ባለቤቱ እንደሱ አጭር አልነበረችም። « በጣም ጨለማ ህይወት ነው ያሳለፍኩት። » ይላል ራሱን ለማጥፋት ሁሉ ፈልጎ የነበረው ፈይሳል።
አባስ አብዱ ናስር የዴራ አብሮ አደግ እና አሁን ላይ ስራአስኪያጁ ነው። « ዴራ በራሱ ተፈጥሮ ያፍርና ይስቁብኛል በሚል ከቤት መውጣት የማይፈልግ ፤ የታችነት የሚሰማው ነበር።» ሲል አብሮ አደጉን ይገልፃል። አባስም ጓደኛው በጥበብ ስራ እንዲሳተፍ አበረታታው።  ዴራ አስተማሪ እና ምክር አዘል የሆኑ ቪዲዮዎችን መስራት ሲጀምርም በራስ መተማመኑ መጨመር ጀመረ። ሌሎች ተመሳሳይ ፈተና የገጠማቸው ኢትዮጵያውያንንም መተዋወቅ ቻለ። « አዲስ አበባ አካባቢ በአጭርነቱ ለ 22 ዓመት ያህል እቤቱ የተቀመጠ ልጅ ልናገኝ ችለናል» ይላል ዴራ። በጠቅላላ ወጣቶቹ እስካሁን 12 አጭር ቁመት ያላቸው ሰዎችን ሊያገኙ እና ሊያበረታቱ ችለዋል። 
ሰዎች ሲወለዱ አንስቶ ድዋርፊዝም ወይም አጭር ቁመት ሊኖራቸው ይችላል። የህክምና ባለሙያዎች እንደሚሉት የእጥረቱ ምክንያት እና አይነት ይለያያል። በከፊል በህክምና ድጋፍ ሰዎች እድገታቸው እንዲስተካከል ማድረግም ይቻላል። ድዋርፊዝም ያለባቸው ሰዎች እንደማንኛውም ሰው የአዕምሮ እድገት ያላቸው ሲሆኑ፣ የመኖር እድሜያቸውም አብዛኛውን ጊዜ መደበኛ ቁመት ካላቸው ሰዎች የተለየ እንዳልሆነ የህክምና ጥናቶች ይጠቁማሉ። ይህንን ማወቁም ለዴራ ጥንካሬ ሰጥቶታል። ለውጡንም ጓደኛው አባስ ከጎኑ ሆኖ ሊታዘብ ችሏል። « እየተሻለው መጣ። ስራችንም መብዛት ጀመረ። ለሌሎችም ሞራል መሆን አለብን ብለን እነዚህ ሰዎችን ማሰባሰብ ጀመርን። » ይላል አባስ። 
ፈይሳል (ዴራ) በርቀት ትምህርት በዲግሪ ተመርቆ በአሁኑ ሰዓት በአንድ የመንግሥት መስሪያ ቤት የቢሮ ሰራተኛ እንደሆነ ገልፆልናል። ጎን ለጎን ደግሞ ከጓደኛው አባስ ጋር ሆኖ የጥበብ ስራውን መቀጠል ይፈልጋል። የእምነት ተቋማት እና ጉዳዩ  ይመለከተናል የሚሉ አካላትም ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ ያሳስባል። የዴራን ህይወት ብቻ ሳይሆን ወደፊትም የብዙ ድጋፍ የሚሹ ኢትዮጵያውያንን ህይወት መቀየር የሚሻው አባስም በዚሁ ስራው መቀጠል ይፈልጋል። 

Äthiopien | Kleinwüchsigkeit
ፈይሳል እና አባስ የተቸገሩ ሰዎችንም ይረዳሉምስል privat
Äthiopien | Kleinwüchsigkeit
እስካሁን 12 አጭር ቁመት ያላቸው ሰዎችን ሊያገኙ እና ሊያበረታቱ ችለዋልምስል privat

ልደት አበበ

እሸቴ በቀለ