1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አጣየ ከተማ የጀመረዉ ጥቃት አሳሳቢ ሆንዋል  

ሰኞ፣ መጋቢት 13 2013

በሰሜን ሸዋ ዞን አጣየና አካባቢ ከተሞችና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ጂሌ ጥጋ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች ወደ ህዝብ ግጭት እያመሩ እንደሆነ የአካባቢው አስተዳዳሪዎች አመለከቱ። የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ገ/ጻዲቅም አካባቢውን እያተራመሰና እያጠቃ ያለው የታጠቀና የተደራጅ ኃይል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

https://p.dw.com/p/3qxej
Karte Sodo Ethiopia ENG

በአጣየ ከተማ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ያደረገው የታጠቀ፣ የሰለጠነና የተደራጀ ሰራዊት ነው

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አጣየ ከተማ ባለፈው አርብ ጀምሮ የተነሳው ግጭት አድማሱን አስፍቶ በተለያዩ የሰሜን ሸዋ ዞንና በዚሁ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር አካባቢዎች ጉዳት ማድረሱን ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ በሰሜን ሸዋ ዞን የአጣየ ከተማ ነዋሪ እንደሚሉት ሰሞኑን በአጣየ ከተማ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ያደረገው የታጠቀ፣ የሰለጠነና የተደራጀ የአነግ ሸኔ ሰራዊት ነው፡፡ የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ገ/ጻዲቅም ቢሆኑ አካባቢውን እያተራመሰና እያጠቃ ያለው የታጠቀና የተደራጅ ኃል መሆኑንና ህይወት መጥፋቱንና ንብረት መውደሙን ተናግረዋል፡፡

በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ አቶ አህመድ ሀሰን ግን በአካባቢው የኦነግ ታጣቂ ጥቃት አድርሷል የሚለውን አይቀበሉም፣ ይልቁንም የአንድ ግለሰብን ግድያ ተከትሎ የሀይማኖትና የብሔር ግጭት ለማድረግ የሞከሩ ሰዎች በቀሰቀሱት ፀብ በህዝቦች መካከል የተፈጠረ ግጭት እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡ በአካባቢው የኦነግ ሸኔ ሰራዊት ተደጋጋሚ ጥቃቶች ሲያደርግ መቆየቱን የሚናገሩት የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ያሁኑ ክስተትም በተጨባጭ መረጃ ይፋ የሚሆን እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡

የፌደራል የፀጥታ ኃይል አሁን ወደ ቦታው የደረሰ ቢሆንም ችግሩን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር እንዳልተቻለ ያመለከቱት አቶ ታደሰ ግጭቱ ወደ ህዝብ ለህዝብ እየተለወጠ ነው ብለዋል፡፡በተፈጠረው ግጭት በሁለቱም ህዝቦች መካከል ቁጥሩ ያልታወቀ ህይወት አልፏል ንብረትም ወድሟል ሲሉ የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ አቶ አህመድ ሀሰን ያብራራሉ፡፡

የሰሜን ሸዋ ዞን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ ሳአዳ ኢብራህም በግጭቱ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ገልፀዋል፡፡በአሁኑ ሰዓት መንግስት ችግሩን ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑን አቶ አህመድ ተናግረዋል፡፡ ከአጣየ ሆስፒታል ትናንት ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው በሆስፒታሉ የቆሰሉ 45 ሰዎች እየታከሙ ሲሆን ሌሎች 7ቱ ደግሞ ህይወታቸው አልፏል፡፡

ዓለምነው መኮንን

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ