1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚኢትዮጵያ

 አዳዲሶቹ መተግበሪያዎች የኢትዮጵያን የሙዚቃ ገበያ ይታደጉታል?

ረቡዕ፣ መጋቢት 15 2013

የኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ የገባበትን የግብይት ችግር በመፍታት የፈጠራ ባለሙያዎች የሚገባቸውን ክፍያ እንዲያገኙ የታቀዱ ሁለት መተግበሪያዎች ሥራ ላይ ውለዋል።800 ገደማ ድምፃውያን ሥራዎቻቸው በመተግበሪያ ለሽያጭ እንዲቀርብ ውል መግባታቸውን የተናገረው የአውታር መልቲሚዲያ ሥራ አስኪያጅ ጆኒ ራጋ ደንበኞቻቸው 100 ሺሕ መድረሳቸውን አስረድቷል

https://p.dw.com/p/3r4BX
Start-ups setzen auf Streaming, um die äthiopische Musikindustrie zu retten
ምስል Eshete Bekele Tekle/DW

ከኤኮኖሚው ዓለም፦ አዳዲሶቹ መተግበሪያዎች የኢትዮጵያን የሙዚቃ ገበያ ይታደጉታል?

አውታር መተግበሪያ ከሁለት አመታት ገደማ በፊት በአራት ቋንቋዎች ተዘጋጅቶ ሙዚቃ ለመሸጥ ሥራ ሲጀምር በኢትዮጵያ በአይነቱ የመጀመሪያ ነበር። ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ኤልያስ መልካ፤ ዮሐንስ በቀለ (ጆኒ ራጋ) ኃይለሚካኤል ጌትነት (ኃይሌ ሩትስ) እና ዳዊት ንጉሴ የተባሉ የሙዚቃ ባለሙያዎች በጥምረት ያቋቋሙት አውታር መልቲ-ሚዲያ የተባለ ኩባንያ በታላቅ ተስፋ መተግበሪያውን ቅንጡ የእጅ ስልኮች ለሚጠቀሙ ኢትዮጵያውያን ይፋ ቢያደርግም ሥራው እንደታሰበው አልሰመረም። 

"በግንቦት 2019 ብንጀምርም ከዚያ በኋላ የመጀመሪያው መተግበሪያ ብዙ ቴክኒካዊ ፈተናዎች ነበሩት። እሱን አስተካክለን ከእንደገና ሌላ መተግበሪያ አዘጋጅተን አሁን ያለፈው መስከረም ነው በትክክል የጀመርንው" ሲል የአውታር መልቲ-ሚዲያ ሥራ አስኪያጅ ዮሐንስ በቀለ በመድረክ ስሙ ጆኒ ራጋ ሒደቱን ለዶይቼ ቬለ አስረድቷል። 

ይኸ መንገራገጭ ግን የአውታር መልቲ-ሚዲያ ሰዎችን የሚያቆም አልሆነም። የኩባንያው ሥራ አስኪያጅ ዮሐንስ በቀለ (ጆኒ ራጋ) እንደሚለው የኢትዮጵያ የሙዚቃ ባለሙያ የሚገባውን ፍትሐዊ ክፍያ እንዲያገኝ ማድረገ ከተፈለገ ሌላ "አማራጭ መንገድ" አልነበረም። 

"በሲዲ በኩል የመጣው የገበያ ሥርዓት ራሱን አጥፍቶ፤ ፕሮዲውሰሮች ከኢትዮጵያ ምድር ጠፍተው ከኋላ ደግሞ የብዙ ባለሙያዎች መብቶች ተዘርፈው፤ ባለ መብት ነን የሚሉ ሰዎች ከሰሩት ሥራ የሚያተርፉበት መንገድ ተዘግቶ አጭበርባሪ ነጋዴዎች ብቻ የሚያተርፉበት ሥርዓት ይዞ ነው የመጣው" የሚለው ጆኒ ራጋ በቴክኖሎጂው ረገድ በአመታት የታየው ለውጥም በኢንዱስትሪው ተፅዕኖ እንዳሳረፈ ያምናል።  

ጆኒ "በጣም ብዙ ሥራዎችን የሰሩ ትላልቅ የሙዚቃ ሰዎች በታመሙ ቁጥር ብር እየሰበሰብን ፤እየረዳን እና እየተረዳን የቆየንበት፤ ሙዚቃ ራሱን ያልቻለበት፤ አንድ ሰው የሰራውን ሙዚቃ ሸጦ የማያተርፍበት፣ ብዙ ሰው ከሙዚቃ ገበያ የወጣበት ቦታ ላይ ነው ያለንው። አገሪቷ በሙዚቃው ዙሪያ ከዚህ በላይ ልትወድቅ አትችልም። የባለሙያዎች መብት የማይከበርበት፣ የሚጣስበት፤ ሙዚቃው አለ የማይባልበት ደረጃ ላይ ነው የቆየንው። እኔን ጨምሮ ብዙ የሙዚቃ ሰዎች ከሙዚቃ የራቁት በዚያ ምክንያት ነው" ሲል ውስብስብ የዘርፉን ችግሮች እየነቀሰ የግብይት ሥርዓቱን ከመቀየር ውጪ አማራጭ እንዳልነበር ይሞግታል። 

Deutschland Hailu Mergia in Köln
የኃይሉ መርጊያ ተወዳጅ የሙዚቃ ሥራዎች ዩቲዩብን ጨምሮ በተለያዩ የኢንተርኔት ገፆች በሕገ ወጥ መንገድ ተሰራጭተው ይገኛሉ። የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ከገጠሟቸው ፈተናዎች አንዱ ይኸን መሰሉን ስርጭት ማስቆም ይሆናል። ምስል DW/T. Waldyes

የኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ እንዲህ አይነት ውስብስብ የግብይት ማጥ ውስጥ የገባው ቀደም ብሎ ነው። የሙዚቃ ገበያው ንቁ በነበረባቸው አመታት የዜማ እና ግጥም ደራሲዎችን አሰባብስቦ፣ ድምፃዊ እና ባንድ ለይቶ፣ ገንዘብ መድቦ ሙዚቃ የመሥራቱ ሚና በአሳታሚዎች የሚከወን ነበር። የኢትዮጵያ የሙዚቃ ዘርፎች ማሕበራት ኅብረትን በፕሬዝዳንትነት የሚመሩት አቶ ዳዊት ይፍሩ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት ገበያው ይከተል የነበረው አሰራር ከሙዚቃ ባለሙያዎች ይልቅ ለአሳታሚዎች ያደላ ነበር።  

"አሳታሚው ነጋዴ ነው። ነጋዴ ሁል ጊዜ ከትርፉ ጋር ነው የሚሔደው። `ያዋጣኛል፣ ያተርፈኛል` የሚለውን ዜማ እና ግጥም በራሱም ይሁን ከሰው ጋር ተማክሮ ያገኛል። ከዚያ በኋላ `በአሁኑ ጊዜ ተደማጭነት አለው` ብሎ ያመነበትን ድምፃዊ ካገኘ የዛን ጊዜ ገንዘቡን ወደ ማውጣት ይሔዳል። ገንዘቡን አውጥቶ በአግባቡ ተቀርፆ ለሰው ጆሮ ተደማጭ እንዲሆን ለማድረግ በዘመኑ ተደማጭነት ካለው ባንድ ጋር መነጋገር አለበት። ከዚያ ባንድ ጋር ተነጋግሮ ከፍሎ ያሰራል። ያ ሥራ ከተሰራ በኋላ ማንኛቸውም ከዚያ በኋላ የሚከፈላቸው ነገር የለም። ለዚያች ሥራ ብቻ ይከፈላል። ሁሉም የየድርሻቸውን ይወስዳሉ። ከዚያ በኋላ ያለው ያሳታሚው ሥራ ነው። እንደ ዕድል ሆኖ በጣም የተወደደ ከሆነ ይኸንን ያሳተመው ሰውዬ በጊዜውም ተጠቃሚ ይሆናል። ለሚቀጥሉትም አመታት በሙሉ እያሳተመ የመሸጥ መብት አለው" ሲሉ የቀደመው የሙዚቃ ገበያ ይከወን የነበረበትን አካሔድ አስረድተዋል። 

የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች የሚገባቸውን ጥቅም ለመጠየቅ ገፋ አድርገው አደባባይ የወጡት በ1990ዎቹ ነበር። በወቅቱ የሙዚቃ ሲዲዎች በሕገ-ወጥ መንገድ እየተባዙ ገበያውን ማጥለቅለቃቸው ለተቃውሞው አንደኛው ምክንያት ነበር። አቶ ዳዊት ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት ጊዜው የቀደመው ሥርዓት አግባብ አለመሆኑን ባለሙያዎቹ የተረዱበት ስለ ቅጂ እና ተዛማጅ መብቶች ጽንሰ-ሐሳብም ግንዛቤ ያገኙበት ነበር።  

አቶ ዳዊት  "ብዙዎቹ ሥራ ይሰራሉ፤ ይሸጣል። አምስት ሺህ ብር የሚከፈለውም ይከፈላል፤ አስር ሺሕም የሚከፈለው ይከፈላል። ያቺን ከጨረሰ በኋላ ሁለተኛ ሥራ ካልሰራ ጾሙን ማደሩ ነው። የኮፒ ራይት መብት የሚባለው ጽንሰ ሐሳቡንም ያወቅንው የዛን ጊዜ ነው። በ1990ዎቹ አካባቢ ብዙ ሰላማዊ ሰልፍ ተደረገ። ብዙዎቹ `በሥራችን ተጠቃሚ አይደለንም` የሚል የመብት ጥያቄ አነሱ። የቅጂ እና ተዛማጅ መብቶች አዋጅ ወጣ" ይላሉ። 

የፈጠራ ባለቤትነትን ያስከብራል ተብሎ ይጠበቅ የነበረው የቅጅ እና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ ሕግ የወጣው ከሙዚቃ ባለሙያዎቹ ግፊት በኋላ በ1996 ዓ.ም. ነው። እንደተጠበቀው ግን ሕጉ በተጨባጭ የቀየረው ነገር እንዳልነበረ ባለሙያዎቹ ይናገራሉ። ጆኒ ራጋ በተለይ ከአዋጁ መውጣት በፊት በተደረጉት ሰልፎች የቀረበው ጥያቄ ከባለሙያዎች ይልቅ ለሙዚቃ አሳታሚዎች ጥቅም መከበር ያዘነበለ ነበር ሲል ይተቻል።

"በሰልፉ መባል የነበረበት የቅጂ እና ተዛማጅ መብቶች ይከበሩ ነበር" የሚለው ጆኒ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለየው ኤልያስ መልካ ጋር በመተባበር የሙዚቃ ሥራዎች በየገበያ ማዕከሉ የሚሸጡበት "አገር ኦሪጅናል" የተባለ የግብይት ሥርዓት ለመጀመር ሙከራ አድርጎ ነበር። የባለሙያዎቹ ሙከራ ግን በተለያዩ ምክንያቶች ሳይሳካ ቀርቷል። ባለሙያዎቹን የወተወቱት እና የሮያሊቲ ክፍያ እንዲፈጸም የሚያስገድደው ማሻሻያ አዋጅ የወጣው ግን ዘግየት ብሎ በ2007 ዓ.ም. ነው።

ጥቅማቸውን ለማስከበር ባለሙያዎቹ የሙያ ማኅበራት ጭምር አቋቁመዋል። ተራው ግብይቱን መቀየር ነው። "የሞተ ገበያ ላይ ያለን ብቸኛ አማራጭ አዲስ ነገር መፍጠር" ነው የሚለው ጆኒ ራጋ አውታርን በመሳሰሉ መተግበሪያዎች ሙዚቃን ለሽያጭ በማቅረብ ግብይቱን ለመቀየር መቁረጣቸውን አስረድቷል። 

Tewodros Kassahun Musik Äthiopien
ቴዲ አፍሮ በሚለው የመድረክ ስሙ ይበልጥ የሚታወቀው ቴዎድሮስ ካሳሁን የሙዚቃ አልበምምስል DW/L.Abebe

በአውታር አንድ ነጠላ ሙዚቃ በሶስት ብር፤ በሲዲ 50 ብር የሚከፈልበት ሙሉ አልበም ደግሞ በ15 ብር ይሸጣሉ። ጆኒ እንደሚለው ሙሉ አልበም ከሥራው ክብደት አኳያ የአውታር መተግበሪያ "የግዴታ አልበም እንዲገዛ የሚያበረታታ መሆን ነበረበት።" 

"አርቲስት፣ [የፈጠራ ሥራ] አመንጪ፣ ሙዚቀኛ የምንለው አካል በቀላሉ የሰራውን ሥራ ኪሱ ሳይጎዳ ለገበያ የሚያቀርብበት፣ ተጠቃሚውም በፈለገው ጊዜ፣ በፍጥነት፣ በቀላል እና በርካሽ የፈለገውን ሙዚቃ የሚያገኝበት፣ ያም ሲሸጥ አርቲስቱ ብዙ ትርፍ የሚያገኝበት፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ 30 አመት እና 40 አመት ወደ ኋላ እየተመለሰ ይኸን ሙዚቃ የሰራው ሰው ማነው ተብሎ ለሰራው ሰው፤ እሱ ባይኖርም ለወራሾቹ መብት የሚተላለፍበትን መንገድ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው አውታር ያመጣው" ይላል ጆኒ መተግበሪያው ያመጣውን ለውጥ ሲያስረዳ። 

ኢትዮጵያውያን ደንበኞች መተግበሪያውን ወደ እጅ ስልኮቻቸው ጭነው ከተመዘገቡ በኋላ በኢትዮ-ቴሌኮም በሚገዙት ካርድ ወይም ከቴሌኮም አቅራቢው ባላቸው አገልግሎት በኩል ሙዚቃዎች መሸመት ይችላሉ። ከዚያ ባሻገር አሞሌ እና ሔሎ ካሽን በመሳሰሉ የባንኮች የክፍያ ሥርዓቶችም ከአውታር ሙዚቃ መግዛት ይቻላል። ከኢትዮጵያ ውጪ ለሚኖሩ ደንበኞች ማስተር ካርድ እና ቪዛን በመሳሰሉ የክፍያ ሥርዓቶች ደንበኞች ለሚገዟቸው ሙዚቃዎች ክፍያ እንዲፈጽሙ የተመቻቸ ቢሆንም ጆኒ መተግበሪያው ሊስተካከሉ የሚገቡ እንከኖች እንዳሉት አስረድቷል። 

እንደ ጆኒ አባባል ከሆነ የገበያውም አቀባበል መልካም ነው። "ገበያው በጣም ክፍት ነበር። እኛ ስንጀምር በ20 ቀናት ነው ወደ 20 ሺሕ ደንበኛ ያገኘንው። ከዚያ በኋላ መተግበሪያው ቴክኒካዊ ችግሮች ገጥመውት ቆመ። አሁን ወደ 100 ሺሕ አካባቢ ደንበኞች አሉን። በ2021 ዓ.ም. አንድ ሚሊዮን ደንበኛ እንዲኖረን አቅደን እየሰራን ነው።"

አውታር ደንበኞቹን አንድ ሚሊዮን ለማድረስ በርካታ ፈተናዎች ይጠብቁታል። በተለይ መተግበሪያው ይታዩበታል የተባሉ ቴክኒካዊ ችግሮችን በዘላቂነት መቅረፍ እና ለአጠቃቀም ቀላል ማድረግ ቀዳሚ ሊሆኑ እንደሚገባ የተጠቀሙበት ሁለት የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ለዶይቼ ቬለ ጥቆማ ሰጥተዋል።

ኩባንያው ከ800 በላይ ሥመ-ጥር እና ወጣት ሙዚቀኞች በመፈራረም ሥራዎቻቸው በመተግበሪያው ለሽያጭ እንዲቀርብ ማድረግ እንደቻለ የገለጸው ጆኒ "በምንም አይነት ሌብነትን የማያበረታታ [መተግበሪያ ነው።] ለአንድ ሰው መላክ ስትፈልግ ኢንክሪፕትድ ነው። በተዓምር አይልክልህም። ከፍለህ ነው የምትገዛው። [ግብይቱ] በጣም ግልጽ ነው። ሰዉ ቤቱ ቁጭ ብሎ በስልኩ ምን ያክል እንደሸጠ የሚቆጣጠርበት መንገድ አለው" ይላል።  

Symbolbild Musik-Streaming
አፕል እና ስፖቲፋይን የመሳሰሉ ኩባንያዎች ይፋ ያደረጓቸው መተግበሪያዎች ባደጉት አገሮች ሰዎች ሙዚቃ የሚሸምቱበትንም ሆነ የሚያደምጡበትን መንገድ ቀይረውታል። ምስል picture-alliance/AP Photo/J. Kane

እንደ አውታር ተመሳሳይ ግልጋሎት ለመስጠት በቅርቡ ይፋ የሆነው ባና የሙዚቃ መተግበሪያም በገበያው ይገኛል። ማድ ቴክኖሎጂስ የተባለ ጀማሪ ኩባንያ ከካዛና ግሩፕ በመተባበር ያዘጋጀው መተግበሪያ ሥራ የጀመረው ድምፃዊ ጥላሁን ገሠሠ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለየ ከ12 አመታት ገደማ በኋላ ለአድማጭ የቀረበውን የሙዚቃ አልበም ለሽያጭ በማቅረብ ነበር።  የባና ሙዚቃ የሽያጭ ኃላፊ ብሌን መኮንን ባለሙያዎች ሥራዎቻቸውን በቀላሉ ለገበያ አቅርበው ግልጽ በሆነ የሽያጭ ሥርዓት ተገቢውን ክፍያ እንዲያገኙ ማስቻል ዋና ዓላማቸው መሆኑን ለዶይቼ ቬለ ተናግራለች። 

ብሌን መኮንን  "አሁን ከአርቲስቶች ጋር ሥምምነት በመፈራረም ላይ ነን። ስለዚህ የተጨማሪ አርቲስቶች ሥራዎች በመተግበሪያው ወደ ፊት ይቀርባሉ። በክፍያ ከኢትዮ-ቴሌኮም ጋር ነው ሥምምነት ያለን። አሁን ለምሳሌ የጥላሁን አልበም 50 ብር ነው። ስለዚህ ስልክህ ላይ መጀመሪያ 50 ብር መኖር አለበት። ከዚያ በኋላ ዳውንሎድ በተኑን ሲጫኑ 50 ብር ይቆርጣል። ከዚያ በኋላ ኦፍላይንም ሆነ ኦንላየን ለማድመጥ ይቻላል" ስትል የባና ደንበኞች እንዴት ከሙዚቃ መተግበሪያው እንደሚሸምቱ አብራርታለች። 

በባና መተግበሪያ ሸማቾች የገዙትን ሙዚቃ በስልኮቻቸው የኢንተርኔት ግልጋሎት ሳይኖር ጭምር ማድመጥ ይችላሉ። ይሁንና የሙዚቃ ሰነዱን እንደ አውታር ሁሉ ሰዎች አንዱ ለሌላው መላክ አይችልም። ይኸ የባለሙያዎቹን መብት ለማስጠበቅ እና ሕገ-ወጡን ዝውውር ለመግታት ያለመ እርምጃ ነው።

እሷ ራሷ ድምፃዊት የሆነችው ብሌን ባና እና አውታርን የመሳሰሉ መተግበሪያዎች ለባለሙያዎቹ ሊሰጡ ስለሚችሉት ጥቅም ጥርጣሬ ባይኖራትም ገበያውን በማለማመድ ረገድ ግን ብዙ ሊሰራ እንደሚገባ ግን ተናግራለች። "እውነት ለመናገር በጣም ብዙ የሚሰራ ሥራ አለ ብዬ አስባለሁ። ለእነደዚህ አይነት ነገር ሰው አዲስ ነው። የዩቲዩብ ገበያ የኢትዮጵያን ሰው ዘልቆ እስኪገባ በጣም ቆይቷል። አሁን ግን ሰው ሁሉ ዩቲዩብ ላይ ገብቶ ሙዚቃ መስማት ጀምሯል። ይኸ ግን ረዥም ጊዜ ወስዷል። በተመሳሳይ ይኸ የሙዚቃ መተግበሪያዎች በደንብ ሰው እስኪለምደው በደንብ ሥራ መሰራት እንዳለበት ነው የተረዳንው።"

የኢትዮጵያን ሙዚቃ በተለያዩ ዘመናት ጠንቅቀው የሚያውቁት የሮሐ ባንዱ አቶ ዳዊት ግብይቱ ለገባበት ቅርቃር መፍትሔ ለማበጀት ባለሙያው ሊታገል እንደሚገባ በአፅንዖት ያስረዳሉ። "ተበደልኩ" እያለ የሚያለቅሰው ባለሙያ ችግሩን ለመቅረፍ "በጋራ እንስራ ሲባል ብቅ አይልም" እያሉ የሚሸነቁጡት አቶ ዳዊት በተለይ ከወጣቶች ብዙ ይጠብቃሉ።

እሸቴ በቀለ 
ነጋሽ መሐመድ