1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

አዲሶቹ የኮቪድ-19 ክትባቶች

ረቡዕ፣ ኅዳር 9 2013

የኮሮና ወረርሽኝ ከተከሰተ ወዲህ  የመከላከያ ክትባት ለማግኘት  በዓለም ላይ በርካታ ምርምሮች በመካሄድ ላይ ይገኛሉ።ጥቂቶቹም ውጤታማ መሆናቸውን እየገለፁ ነው።

https://p.dw.com/p/3lWRX
Deutschland | Coronavirus | Impfstoff Schott
ምስል Schott

በአዳዲሶቹ የኮሮና ክትባቶች ያልተመለሱ ጥያቄዎች

ከነዚህም መካከል ያለፈው ሳምንት  የጀርመኑ ባዮንቴክና የአሜሪካው ፌዘር  ኩባንያ፤በዚህ ሳምንት ደግሞ  ሞደርና የተባለው የአሜሪካ የመድሃኒት አምራች ኩባንያ ለኮሮና ተዋህሲ መከላከያ ክትባት ማግኘታቸውን ይፋ አድርገዋል።
የጀርመኑ ባዮንቴክና የአሜሪካው ፊዘር ኩባንያዎች  ውጤታማ የሆነ የኮሮና ተዋህሲ ክትባት በጋራ ማግኘታቸውን ያለፈው ሳምንት ገልፀው ነበር።የመድሃኒት አምራች ኩባንያዎቹ ይህንን ከገለፁ ከሳምንት በኋላ ደግሞ ሞደርና የተባለው ሌላው የአሜሪካ የመድሃኒት አምራች ሌላ የኮሮና ተዋህሲ መከላከያ ክትባት ማግኜቱን በሳምንቱ መጀመሪያ አስታውቋል።ሩሲያ በበኩሏ« ስፑኒክ አምስት» የተባለውን የኮሮና መከላከያ ክትባት ውጤታማነት በመግለፅ ላይ ትገኛለች።
ለመሆኑ እነዚህ ክትባቶች  ለሁሉም እኩል ይሠራሉ ? የጎንዮሽ ጉዳቶችስ ይኖሯቸው ይሆን? ለምን ያህል ጊዜስ ይከላከላሉ ?  ውጤታማነታቸውስ?
ባዮንቴክና ፊዘር  የተባሉ ሁለት የመድሃኒት አምራች ኩባንያዎች ያለፈው ሳምንት መጀመሪያ ይፋ ያደረጉት የኮሮና ተዋህሲ መከላከያ ክትባት ካለፈው ሐምሌ ወር  ጀምሮ  50 ሺህ በሚጠጉ ሰዎች ላይ ተሞክሯል።  በሙከራው በኮቪድ-19 በሽታ የመያዝ አደጋን 90 በመቶ እንደሚቀንስ የጀርመኑ ባዮንቴክ ኩባንያ መስራች የሆኑት ሁጎ ሻሂ ገልፀዋል።
ሞደርና በተባለው የአሜሪካ የመድኃኒት አምራች ኩባንያ  ባለፈው ሰኞ ይፋ የተደረገው የመከላከያ ክትባት ደግሞ  94 በመቶ በላይ  ውጤታማ ነው ተብሏል፡፡
የኩባንያው ዋና ስራ አስፈፃሚ ስቴፋኔ ባንሴል እንደሚሉት በክትባቱ ላይ በተደረገው ሶስተኛ ደረጃ ክሊኒካዊ ሙከራ መሰረት ይህ አዎንታዊ ውጤት ተረጋግጧል፡፡በኮቪድ-19 በሽታ የመያዝ ዕድልን በእጅጉ ይቀንሳል ።  
እንደ ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት አንድ ክትባት ተቀባይነት የሚያገኘው ነት፣ ጥራቱና ደህንነቱ የተጠበቀ መሆንና በሽታ ተከላከይነቱ ላይ በሚያቀርበው መረጃ መሰረት ነው።በዚህ መሰረት
 ለአንድ ክትባት ከ94 በመቶ በላይ ውጤታማ ነው ማለት በጣም ትልቅ ዉጤት መሆኑን በአሜሪካ የሀርባርድ ዩንቨርሲቲ የተላላፊ በሽታዎች ባለሙያ የሆኑት ኤሪክ ፋይገል ዲንግ ገልፀዋል።
ክትባትን ለማበልፀግ ተመራማሪዎች  የተለያዩ ዘዴዎችን የሚጠቀሙ ሲሆን ውጤታማነቱም በርከት ያሉ ዓመታትን የሚወስድ ነው።ይሁን እንጅ ፤የፒፊዘር እና ሞደርና ክትባቶች  ከተለመደው የክትባት ማምረት መንገድ  ወጣ ብለው «ሜሴንጀር አር ኤን ኤ» በተሰኘ አዲስ  መንገድ የተገኘ ነው። ይህ  ዘዴ  ዘረ -መል ላይ የተመሰረተ  ሲሆን በሰዎች ላይ የሚደረገው ሙከራ  በጥቂት ወራት  ሊከናወን ይችላል።ያ በመሆኑ ምናልባት የክትባቱን ደህንነትና የጥራት ደረጃን  ጥያቄ ውስጥ ያስገስባል የሚሉ አሉ። ተመራማሪው ኤሪክ ፊገል ግን በውጤታማነታቸው ላይ ጥርጥሬ የላቸውም።በመሆኑም ውጤቱ በሳይንስ ሊቃውንቱ ዘንድ ትልቅ ተስፋ አሳድሯል።በጀርመን  ሬገንስበርግ ዩንቨርሲቲ ክሊኒክ የተላላፊ በሽታዎች ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ቤንዝ ዛልስቤርገርም የኮሮና ወረርሽኝ በተለይም በአውሮፓና በአሜሪካ በርካቶችን በሚያጠቃበት በዚህ ወቅት  የክትባቶቹ  መገኘት የሚያበረታታ ነው ይላሉ።ለምን ያህል ጊዜ እንደሚከላከል ግልፅ መረጃ ባይኖርም።
«እርግጥ እነዚህ ክፍት ጥያቄዎች ናቸው።አሁኑ ወቅት ልንመልሳቸው አንችልም።ምክንያቱም የክትባት ውጤታማነት ብዙ ወራትን ይወስዳል።አሁን የምናውቀዉ አስፈላጊው ነገር በክትባት በሽታዉን መከላከልና ለወደፊቱ መደበኛ ህይወትን እንደገና  መቀጠል እንደምንችል ነው።»
የሞደርና ክትባት  ከ 2 ዲግሪ ሴልሺየስ እስከ 8 ዲግሪ ሴልሺየስ (36 ዲግሪ ፋራናይት እስከ 46 ዲግሪ ፋራናይት) በሚደርስ መደበኛ የሙቀት መጠን  መቀመጥ ይችላል።  በሌላ በኩል የባዮንቴክና የፒፊዘር ክትባት  ማቀዝቀዣ  ውስጥ ማቆየትን ይጠይቃል።ይህም ምናልባትም የክትባት የአቅርቦቱን ሰንሰለት ሊያወሳስብ ይችላል ተብሏል።
በመጭው ታህሳስ ወር ከአሜሪካ የመድሃኒት አስተዳደር ባለስልጣናት   ማረጋገጫ ያገኛሉ ተብሎ የሚጠበቀው የሞዴርና ክትባት፤ በአሜሪካ ብሔራዊ የጤና ተቋማት በጋራ የተገነባ ሲሆን ለአንድ ሰው የሚሰጠው የክትባት መጠን በ 28 ቀናት ልዩነት ሁለት ጊዜ ነው።የሚያመጣዉን የጎንዮሽ ጉዳት  ግን እስካሁን በውል አለመታወቁን ፕሮፌሰር ቤንዝ ዛልስቤርገር ያስረዳሉ።
«በጣም የተወሰነ መረጃ ነው ያለን።የጎንዮሽ ጉዳትን በተመለከተ ነገር ግን በጣም የከፋ የጎንዮሽ ጉዳት አልተመዘገበም።ትክክለኛውን መረጃ ለመስጠት በእርግጥ ቁጥራቸውን  በትክክል ማወቅ አለብን።አሁን  ያለነው ክትባቱን የአጭር ጊዜ ምልከታ  ላይ ነው። እናም ክትባቱ ፈቃድ ከማግኘቱ በፊት ክትባቱ  ከተሞከረባቸው ሰዎች ግማሽ ያህሉ ቢያንስ  ለሁለት ወራት ክትትል ሊደረግ ይገባል።»
በዚህ ክትባት ሙከራ 30 ሺህ አሜሪካውያን የተሳተፉ ሲሆን በመጭዎቹ ሳምንታት 2 ሚሊየን  ክትባት ይመረታል ተብሏል።በቀጣዩ የፈረንጆቹ
ዓመት ደግሞ 1 ቢሊየን  ክትባት በዓለም ዙሪያ ለማሰራጨት ዕቅድ መያዙን ኩባንያው  ይፋ አድርጓል።ባዮንቴክና ፌዘርም ክትባት ማምረቱን ቀደም ብለው መጀመራቸውን አስታውቀዋል።
ከነዚህ ሁለት ክትባቶች በተጨማሪም ባለፈው ሳምንት ሩስያ 92 በመቶ ተዋህሲውን የመከላከል አቅም አለው ያለችውን ክትባት ይፋ አድርጋለች፡፡
የክትባቶቹ ዉጤታማነት ምንም ይሁን ምን  ወረርሽኙን  ለመከላከል የሚረዱ የጥንቃቄ ርምጃዎችን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ባለሙያዎች በማሳሰብ ላይ ናቸው።የዓለም የጤና ድርጅት ሀላፊ ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም በበኩላቸው የክትባቶቹ መገኘት መልካም ቢሆንም በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመር ግን አሁንም አሳሳቢ መሆኑን ገልፀዋል።
«ይህ  የእፎይታ ጊዜ አይደለም። ምንም እንኳ የኮቪድ -19 ክትባትን በተመለከተ የሚያበረታቱ  ዜናዎችን መቀበል የቀጠልንበት ጊዜ ቢሆንም። በጥንቃቄ በሚቀጥሉት ወራት አዳዲስ መሳሪያዎች  መምጣት እንደሚጀምሩም ተስፋ እናደርጋለን።ላሁኑ ግን በአንዳንድ ሀገሮች የምናየው በተዋህሲው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመር እጅግ በጣም ያሳስበናል።»ነው ያሉት።

Coronavirus | Impfstoff | Pfizer
ምስል Zeljko Lukunic/PIXSELL/picture alliance
Deutschland | Coronavirus | Impfstoff Schott
ምስል Schott
USA Coronavirus Impfstoff-Test
ምስል H. Pennink/AP Photo/picture-alliance

ፀሐይ ጫኔ
ሂሩት መለሰ