1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አዲሱ የጀርመን መንግሥትና ተግዳሮቶቹ 

ማክሰኞ፣ ኅዳር 28 2014

17ቱ የአዲሱ ካቢኔ አባላት ነገ ቃለ መሃላ ይፈጽማሉ ተብሎይጠበቃል። የአዲሱ የጀርመን መንግስት ምስረታ ሂደት ከከዚህ ቀደሙ የመንግሥት ምስረታ በተለየ ብዙ ውጣ ውረድ ያልታየበት፣ውዝግብም ያልተሰማበት ነው። ከሁለት ወራት ድርድር በኋላ ሶስት የተለያየ መርህ የሚከተሉ ፓርቲዎች ተግባብተው በጥምረት ጀርመንን ለመምራት መስማማታቸው ተወድሷል።

https://p.dw.com/p/43xVG
Symbolbild Koalitionsvertrag Ampel-Parteien
ምስል Markus Schreiber/AP/picture alliance

አዲሱ የጀርመን መንግሥትና ተግዳሮቶቹ 

አዲሱ የጀርመን መንግሥት ነገ በጀርመን የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ቃል መሃላ ይፈጽማል። ምክር ቤቱ የመስከረሙ የጀርመን ምርጫ አሸናፊ የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ መሪ የኦላፍ ሾልዝን መራሄ መንግሥትነት ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል። ሦስት ፓርቲዎች የተጣመሩበት የአዲሱ የጀርመን መንግስት ምስረታና ተግዳሮቶቹ የዛሬው አውሮጳና ጀርመን ዝግጅታችን ትኩረት ነው።
ጀርመንን ተጣምረው ለመምራት የተስማሙት የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ በጀርመንኛው ምህጻር ኤስ ፔ ዴ፣አረንጓዴዎቹና እና የነጻ ዴሞክራቶቹ ፓርቲ በጀርመንኛው ምህጻር ኤፍ ዴ ፔ አዲስ መንግሥት ለመመስረት የሚያበቃቸውን ዝግጅት አጠናቀዋል። የሦስቱ ፓርቲዎች መሪዎች በፓርቲዎቹ አርማ ቀለም  የትራፊክ መብራት የሚል ስያሜ የተሰጠውን ጥምረት ውል ዛሬ ፈርመዋል። ባለ 177 ገጽ የጥምረት ውል የተፈረመው የሦስቱም ፓርቲዎች አባላት ይሁንታ ከተገኘ በኋላ ነው። የጀርመን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ ነገ የአሸናፊው የኤስ ፔዴ ፓርቲ መሪ ኦላፍ ሾልዝን መራኄ መንግስትነት ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል። ሾልዝን ጨምሮ ከስስቱም ፓርቲዎች የተውጣጡት 17 የአዲሱ ካቢኔ አባላትም ነገ ቃለ መሃላ ይፈጽማሉ ተብሎም ነው የሚጠበቀው። የአዲሱ የጀርመን መንግስት ምስረታ ሂደት ከከዚህ ቀደሞቹ የመንግሥት ምስረታ ድርድሮች በተለየ ብዙ ውጣ ውረድ ያልታየበት፣ውዝግብም ያልተሰማበት ነበር። ከሁለት ወራት ድርድር በኋላ ሶስት የተለያየ መርህ የሚከተሉ ፓርቲዎች ተግባብተው በጥምረት ጀርመንን ለመምራት መስማማታቸው ተወድሷል። ይህን ካደነቁት አንዱ ከ30 ዓመታት በላይ እዚህ ጀርመን የኖሩት የምጣኔ ሀብት ምሁሩ ዶክተር ጸጋዬ ደግነህ ናቸው። የክርስቲያን ዴሞክራቶቹ ፓርቲ ካሸነፈበት ከዛሬ አራት ዓመቱ ምርጫ በኋላ የመንግሥት ምስረታው ድርድር እንደአሁኑ ፈጣን እንዳልነበረ የዶቼቬለ የበርሊን ዘጋቢ ይልማ ኃይለ ሚካኤል ከነ ምክንያቱ ጭምር ያስታውሳል።
ከአዲሱ ካቢኔ አባላት ኦላፍ ሾልዝን ጨምሮ ስምንቱ ከኤስ ፔ ዴ፣ አምስቱ ከአረንጓዴዎቹ እንዲሁም አራቱ ከነጻ ዴሞክራቶቹ ናቸው። ዋና ዋናዎቹን ለመጥቀስ ያህል የገንዘብ ሚኒስትር የኤፍ ዴ ፔው መሪ ክርስቲያን ሊንድነር ከአረንጓዴዎቹ ፓርቲ መሪዎች አንዷ አነ ሌና ቤርቦክ  የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሌላው የፓርቲው መሪ ሮበርት ሀቤክ የኤኮኖሚና የአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ሚኒስትርና ምክትል መራኄ መንግሥት እንዲሁም ታዋቂው ሐኪም የኤስፔዴው ካርል ላውተርባህ በጤና ሚኒስትርነት ተሹመዋል።

Deutschland Regierungsbildung l Koalition von SPD, die Grünen und FDP, in Berlin
ምስል Abdulhamid Hosbas/AA/picture alliance
BG Deutschland neue Bundesregierung
ምስል Ralph Pache/PRESSCOV/ZUMAPRESS.com/picture alliance

ከ16 ዓመታት የመራኂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የስልጣን ዘመን በኋላ ጀርመንን የሚመራው የአዲሱ መንግሥት ብቃት ጥያቄ ውስጥ መግባቱ አልቀረም። በተለይም ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ በዙ አድናቆት የሚቸረው የተሰናባቿ የአንጌላ ሜርክል የአመራር ብልሀትና ጥበብ የርሳቸውን ቦታ በሚተካው ሰው አለ የለም የሚለው ከአነጋጋሪዎቹ ነጥቦች አንዱ ነው። ነገ ስልጣኑን ይረከባሉ ተብለው የሚጠበቁት ኦላፍ ሾልዝ  ጀርመንንም ሆነ የአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራትን ከገጠሟቸው የጋራ ቀውሶች የሚያወጡ መፍትሄዎችን በማፍለቅና በመተግበር የሚታወቁትን የሜርክልን ያህል ብቃት ይኖራቸዋል የሚለውም እንዲሁ። ለምጣኔ ሀብት ምሁሩ ለዶክተር ፀጋዬ ደግነህ ይህ ለሜርክል ተተኪ ለሾልዝ ከባድ ፈተና መሆኑ አይቀርም። 
ይልማ እንደሚለው ደግሞ ከሜርክል ጋር በምክትል መራሄ መንግስትነት ለሰሩትና የገንዘብ ሚኒስትርም ለነበሩት ለሾልዝ ይህ አያሳስብም። የጀርመን የፖለቲካ ውሳኔ በአንድ ሰው ሃሳብ ላይ ብቻ የሚመራ ስላልሆነም እንደ ችግር የሚነሳም አይደለም ይላል ይልማ።
በመራኂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የስልጣን ዘመን የስራና የማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር እንዲሁም የገንዘብ ሚኒስትርና ምክትል መራሄ መንግሥት ሆነው ያገለገሉት  ሾልዝ ወደፊት የሚመሩት አዲሱ መንግሥት ከፊቱ የተለያዩ ተግዳሮቶች ይጠብቁታል። ከነዚህም አንዱ አሁንም እንደገና ያገረሸው የኮሮና ወረርሽኝ ነው። ወረርሽኙ ሰዎችን ከመግደልና ለከፋ ህመም ከመዳረግ በተጨማሪ የሀገሪቱን ኤኮኖሚ እየጎዳ ነው። ኮሮናን ጨምሮ ለተለያዩ ችግሮች መፍትሄ በመሻት ረገድ ደግሞ ከአዲሱ ካቢኔ ብዙ ይጠበቃል። እነዚህም በአዲሱ መንግሥት ላይ ጫና የሚያሳድሩ ጉዳዮች መሆናቸው እንደማይቀር ነው ዶክተር ጸጋዬ የተናገሩት ።
ይልማ እንዳለው የተለያየ አቋም ያላቸው ሦስት የጀርመን ፓርቲዎች ለ2 ወራት ተደራድረው በተስማሙበት የጥምረት ውል መሰረት ከሚመሩት ከአዲሱ የጀርመን መንግሥት ብዙ ይጠበቃል። ከመካከላቸው የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ድርሻ ከፍ ይላል።

Angela Merkel
ምስል John MacDougall/picture-alliance/AP

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ